የሃቫና ሲንድረም ምልክት ቀድሞ የታየው ሃቫና በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ነው።
የምስሉ መግለጫ,የሃቫና ሲንድረም ምልክት ቀድሞ የታየው በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ነው

1 ሚያዚያ 2024, 13:35 EAT

አሜሪካውያን የደኅንነት ሠራተኞችን ዒላማ የሚያደርግ ነው ከተባለው እና ‘ሃቫና ሲንድረም’ ተብሎ ከሚጠረው ህመም ጀርባ ሩሲያ ስለመኖሯ አንድ ሪፖርት አመለከተ።

ይህ ለዓመታት ምንነቱ ሳይታወቅ የቆየው ህመም የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን፣ የኤፍቢአይ እና ሲአይኤ ባልደረቦችን ሲያጠቃ ቆይቷል።

ትኩረቱን ሩሲያ ላይ አድርጎ የሚሠራው ዘ ኢንሳይደር የተባለ የዜና ድረ-ገጽ፣ ዴር ስፒግል የተባለ የጀርመን ጋዜጣ እና 60 ሚነትስ የተባለ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በጥምረት የሠሩት ሪፖርት፤ ሃቫና ሲንድረም ከሩሲያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ጋር እንደሚገናኝ አሳይተዋል።

ሞስኮ ከሃቫና ሲንድረም ጋር የሚያገናኘኝ ነገር የለም በማለት ስታስተባብል ቆይታለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደግሞ ለሃቫና ሲንድረም የውጭ ኃይሎችን ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል ምንም ማስረጃ የለንም ቢሉም፤ ዲፕሎማቶችን እና የደኅንነት ሰዎችን ለይቶ ስለሚያጠቃው ምሥጢራዊ በሽታ ምንነት ማብራሪያ ማቅረብ ግን አልቻሉም።

ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ሃቫና ሲንድረምን በተመለከተ ምርመራ ያደረጉ የተለያዩ የአሜሪካ ተቋማት የተለያየ የግምገማ ውጤት ላይ መድረሳቸውን አልካዱም።

ይህ ምንነቱ ያልታወቀ ህመም መጠሪያውን ያገኘው ምልክቱ እአአ 2016 ላይ ቀድሞ ከታየባት የኩባዋ ዋና ከተማ ሃቫና ነው።

በሃቫና ሲንድረም የተጠቁ የዋይት ሐውስ፣ የሲአይኤ እና የኤፍቢአይ ባልደረቦች መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ ትኩረት ማድረግ አለመቻል እና በጆሮዎቻቸው ውስጥ የማያቋርጥ ህመም ያለው ከፍተኛ ድምጽ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል።

እነዚህ ሰዎች ከተደበቀ መሳሪያ በማይክሮዌቭ አልያም ደግሞ የኬሚካል ወይም ኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ወደ ጨረር ኃይል በመቀየር ዒላማውን በሚመታ ኤሌክትሮማግኔቲክ ሥርዓት ዒላማ ሳይደረጉ እንዳልቀረ ጥርጣሬ ነበር።

አሁን ይፋ የሆነው ሪፖርት ሃቫና ሲንድረምን 29155 ከተባለ በሩሲያ ወታደራዊ ደኅንነት ውስጥ ካለ ቡድን ጋር አያይዞታል።

ሪፖርቱ 29155 የተባለው የሩሲያ ቡድን የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አእምሮን ዒላማ እያደረገ ነው ብሏል።

የሚዲያ ተቋማቱ ያካሄዱት ጥናት የአሜሪካ ዜጎች ህመሙ አጋጥሞናል ባሉባቸው ከተሞች የዚህ ቡድን አባላት በእነዚያ ከተሞች ነበሩ ይላል።

ሩሲያ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ዘ ኢንሳይደር 29155 ቡድን አባላት “ገዳይ ያልሆነ ድምጽ አልባ መሳሪያ” በማበልጸግ ሽልማት ተቀብለዋል ብሏል።

አሜሪካዊው የወታደራዊ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ግሬድ ኤድግሪን ለ’60 ሚነትስ’ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲናገሩ፣ በሃቫና ሲንድረም የሚጠቁ ሰዎች ያላቸው አንድ ተመሳሳይ ነገር “ከሩሲያ ጋር ያላቸው ትስስር ነው” ብለዋል።

ኤድግሪን ሐሳባቸውን ሲያስረዱ በዚህ በሽታ ዒላማ የተደረጉት በሙሉ “በሩሲያ ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ሠርተዋል አልያም ከሩሲያ ፍላጎት በተቃራኒ ተንቀሳቅሰዋል” ይላሉ።

እኒህ የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ እንደሚሉት የአሜሪካ ባለሥልጣናት “እውነታውን መጋፈጥ” ስላልፈለጉ በጉዳዩ ላይ የሩሲያን ተሳትፎ በግልጽ የሚያሳይ ማስረጃ ካልቀረበላቸው በቀር እርምጃ ለመውሰድ ማመንታት እያሳዩ ነው።

በቫሃና ሲንድረም ከተጠቁ የኤፍቢአይ ባልደረቦች መካከል አንዷ ፍሎሪዳ በሚገኘው መኖሪያ ቤቷ እአአ 2021 እንዴት ጥቃቱ እንደደረሰባት ለ60 ሚነትስ ተናግራለች።

“ቀኝ ጆሮዬ ውስጥ ደንገት በኃይል ጮኽብኝ፤ በስለት የተወጋው መሰለኝ። ለጆሮዬ ታንቡር የቀረበ ኃይለኛ ህመም ነበር” ትላለች ይህች ኬሪ የተባለችው የኤፍቢአይ ባልደረባ።

ኬሪ ከጥቃቱ በኋላ ራሷን ስታ መውደቋን ትገልጻለች። ከዚያ በኋላ ሥራዋን በአግባቡ መከወን እንዳትችል ተጽእኖ ያሳደረባት ትኩረት ማጣት እና የማስታወስ ችግር እንደገጠማት ታስረዳለች።

መገናኛ ብዙኃኑ ያወጡትን ሪፖርት ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት ሃቫና ሲንድረምን በተመለከተ የምናደርገውን ምርመራ እንቀጥላለን ከማለት ውጪ ተጨማሪ ነገር አላሉም።

ሩሲያ የሪፖርቱን መውጣት ተከትሎ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።