April 1, 2024 – Konjit Sitotaw 

በአማራ ክልል ባንዳንድ አካባቢዎች በመንግሥት ወታደሮች እና በፋኖ ሚሊሺያዎች መካከል ግጭቶች ቀጥለዋል።

በተለይ በጎንደር ከተማ ባንዳንድ ክፍለ ከተሞች እንዲኹም በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በደሃና ወረዳ በርካታ አካባቢዎች በኹለቱ ወገኖች መካከል ውጊያ መካሄዱን ዋዜማ ከምንጮች ተረድታለች።

ሰሞኑን በምሥራቅ ጎጃም ዞን በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረው ውጥረት ሳቢያ፣ ባሕርዳር እና ደብረማርቆስ ከተሞችን የሚያገናኘው ዋናው መንገድ እንደተዘጋና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም እንደተገደበ ዋዜማ ሰምታለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙት አቶ አደም ፋራህ የፓርቲ ስልጣናቸውን ይዘው ይቆያሉ ተባለ

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ካሉት ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። ለአቶ አደም ዛሬ ሰኞ መጋቢት 23፤ 2016 ሹመቱን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሆናቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት፤ በመጋቢት 2014 በተካሄደው የፓርቲው አንደኛ ጠቅላላላ ጉባኤ ላይ ነው። በወቅቱ የገዢው ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ከተጠቆሙት ሶስት አባላት ውስጥ አቶ አደም 1,330 ድምጽ በማግኘት በከፍተኛ ድምጽ መመረጣቸው ይታወሳል።

በዚያ ጉባኤ ከተሳተፉ 1,564 አባላት መካከል የ970ዎቹን ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት፤ ባለፈው ጥር ወር ከፓርቲው ኃላፊነታቸው የተሰናበቱት አቶ ደመቀ መኮንን ነበሩ። በመጋቢት 2014ቱ ስብሰባ ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አቶ ደመቀን በመተካት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል።