አል-ሺፋ ሆስፒታል
የምስሉ መግለጫ,አል-ሺፋ ሆስፒታል

1 ሚያዚያ 2024, 15:17 EAT

የእስራኤል ጦር ኃይል ለሁለት ሳምንታት ያህል በጋዛው አል-ሺፋ ሆስፒታል ላይ ወረራ ካካሄደ በኋላ አብዛኛውን የህክምና ተቋሙን ክፍል ለቆ መውጣቱ ተገለጸ።

በሆስፒታሉ ላይ ከተካሄደው ወረራ እና ጥቃት በኋላ የጋዛው ሆስፒታል ሕንፃ አፅሙ ቀርቶ ታይቷል።

የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት እንደገለጸው ወታደሮቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ “ሽብርተኞችን” ገድለዋል እንዲሁም በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

ሠራዊቱ “በሆስፒታሉ ዙሪያ” የጦር መሣሪያዎች እና የደኅንነት መረጃዎች ማግኘቱን ገልጧል።

በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በርካታ ሬሳዎችን ጥሎ ለመሄድ መገገዱን አሳውቋል። የአካባቢው ሰዎች ደግሞ ሥፍራው መውደሙን ይናገራሉ።

የእስራኤል ጦር፤ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ላይ ወረራ እና ጥቃት የፈጸመው ሐማስ መልሶ ስለተደራጀበት መሆኑን ይገልጣል።

በእስራኤል አየር ድብደባው ምክንያት በሆስፒታሉ ዙሪያ ያሉ ሕንፃዎችንም ጭምር ያጠቃ ነበር። የእስራኤል ጦር የሆስፒታሉን የሕክምና ክፍሎች ያወደምኩት ሐማስ እና የፍልስጤም ኢስላሚክ ጂሀድ ስለሚጠቀሙበት ነው የሚል መግለጫ አውጥቷል።

የእስራኤል ጦር ሥፍራውን ለቆ ከወጣ በኋላ የተለቀቁ ፎቶዎች እንደሚያሳዩት የሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ክፍል እና ሌሎች ሕንፃዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

መግለጫው ግን የእስራኤል ወታደሮች “በአል-ሺፋ ሆስፒታል እና በአካባቢው ለይቶ የማጥቃት እርምጃ ወስደዋል” ይላል።

አክሎም “የእስራኤል ጦር ሰላማዊ ዜጎችን፣ ታካሚዎችን እና ሕክምና ሰጪዎችን ከማጥቃት ተቆጥቧል” ይላል መግለጫው።

እሑድ ጥዋት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አል-ሺፋ “የሽብርተኞች መሸሸጊያ” ሆኗል ካሉ በኋላ፣ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ200 በላይ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን አባላት መገደላቸውን ተናግረዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴደሮስ አድሃኖም፤ አል-ሺፋ “ጥቃት ከተከፈተበት በኋላ” 20 ታካሚዎች መሞታቸውን አሳውቀዋል።

ኃላፊው አክለውም ከ100 በላይ ታካሚዎች “በቂ ቁሳቁስ በሌለው ሆስፒታል ውስጥ” በቂ ሕክምና ሳያገኙ ለቀናት ቆይተዋል ብለዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ጦር ሠራዊት አባላት ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር የጋዛ ሰርጥ ትልቁ ሆስፒታልን የወረሩት።

የእስራኤል ጦር ባለፈው ኅዳር ብዛት ያላቸው ታንኮች አስከትሎ በአየር ኃይሉ ታግዞ ወደ አል-ሺፋ ሆስፒታል አምርቶ ነበር።

የጦር ኃይሉ ቃል አቀባይ እርምጃውን “በጣም ውጤታማ” ሲሉ ገልጸው የተገኘውን የደኅንነት ድል አወድሰዋል።

በእስራኤል-ሐማስ ጦርነት ሆስፒታሎች የጥቃት ዒላማ ሲሆኑ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን የእስራኤልን የአየር ድብደባ ሸሽተው የሚደበቁባቸው ሆስፒታሎች ብዙ ጊዜ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ምንም እንኳ በርካታ ሰላማዊ ዜጎች ሆስፒታሎች ውስጥ ቢደበቁም የእስራኤል ጦር ሐማስ ተደብቆባቸዋል በሚል ጥቃት ያደርሳል።

እስራኤል በተደጋጋሚ ሐማስ ሰላማዊ ዜጎች የሚጠቀሙበትን ሆስፒታል መሸሸጊያው ያደርጋል ስትል ብትወቅስም የፍልስጤም ተቆርቋሪዎች ግን ይህ ሐሰት ነው ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እሑድ ዕለት ለቀዶ ህክምና ወደ ሆስፒታል ከመግባታቸው በፊት ነው ስለአየር ጥቃቱ የተናገሩት።

በተያያዘ ዜና እሑድ ዕለት አንድ ለቢቢሲ ‘ፍሪላንስ’ ሆኖ የሚያገለግል ጋዜጠኛን ጨምሮ ሰባት የመገናኛ ብዙኃን ሙያተኞች በአስራኤል ጥቃት ጉዳት ደርሶባቸዋል።