March 31, 2024 – Konjit Sitotaw 

ንግድ ባንክ በንዝህላልነት እና በግዴለሽነቱ የጠፋበትን ገንዘብ ፍለጋ ወደ ቁማር ቤቶች መዝመቱ ተሰምቷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለ አግባብ የራሳቸው ያለሆነን ገንዘብ ከባንኩ ወስደው ወደ ቤቲንግ ተቋማት ያዘዋወሩ ሰዎች ባንክ በመገኘት ለዚሁ የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት እንዲያመለክቱ አሳሰበ፡፡

ባንኩ መጋቢት 6 ቀን 2016 ባጋጠመው የሲስተም ችግር ምክንያት ያለአግባብ የገንዘብ ልውውጥ እንደነበር አስታውሷል።

በዚህም በርካታ ግለሰቦች በጥሬ ገንዘብ እና በዲጂታል የክፍያ አማራጮች የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ እንደሚገኙም ገልጿል፡፡

ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ ወደ ቤቲንግ ተቋማት በማዛወራቸው መመለስ እንደተቸገሩ መጠቆማቸውንም ጨምሮ አስታውቋል፡፡

በዚህም “ገንዘቡን ተመላሽ ማድረግ እንዲቻል ወደ ቤቲንግ ተቋማት የራሳችሁ ያልሆነውን ገንዘብ ያዘዋወራችሁ አቅራቢያችሁ በሚገኝ የባንካችን ቅርንጫፍ በመገኘት ለዚሁ የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላት እንድታመለክቱ እናሳስባለን” ሲል መልዕክቱን ያስተላለፈው ንግድ ባንክ በንዝህላልነት እና በግዴለሽነቱ የጠፋበትን ገንዘብ ፍለጋ ወደ ቁማር ቤቶች መዝመቱን የገለጸ ሲሆን ሆን ተብሎ ፖለቲከኞች የሰገሰጓቸው ሰራተኞቹ በሰሩት ተንኮል በቀጣይነትም ከዘረፋ እንደማያመልጥ ታውቋል።