April 1, 2024 – Konjit Sitotaw
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ከአገር ዓቀፍና ከክልላዊ ፓርቲዎች ጋር መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
የውይይቱ ዓላማ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ላይ አስተያየቶችና ትችቶችን ማሰባሰብና ለፖሊሲ ግብዓት አስፈላጊ የኾኑ እርማቶችንና ማስተካከያዎችን መለየት እንደነበር ዐቢይ ገልጸዋል።
በውይይቱ እንዲገኙ ጥሪ ከቀርበላቸው 60 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲዎች ኮከስ አባላት የኾኑ 13ት ፓርቲዎች ጥሪውን እንዳልተቀበሉ መስማቱን ሸገር ዘግቧል።
የኮከሱ አባል የኾነው የኅብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ግርማ በቀለ፣ ፓርቲዎቹ በውይይቱ የማይሳተፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ካኹን ቀደም ከነጋዴዎች፣ ከኃይማኖት ተቋማትና ሌሎች አካላት ጋር ያደረጓቸው ተመሳሳይ ውይይቶች የገጽታ ግንባታን ዒላማ ያደረጉ እና የገዥው ብልጽግና ፓርቲ መወድስ የሚቀርብባቸው መኾናቸውን በመረዳታቸው እንደኾነ ለሸገር ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች፣ ነገ ማክሰኞ የኔዘርላንድ መንግሥት ባዘጋጀላቸው ሥልጠና ላይ እንደሚገኙ መስማቱን ዘገባው አመልክቷል።