ቱርክ

1 ሚያዚያ 2024, 07:54 EAT

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን በአካባቢ ምርጫ ያልተጠበቀ ሽንፈት አጋጠማቸው።

ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ አንካራ እና ኢስታንቡልን ጨምሮ በዋና ዋና የቱርክ ከተሞች የተደረገውን ምርጫ አሸንፏል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን በተለይ ተወልደው ባደጉባት እና ከንቲባ ሆነው በመሯት ኢስታንቡል እንደሚያሸንፉ በመተማመን ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነበር።

ይሁን እንጂ እአአ 2019 ላይ በከተማው በተደረገ የአካባቢ ምርጫ አብላጫውን ድምጽ አግኝተው የነበሩት ኤክሬም ኢማሞግሉ ፓርቲ አሸንፏል።

ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን የ16 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ለሆነችውን ኢስታንቡል አዲስ ዘመን አመጣለሁ ብለው ቅስቀሳ ቢያደርጉም ሳይሰምርላቸው ቀርቷል።

ተቃዋሚ ፓርቲው ሲኤችፒ ከኢስታንቡል በተጨማሪ አንካራ፣ እዝሚር፣ ቡርሳ፣ አዳና እና የመዝናኛ ከተማ በሆነችውን አንታላያ አሸናፊ ሆኗል።

ኤርዶሃን በበርካታ የቱርክ ከተሞች በተደረገው የአካባቢ ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ በመዲናዋ አንካራ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ይህ የኤኬ ፓርቲ መጨረሻ ሳይሆን ለውጥ የምናመጣበት አጋጣሚ ይፈጥርልናል ብለዋል።

የኤርዶሃን ፓርቲ ከ21 ዓመታት በፊት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በአካባቢ ምርጫ በመላው አገሪቱ በሚገኙ ዋነኛ ከተሞች ሽንፈት ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው ነው።

ፕሬዝዳንታዊ የስልጣን ዘመናቸው እአአ 2028 ላይ የሚያበቃው ኤርዶሃን በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት በአካባቢ ምርጫ የሚሳተፉት ይህ ለመጨረሻ ጊዜ መሆኑን ተናግረው ነበር።

ተንታኞች ግን ኤርዶሃን በአካባቢ ምርጫ የተሻለ ድምጽ ቢያገኙ ኖሮ በስልጣን መቆየት እንዲቻላቸው ሕገ-መንግሥቱን ማሻሻል ላይ ይሰሩ ነበር ይላሉ።

በኢስታንቡል የተደረገውን ምርጫ ያሸነፉት ኤክሬም ኢማሞግሉ
የምስሉ መግለጫ,በኢስታንቡል የተደረገውን ምርጫ ያሸነፉት ኤክሬም ኢማሞግሉ

በአንጻሩ የተቃዋሚ ፓርቲው ሲኤችፒ ሰብሳቢ ኦዝጉር ኦዜል ቱርካውያን በአገራቸው አዲስ የፖለቲካ ሰርዓት እንዲኖር ፍላጎት እንዳላቸው በድምጽ መስጫ ካርድ አረጋግጠዋል ብለዋል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች በኢስታንቡል ጎዳናዎች ላይ የቱርክን ሰንደቅ ዓላማ ይዘው ወጥተዋል።

ኢስታንቡል 85 ሚሊዮን ከሚሆነው ከአጠቃላይ የቱርክ ሕዝብ አንድ አምስተኛውን ትይዛለች። ይህችን ከተማ መቆጣጠር ንግድ፣ ቱሪዝም እና ፋይናንስን ጨምሮ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብት እንደመቆጣጠር ይታያል።

በዚህም በኢስታንቡል የተደረገውን ምርጫ ያሸነፉት ኤክሬም ኢማሞግሉ እአአ 2028 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ሊቀርቡ እንደሚችሉ በሰፊው ተገምቷል።