
ከ 3 ሰአት በፊት
በእስራኤል ያለው የፖለቲካ ልዩነት በድጋሚ አደባባይ ወጥቷል።
ሐማስ መስከረም 26 የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል ብሔራዊ አንድነት የታየ መስሎ ነበር። ከስድስት ወራት በኋላ ግን እስራኤላውያን ለተቃውሞ ወደ ጎዳናዎች መትመም ጀምረዋል።
ቤንያሚን ኔታንያሁ ለረዥም ዓመታት በጠቅለይ ሚንስትርነት እስራኤልን አስተዳድረዋል። የአሁኑ ጦርነት ግን ከስልጣን እንዲወርዱ የሚደረገውን ግፊት አቀጣጥሎታል።
የእየሩሳሌም ፖሊስ መጥፎ ሽታ ያለው ውሃ በመርጨት ሰልፈኞችን ለመበተን ተገዷል። ሠልፈኞቹ በከተማዋ የሚገኘውን አውራ ጎዳን ዘግተው ነበር።
ኔታንያሁ በፍጥነት ከስልጣን እንዲወርዱ፤ ከግዜ ሰሌዳው በፊት ምርጫ እንዲከናወን እና አሁንም በሐማስ እጅ የሚገኙ 130 ታጋቾች እንዲለቀቁ በአፋጣኝ ስምምነት ይደረስ ሲሉም ጠይቀዋል።
ጦርነቱ በቀጠለ ቁጥር ታግተው ያሉት ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት በቤተሰቦቻቸው፣ በጓደኞቻቸው እና በተቃዋሚዎች ዘንድ ስጋት ተፈጥሯል።
እስራኤል በጋዛ በምታደርገው ጦርነት እየተሳተፈ የሚገኝ ልጅ ያላት ካትያ አሞርዛ መፈክር የምታሰማበትን ሜጋፎን ዝቅ አድርጋ ሐሳቧን ማከፈል ጀመረች።
“ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እዚሁ ነበርኩ። የአንድ ጉዞ ቲኬት ገዝቼ ከአገር ወጥቶ ተመልሶ እንዳይመጣ ለማድረግ ደስተኛ መሆኔን ለኔታንያሁ እየነገርኩ ነው” ትላለች።

“በአስተዳደሩ ውስጥ የሰገሰጋቸውን ሰዎች አንድ በአንድ ይዞ ከአገር እንዲወጣ ነው የምነግረው። ይህ በማህረሰባችን የመጥፎ መጥፎው አስተዳደር ነው።”
በዚህ በተቃውሞ ስፍራ እያለፉ የነበሩት የአይሁድ የሃይማኖት መሪ ከካቲያን የተለያ ሐሳብ አላቸው።
ግሊክ የተባሉት የሃይማኖት መሪ ተቃዋሚዎቹ እውነተኛ ጠላታቸው ረስተዋል ይላሉ።
እንደእሳቸው ከሆነ የተቃዋሚዎቹ ዋነኛ ጠላት ሐማስ እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ አይደሉም።
“እሱ በጣም ተወዳጅ እንደሆነ አስባለሁ። እነዚህ ሰዎች ለረዥም ጊዜ ተቃውመውት አሁንም ስልጣን ላይ የመሆኑን እውነታ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አይደሉም።”
“ሠላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ፤ ደጋግመው እንዲመጡ በሠላማዊ መንግድ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚሰማቸውን በግልጽ እንዲናገሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ሆኖም ግን በዲሞክራሲ እና በስርዓተ አልበኝነት መካከል ያለውን ቀጭን መስመር እንዳያልፉ መጠንቀቅ አለባቸው” ብለዋል።

ተቃዋሚዎቹ እና የኔታንያሁን ተቺዎች በጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዳደር ውስጥ የዴሞክራሲ ጠላቶች እንዳሉ ያምናሉ።
ከእነዚህም መካከል በገንዘብ ሚኒስትሩ ባዛል ስሞትሪች የሚመራው ሪሊጂየስ ዛዮኒዝም ፓርቲ ይገኝበታል። ከፓርቲው የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት ኦሃድ ታል በሐማስ ላይ ከሚደረገው ወታደራዊ ጫና ውጪ ታጋቾቹን የሚያስፈታ ሌላ አማራጭ አለ ብሎ ማመን “የዋህነት” ነው ይላሉ።
“ሐማስ ታጋቾቹን በቀላሉ በስምምነት የሚመልስ እንዳይመስላችሁ። በስምምነት ሁሉንም ፈትቶ በቀላሉ ሁሉንም ሽብረተኞች እንድንገላቸው አይፈቅድልንም… ቀላል አይደለም።”
ቤንያሚን ኔታንያሁ የአገራቸውን ደህንነት መጠበቅ የሚችሉት እሳቸው ብቻ እንደሆኑ ደጋግመው ይገልጹ ነበር። ብዙ እስራኤላውያንም አምነዋቸዋል።
ይህ ሁሉ ግን ሐማስ መስከረም 26 ድንበር ተሻግሮ ባደረሰው ጥቃት ተለወጠ።

ሐማስ ላደረሰው አሰቃቂ ጥቃት እና ለደረሰው የደህነነት እጦት በርካታ እስራኤላዊያን ጣታቸውን ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ እየጠቆሙ ነው።
የኔታንያሁ የደህንነት ኃላፊዎች በፍጥነት መግለጫ በማውጣት ኃላፊነት ወስደዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን እስካሁን የወሰዱት ኃላፊነት የለም።
ይህ ደግሞ እሑድ ምሽት የእየሩሳሌም መንገዶችን የዘጉትን በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን አስቆጥቷል።
ቤንያሚን ኔታንያሁ ዓለም ያወቃቸው በተባበሩት መንግስታት የእስራኤል አንደበተ ርቱዕ ቃል አቀባይ ሆነው ብቅ ካሉ በኋላ ነው። ለመጀመርያው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የሆኑት በ1996 በጠባብ ውጤት በማሸነፍ ነበር። ለድሉ ያበቃቸው የኦስሎን የሠላም ሂደትን መቃወማቸው የፈጠረላቸው ድጋፍ ነው።
ልክ አሁን አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ሠላም ለመፍጠር በምታቅደው መሠረት የኦስሎ ስምምነትም ፍልስጤማውያን የእስራኤል ጎረቤት ሆነው ነፃ አገር እንዲመሠርቱ ይፈቅዳል። ይህም የሆነው በአረቦች እና በአይሁዶች መካከል ለዘመናት የዘለቀው ግጭት እንዲያበቃ ብቸኛው ተስፋ ነው በሚል ሐሳብ ነው።

ኔታንያሁ የፍልስጤም መንግስት እንዳይመሠረት በቋሚነት ተቃዋሚ ነበሩ። አሜሪካ ለፍልስጤም ነፃነት የምትደግፈውን ስትራቴጂ መካከለኛው ምስራቅን እንደገና የመፍጠር “ትልቅ የድርድር” አካል አድርገው በንቀት ውድቅ አድርገውታል።
ለተቃውሞ ከተሰበሰቡ መካከል አንዱ ዴቪድ አግሞን ናቸው። ዴቪድ ከእስራኤል ጦር በጡረታ የወጡ ብርጋዴር ጄኔራል ሲሆኑ ኔታንያሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመረጡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽህፈት ቤት መርተዋል።
“ከ1948 ወዲህ ያጋጠመን ትልቁ ቀውስ ነው። ሌላ ነገር መጨመር እፈልጋለሁ። በ1996 ኔታንያሁ ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ሲሆን ጽህፈት ቤቱን መራቻለሁ፤ ስለዚህ አውቀዋለሁ። ከሦስት ወራት በኋላ ግን ለመልቀቅ ወሰንኩ። ምክንያቱም ለእስራኤል አደጋ እንደሆነ ተገነዘብኩ” ብለዋል።
“ውሳኔዎችን እንዴት እንደሚወሰዱ አያውቅም፣ ይፈራል። የሚያውቀው ብቸኛ ነገር መናገር ነው። በእርግጥ በሚስቱ ላይ የተማመነ እንደሆነ አይቻለሁ። ውሸቱንም አየሁ። እናም ከሦስት ወራት በኋላ ‘ቢቢ’ ረዳቶች ሳይሆን የሚተካው ነው የሚያስፈልግህ ብዬው ወጣሁ።”

ተቃዋሚዎቹ ጎዳናዎችን ማጨናነቃቸውን ቢቀጥሉም ኔታንያሁ ከተያዘለት መርሐ ግብር በፊት የሚደረግ ምርጫ የለም ብለዋል። በራፋህ በሐማስ ኃይሎች ላይ አዲስ ጥቃት ለመሰንዘር ያላቸውን ቁርጠኝነትም ደግመዋል።
ፖለቲካ ውስጥ በተደጋጋሚ ከውድቀት መትረፍን የለመዱት እና በምርጫ ቅስቀሳ የማይታሙት ኔታንያሁ፤ ምርጫ ይደረግ ቢባል እራሱ እንደሚያሽንፉ ቁጥራቸው ከተመናመነው ታማኝ ደጋፊዎቹ ዘንድ ይደመጣል።
እስራኤላውያን ሐማስን በማጥፋት ዙሪያ አልተከፋፈሉም። የጦርነቱ ዓላማ ከፍተኛ ድጋፍ አለው።
ጦርነቱ እየተካሄደበት ያለበት መንገድ እና ታጋቾቹን በሙሉ ለማዳን ወይም ለማስለቀቅ አለመቻሉ ቤንያሚን ኔታንያሁን የፖለቲካ ህይወታቸው ማብቂያ ላይ እያደረሳቸው ይገኛል።