የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የፑንትላንድ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሳይድ አብዱላሂ ዴኒ
የምስሉ መግለጫ,የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የፑንትላንድ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሳይድ አብዱላሂ ዴኒ

1 ሚያዚያ 2024, 12:15 EAT

ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የሶማሊያዋ ግዛት ፑንትላንድ ሞቃዲሾ ለሚገኘው ለሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ትሰጥ የነበረውን እውቅና ማንሳቷ ይታወሳል።

ፑንትላንድ መንግሥት ካቢኔ ቅዳሜ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ላይ መተማመን የለኝም፤ ለአገሪቱ መንግሥት ትሰጥ የነበረውን ዕውቅና ማንሳቱን አስታውቋል።

ይህ የፑንትላንድ አስተዳደር ውሳኔ የተሰማው የሶማሊያ መንግሥት ፓርላማ ብዙ ባወዛገበ ሂደት በአገሪቱ ሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ቅዳሜ ዕለት ይሁንታ መስጠቱን ተከትሎ ነው።

ቅዳሜ መጋቢት 21 የሶማሊያ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የማሰናበትን ሥልጣን የሚሰጠውን ጨምሮ ሌሎችም ማሻሻያዎች በሕገ መንግሥቱ ላይ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፈዋል።

ይህ ለበርካታ ሳምንታት ብዙ ሲያነታርክ የቆየው የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ጊዜ ተወስዶ ሰፊ ውይይት እንዲደረግበት የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጥሪ ሲያቀርቡ ነበር።

ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተደረገው ማሻሻያ ምንድነው?

የሶማሊያ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት አባላት በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመጀመሪያዎቹ አራት ምዕራፎች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ወስነዋል።

ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀጾች ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የሴቶች ተሳትፎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት፣ የአስተዳደር ሥርዓት እና ከምርጫ እና ከድንበር ኮሚሽን አወቃቀር ጋር የተያያዙ ናቸው።

የብዙ ንትርክ ምንጭ የሆነው ግን የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት እና ከሥልጣን ማንሳትን የሚመለከተው በአስተዳደር ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ ነው።

ማሻሻያ የተደረገበት የሶማሊያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49.1 በቀጥታ ምርጫ ለሚመረጡት ፕሬዝዳንት የአገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትር መሾም እና መሻር እንዲችሉ የሚያደርግ ሥልጣን ይሰጣል።

ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም እንጂ ማንሳት አይችሉም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትርን ከሥልጣን ማንሳት የሚችለው ፓርላማው ነበር።

የተሻሻለው ሕገ መንግሥት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ቁጥር ከሦስት እንዳይበልጥ ገድቧል።

የሶማሊያ እና ፑንትላንድ የፖለቲካ ልዩነት ምንጭ

በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ውስጥ ከሚገኙ ዋነኛ ከሚባሉ ግዛቶች መካከል አንዷ የሆነችው ፑንትላንድ በአገሪቱ አጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ ጉል ሚና አላት።

በእስላማዊው የአል ሻባብ ጥቃት በምትናጠው ሶማሊያ ውስጥ ፑንትላንድ በአንጻራዊነት ዝቅተኛ የቡድኑ ጥቃት የሚፈጸምባት ግዛት ናት።

የሲያድ ባሬ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የጎሳ የጦር አበጋዞች በሶማሊያ ግዛቶች ውስጥ የበላይነት ይዘው ጦርነት ሲካሄድ ቆይቶ አገሪቱን ወደ ተረጋጋ ሥርዓት ይመልሳታል ተብሎ የታሰበው የሽግግር መንግሥት ሲቋቋም ፑንትላንድ ጉልህ ሚና ነበራት።

የፖለቲካዊ ሥርዓቷ በዋናነት በጎሳዎች አማካይነት በሚዘወርባት ሶማሊያ፤ የማዕከላዊ መንግሥቱን መልሶ ለማወቀር ጥረት በሚደረግበት ጊዜ ዋነኞቹ ጎሳዎች ሠፊ ሚና እንዲኖራቸው በማሰብ በሂደቱ ላይ ተጽእኖ ሲያሳድሩ ነበር። ለዚህም በፑንትላንድ የሚገኙት ፖለቲከኞች ይጠቀሳሉ።

በአውሮፓውያኑ 1998 በሶማሊያ የፑንትላንድ አስተዳደር በሚል በይፋ የተመሠረተችው ግዛት በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ የምትገኝ የፌደራሉ መንግሥት አካል ሆናለች።

መቀመጫቸውን በዋና ከተማዋን ጋሮዌ ላይ ያደረጉት የግዛቲቱ አስተዳዳሪያዎች በዚያው ዓመት የፌደራሉ መንግሥት አካል ሆና ራስ ገዝ መሆኗንም አውጀዋል።

ፑንትላንድ በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ

በሲያድ ባሬ የሥልጣን ዘመን አንስቶ የጉልህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ መነሻ እንደሆነች የሚነገርላት የፑንትላንድ ግዛት፣ በውጪ መንግሥታት የሚደገፍ ፀረ ሲያድ ባሬ የትጥቅ እንቅስቃሴ የተነሳው ከዚያ ነበር።

የግዛቲቱ ፖለቲከኞች በአገሪቱ ለውጥ እንዲመጣ በተለያዩ መንገዶች እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁ ሲሆን፣ የሲያድ ባሬ አስተዳደር ከወደቀ በኋላም በሶማሊያ የተረጋጋ መንግሥት እንዲቋቋም በሚደረገው ሂደት ውስጥ ወሳንኝ ሚና ነበራቸው።

ፖለቲከኞቹ የፑንትላንድ ግዛትን ከመቆጣጠር ባሻገር በማዕከላዊው የሶማሊያ መንግሥ ውስጥም ተጽእኗቸው የሚታይ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉትም ፑንትላንድ የሶማሊያ “ፌደራል መንግሥት እናት” በማለት የሚናቸውን መጠን ይገልጹታል።

በዚህም ማዕከላዊው መንግሥት በሚፈጽማቸው እያንዳንዱ ተግባራት እና በሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች ላይ የፑንትላንድ ፖለቲከኞች እጅ በእጅጉ አስፈላጊ ሆኖ ቆይቷል።

የፑንትላንድ መሪዎች የማያውቋቸው ወይም ያልደገፏቸው ውሳኔዎች ተቀባይነታቸው ደካማ ከመሆኑ በሻገር ከባድ ተቃውሞን በመንግሥት ላይ የሚያስከትሉ ናቸው።

በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ የሚደረጉ ሹመቶች እና ምርጫዎች በአብዛኛው ከፑንትላንድ በኩል በሚሰጥ ድጋፍ የሚቀርቡ ወይም ከእነሱ ጋር በሚደረግ ምክክር የሚፈጸሙ ናቸው። ስለዚህም የፑንትላንድ መሪዎችን ድጋፍ እና ይሁንታን ያላገኘ የፌደራል መንግሥቱ ሹመት መደምደሚያው ምን እንደሚሆን የታወቀ ነው።

አሁን በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ምክንያት ከፑንትላንድ መሪዎች ጋር ሳይግባቡ የቀሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን የመጡት በፑንትላንዶች ድጋፍ እንደሆነ ይነገራል። የቀደሙት ፕሬዝዳንትም በምርጫው ለሽንፈት የተዳረጉት የግዛቲቱ መሪዎች ፊታቸውን ስላዞሩባቸው እንደሆነ ይገለጻል።

ፑንትላንድ ካርታ

የሥልጣን ፉክክር

ፑንትላንድ በአሁኑ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ሂደት ድጋፍ ያልሰጠችው ውሳኔ በፕሬዝዳንቱ እና በአገሪቱ ምክር ቤቶች ጸድቋል።

ይህ ደግሞ ፑንትላንድ በሶማሊያ ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ተጽእኖ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እና ለወደፊቱም ያላትን ሚና የሚያሳንስ ሊሆን ይችላል በሚል በይፋ ማሻሻየውን ተቃውማዋለች። ከዚያም አልፋ ለፌደራሉ መንግሥት ያላትን ዕውቅና በማንሳት ነጻነትን የማወጅ ያህል ከውጭ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በቀጥታ ለማካሄድ ወስናለች።

በፑንትላንድ እና በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት መካከል እንዲ ያለ አለመግባባት ከዚህ በፊት ያጋጠመ ሲሆን፣ እንዳሁኑ ግን ጠንካራ እና የፌደራሉን መንግሥት ዕውቅና የሚነፍግ አልነበረም።

ቢቢሲ ሶማሊኛ እንደሚለው የፑንትላንድ መሪዎች ደግፈው ወደ ሥልጣን ባመጧቸው ሼክ ሐሰን ሞሐሙድ እና በግዛቲቱ ፖለቲከኞች መካከል ያለው የሥልጣን ፉክክር በሕገ መንግሥት ማሻሻል ሂደቱ ምክንያት ይፋ ወጥቷል።

ምንም እንኳን የፑንትላንድ መሪዎች በሕገ መንግሥት ማሻሻሉ ላይ በይፋ ያነሱት ጥያቄም ሆነ ተቃውሞ ባይኖርም የፌደራሉን መንግሥት ዕውቅና አስከ መንፈግ የሚደርስ ከባድ ውሳኔ አሳልፈዋል። ይህም ከሶማሊላንድ ቀጥሎ በማዕከላዊው መንግሥት ላይ ያመጸ ተጨማሪ ግዛት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም ሌሎች የፌደራሉ መንግሥት አካል የሆኑ ግዛቶች ውሳኔውን ተቃውመው ከጎኗ እንዲቆሙ እየጠየቀች በመሆኗ ሌላ ዙር ፖለቲካዊ ውጥረት በአገሪቱ ውስጥ እንዳይከሰት አስግቷል።

የፖለቲከኞች አለመግባባት

የፑንትላንድ መሪ ባለፈው ዓመት በተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በፌደራሉ መንግሥት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖራቸው በማሰብ ፕሬዝዳንት ወይም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ አጥብቀው ፈልገውት ነበር።

ገር ግን በዝግ በተደረጉ ፖለቲካዊ ድርድሮች አማካይነት ለሐሰን ሼክ ሞሐመድ ድጋፍ ሰጥተዋል።

በዚህ ንግግርም ሁለተኛውን ዋነኛ ሥልጣን በፑንትላንድ መሪዎች የሚጠቆም ሰው እንዲይዝ ቢፈልጉም፣ ፕሬዝዳንቱ በራሳቸው ውሳኔ ከፑንትላንድ ጎሳዎች መካከል አንዱን በመሰየም ምላሽ ቢሰጡም ፖለቲከኞቹ ደስተኛ አልሆኑም። ቅራኔው የሚጀምረውም ከዚህ ነው።

የፑንትላንድ መሪዎች የሚፈልጉት ወይም ተመካክረው የተስማሙበት ባለመሆኑ እንዲመረጡ ካደረጓቸው ፕሬዝዳንት ላይ ፊታቸውን እያዞሩ ነው። የሐሰን ሼክ መንግሥትንም ለማዳከም ከቀድሞዎቹ ፕሬዝዳንቶች ጋር ግንባር ለመፍጠር የወሰኑ ይመስላሉ። ለዚህም ፕሬዝዳንቶቹ ባለፈው ሳምንት ለምክክር ጋሮዌ መገኘታቸው ተዘግቧል።

በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ላይ ወሳኝ ሚና ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ቦታ በፕሬዝዳንቱ ቁጥጥር ስር መግባቱ ፑንትላንዶችን አላስደሰተም።

ከዚህ ቀደም የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰናበተው በምክር ቤቱ የነበረ ቢሆንም በተሻሻለው ሕገ-መንግሥት ግን ኃላፊነቱ ወደ ፕሬዝዳንቱ ዞሯል።

ምንም እንኳን ለማዕከላዊው መንግሥት የሰጡትን ዕውቅና ቢያነሱም፣ የፑንትላንድ መሪዎች ጥቅም እና ፍላጎታቸውን የሚያስከብር ስምምነት ላይ መድረስ ከቻሉ ውሳኔያቸውን ይቀለብሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በፊት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የተፈጠሩ በርካታ አለመግባባቶች በድርድር እንደተፈቱት ሁሉ አሁንም ይህ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ፑንትላንድ በሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ውስጥ ፍላጎቷን እና ተጽእኖዋን ማስከበር ትችላለች የሚል ግምት አለ።

ከሶማሊያ መለየት ለፑንትላንድ ምን ማለት ሊሆን ይችላል?

ምንም እንኳ ፑንትላንድ ለፌደራል መንግሥቱ እውቅና በመንሳት የውጭ ጉዳዮችን በራሴ እከወናለሁ ማለቷ ነጻ አገርነትን እንደ ማዋጅ ቢታይም፣ ፑንትላንድ እስካሁን ‘ነጻ አገር’ ነኝ በማለት በይፋ አላወጀችም።

ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ ልክ እንደ ሶማሊላንድ ሁሉ ነጻ አገርነቷን ብታውጅ በተለይ ከገቢ ጋር በተያያዘ ምጣኔ ሃብቷን የምትገድፍበት ገንዘብ ሊያጥራት ይችላል።

ሶማሊያ ወጪዋን ለመሸፈን በውጭ እርዳታ ላይ ጥገኛ ብትሆንም፣ ለፌደራል ግዛቶቿ የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች።

ሞቃዲሹ በእርዳታ እና በብድር ከውጪ የምታገኘውን ገንዘብ ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ አባል ለሆኑ ክልሎች የማከፋፈል ግዴታ አለባት።

ምንም እንኳ የፑንትላንድ መሪዎች ከእርዳታ እና ብድር ከሚገኘው ገንዘብ የሚገባንን እያገኘን አይደለም በሚል በተደጋጋሚ ቅሬታ ቢያቀርቡም፤ ከሶማሊያ ለመገንጠል የሚወስኑ ከሆነ አነስተኛም ቢሆን ያገኙት የነበረው ገቢ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል።

በሶማሊያ እና ፑንትላንድ መካከል ሊፈጠር የሚችል መቃቀር በጽንፈኛው ቡድን አል ሸባብ ላይ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ ሊያዳክም ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሯል።

የወቅቱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው መካከል አንዱ አል ሸባብን መዋጋት መሆኑን ገልጸው ነበር።

ይህን ለመፈጸምም በበርካታ የአገሪቱ ክፍል ወታደራዊ ዘመቻዎች እየተናወኑ ነው። የሶማሊያ እና ፑንትላንድ ፖለቲካዊ ልዩነት ታዲያ ይህን ወታደራዊ ዘመቻ ሊያዳክም እንደሚችል ይገመታል።