
ከ 6 ሰአት በፊት
በአውሮፓውያን አቆጣጠር ዛሬ ኤፕሪል 1/2024 ነው። ይህ ዕለት በመላው ዓለም ብዙዎች ከአንድ ነገር ጋር ያያይዙታል። ይህም ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ከሚባለው ሰዎችን በሐሰተኛ ነገር ከማስደንገጥ እና ከማሞኘት ጋር ነው የሚያያዘው።
ምንም እንኳን ይህ ዕለት ከኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር እና ልማድ ጋር የሚያዛምደው ነገር ባይኖርም፣ በወጣቶች ዘንድ ቤተሰብ እና ጓደኛን በውሸት “ክው” ማድረግ በዚህ ዕለት ያጋጥማል።
ምንም እንኳን ቀልድ እና ሳቅን የሚፈጥሩ አጋጣሚዎች ቢኖሩም፣ በዚህ ዕለት በአብዛኛው ብዙዎች በሚሰሙት ድንገተኛ እና አስደንጋጭ ነገር ከባድ ሐዘን እና ድንጋጤ ውስጥ ከመግባት ባሻገር ጉዳትም የገጠማቸው ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።
ይህ ልማድም በጊዜ ሂደት ወደ ተለያዩ አገራት በመስፋፋት አሁን ካለንበት ዘመን ላይ ደርሷል። አሁን ባለበት ሁኔታ ዕለቱ በቀዳሚነት መታሰብ ጀምሯል ተብሎ የሚገመተው በ1500ዎቹ በፈረንሳይ እና በሆላንድ ውስጥ ነው ይባላል። ከዚያም ወደ ሌሎቹ የአውሮፓ አገራት እየተስፋፋ መጥቷል።
ለመሆኑ ይህ የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ልማድ እንዴት ጀመረ? ተብሎ ቢጠየቅ በትክክል ይህ ነው ተብሎ የሚነገር ወጥ ታሪክ የለም። ነገር ግን ስለጅማሬው የተለያዩ ታሪኮች እና መላምቶች ይነገራሉ።
በዚህ አጋጣሚ ዛሬ የፈረንጆቹ ሚያዝያ 1 (ኤፕሪል 1) መሆኑን በማስታወስ ለማስጠንቀቅ እንወዳለን።
- የአእምሮ ጤና እክል የሆነው ባይፖላር ዲስኦርደር ምንድን ነው? ለምንስ ከታዋቂው ሠዓሊ ጋር ተያያዘ?30 መጋቢት 2024
- የኩላሊታችንን ጤና ለመጠበቅ የሚያግዙ 6 ቀላል መንገዶች29 መጋቢት 2024
- ብዙ ንጥረ-ነገሮች የሚጨመሩባቸው በፋብሪካ የሚቀነባበሩ ምግቦች እና በጤና ላይ የሚያስከትሉት ጠንቅ30 መጋቢት 2024
ከግጥም ታሪክ ላይ መገኘቱ
ታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት ይህ ሰዎችን የማሞኘት የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ታሪክ አመጣጥን በተመለከተ በርካታ እና የተለያዩ ታሪካዊ ዳራዎች የቀርባሉ።
ቢሆንም ግን ሁሉም ከበርካታ ክፍለ ዘመናት በፊት ከሰዎች የዘመን አቆጣጠር ጋር እና ተፈጥሯዊ ክስተት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መላ ምቶች እና ታሪኮችን ይጠቅሳሉ።
ከእነዚህም መካከል የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ልማድ የሚጀመረው ከአንድ ጥንታዊ የግጥም ታሪክ ጋር ነው በማለት ጅማሬውን የሚጠቅሱ የታሪክ አጥኚዎች አሉ።
ጄፍሪ ቹሰር የተባለው ቀደምት እንግሊዛው ገጣሚ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በጻፈው የግጥም ታሪክ ላይ በዚያ ዕለት አንድ ቀበሮ አውራ ዶሮን ሲያሞኝ የሚተርክ ግጥም ጽፎ ነበር። ይህም ከ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ጋር የሚዘመድ ቀደምት ታሪክ እንደሆነ ይታመናል።
በእርግጥ ገጣሚው በቀጥታ በታሪኩ ውስጥ ኤፕሪል አንድን አልጠቀሰም። ነገር ግን በግጥሙ ላይ “የመጋቢት (ማርች) ወር በገባ በ32ኛው ቀን ላይ” በሚል ዕለቱን ማመልከቱ ይጠቀሳል። ይህም ኤፕሪል 1 ማለቱ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል።
ነገር ግን የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ መነሻ ታሪክን ከዚህ ገጣሚ ሥራ ጋር መያያዙን የሚያመለክተውን መላምት የማይቀበሉ ሰዎች፣ በግጥሙ ውስጥ ገጣሚው ግራ አጋቢ ቃላትን በመጠቀም አስቂኝ ነገር ለመፍጠር መሞከሩ እንጂ ከዕለቱ ጋር የሚያይዘው ነገር የለም ይላሉ።

ከአዲስ ዓመት ጋር መያያዙ
አንዳንዶች ደግሞ የኤፕሪል ዘ ፉልስ ታሪክ የጀመረው ከዘመን አቆጣጠር እና ከወቅቶች መቀያየር ጋር በተያያዙ ክስተቶች ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ።
ይህም በሮማውያን ጊዜ ይከበር ከነበረው “የመታደስ ክብረ በዓል” ጋር ቁርኝት እንዳለው በምሳሌ ያስረዳሉ። ይህ በዓል በአዲስ ዓመት ወይም በአዲስ ወቅት መጀመሪያ ላይ ይከበር የነበረ ነው።
ከዚህ በዓል ጋር በተያያዘም በዘመኑ በሌላው ጊዜ ይካሄዱ የነበሩ መደበኛ የአኗኗር ዘይቤዎች ይገለባበጣሉ። የማይሆነው ይሆናል፤ ሲደረግ የነበረው በዚያ ዕለት ቦታውን ይለቃል።
ታሪክ አጥኚዋ አንድሪያ ላይቭሴይ እንደሚሉትም በበዓሉ ዕለት “አሽከሮች በጌቶቻቸው ላይ፣ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ የበላይ ይሆናሉ” በዚህም በሌላው ጊዜ የማይታሰበው የሐሰት የበላይነት በቀኑ ይነግሳል።
በዚህ ጊዜ መጋቢት (ማርች) የፀደይ ወቅት ጅማሬ በመሆኑ አበቦች በሚበቅሉበት ጊዜ በርካቶች የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ወር አድርገው የስቡ እና የሚያዝያ (ኤፕሪል) መጀመሪያ ዕለትን የአዲስ ዘመን መክፈቻ በማድረግ ያከብሩት ነበር።
ከዘመናት በኋላም ይህ የአዲስ ዓመት ጅማሬ ዕለት ከመጋቢት (ማርች) ማብቂያ አሁን ወዳለበት ጃንዋሪ (ጥር) ሲሸጋሸግ፣ የቀደመውን ልማድ ይዘው ለመዝለቅ የወሰኑት በኤፕሪል አዲስ ዓመትን መቀበል ቀጠሉ። በዚህም ሳቢያ እነዚህ ሰዎች እንደሞኝ ይቆጠሩ ጀመር።
በዚህም ምክንያት የኤፕሪል ወር የመጀመሪያ ቀን “የሞኞቹ” አዲስ ዓመት ቀን ነው በሚል ያ ዕለት አሁን ድረስ ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ይባላል የሚል ታሪክ አለ።
‘ኤፕሪል ዘ ፊሽ ዴይ’
ሌላው ደግሞ በፈረንሳይ እና በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ይህንን ዕለት ከተፈጥሯዊ ክስተት ጋር በማያያዝ በተለየ ስያሜ ሲያስቡት ኖረዋል።
በዚህም ዕለቱን ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ሳይሆን ‘ኤፕሪል ዘ ፊሽ ዴይ’ በማለት ሰይመው ለዘመናት ሲያስቡት መኖራቸውን የታሪክ አጥኚዎች አመልክተዋል።
ለዚህም ምክንያቱ በኤፕሪል 1 ፈረንሳይ ውስጥ በሚገኙ ምንጮች እና ወንዞች ውስጥ ከሌላው ጊዜ በተለየ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዓሳዎች ስለሚገኙ፣ መረቡን የዘረጋ ሁሉ በርከት ያሉ ‘ሞኝ ዓሳዎችን’ መያዝ ስለሚችል ነው ይላሉ።
ከዚያ በኋላም በዚያ ዕለት ሰዎችን የማሞኘት እና የማታለል ልማድ እየተስፋፋ የኤፕሪል የመጀመሪያ ዕለት ከዚሁ ጋር ተቆራኝቶ አሁን ድረስ ዘልቋል።
ከዚሁ የዓሳ ታሪክ ጋር ተያያዘም ሰዎችን ለማሞኘት ከወረቀት የተሠራ የዓሳ ሥዕል በሰዎች ጀርባ ላይ ሳያውቁ በመለጠፍ መሳቂያ ማድረግ በዕለቱ ከሚያጋጥሙ ነገሮች መካከል ይጠቀሳል።
እንዲሁም በዓሳ ቅርጽ የተሰሩ ቼኮሌቶችን በዕለቱ ለወዳጅ ለጓደኛ መስጠትም የተለመደ ነበር ይላሉ የታሪክ አጥኚዋ አንድሪያ ስለኤፕሪል ዘ ፊሽ ዴይ ሲያስረዱ።

ታሪኩ በትክክል የማይታወቀው ዕለት
አሁን በመላው ዓለም የተለያየ የዘመን አቆጣጠር በሚጠቀሙ አገራት ጭምር ሳይቀር የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ቀን በተለያዩ የማሞኛ ድርጊቶች ይታወሳል።
ነገር ግን አሁንም ከተጠቀሱት እና ከሌሎችም መላምቶች ውጪ የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ቀን እንዴት እና የት ተጀመረ የሚለውን ታሪክ በተመለከተ በትክክል ሁሉም የሚታወቅ መረጃ የለም።
ቢሆንም ግን በአንድ ነገር እርግጠኛ መሆን የሚቻለው በተለያዩ አገራት ውስጥ ያሉ ሰዎች በዕለቱ የቀልድ እና የማሞኘት ድርጊትን እየፈጸሙ ዘመናት መቆጠራቸውን ነው።
ስለዚህ በኢትዮጵያም በወጣቶች ዘንድ ይኽው የ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ ቀን የማሞኛ ድርጊቶች ጨዋታ እና ሳቅ ከሚፈጥሩ ነገሮች ባሻገር አሳዛኝ እና አስደንጋጭ ነገሮችን ጨምረው ሲከሰቱ ተስተውሏል።
ስለዚህም ዛሬ ያ ‘ኤፕሪል ዘ ፉልስ’ የተሰኘው የማሞኛ ቀን በመሆኑ ጠንቀቅ እንድትሉ ለማስታወስ እንወዳለን።
አነጋጋሪው የቢቢሲ ዘገባ
በመላው ዓለም በኤፕሪል 1 ቀን ሰዎችን ለማሞኘት ከተነገሩ ሐሰተኛ ዘገባዎች መካከል ቢቢሲ እአአ 1957 ላይ የፓስታ እጥረትን በተመለከተ የሠራው ዘገባ ይጠቀሳል።
በጊዜው በከባድ የክረምት ምክንያት የፓስታ እጥረት አጋጥሞ ነበር። ታዲያ ይህ ዘገባ የስዊትዘርላንድ ገበሬዎች የፓስታ እጥረቱን የሚቀርፍ ምርት ለገበያ እያቀረቡ የሚል ነበረ።
ፓኖራማ በዚህ የቴሌቪዥን ዘገባው፤ ገበሬዎች ከዛፍ ላይ ፓስታ ሲሰበስቡ የሚያሳይ ምስል አሳየ።
በርካታ ተመልካቾችም ይህ ዘገባ እውነት መስሏቸው ነበር። ብዙዎች ውደ ቢቢሲ ስቱዲዮ በመደወል ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? እያሉ ሲጠይቁ ነበር።