
ከ 6 ሰአት በፊት
ታዋቂው የ63 ዓመቱ ባሕላዊ የሐይማኖት አባት የ12 ዓመት ታዳጊ ማግባታቸው በጋና ትልቅ ቁጣ ቀስቅሷል።
ኑሞ ቦርኬቴ ላዌህ ትሱሩ 33ኛ ቅዳሜ ዕለት በተካሄደ የሠርግ ሥነ-ሥርዓት ነው ታዳጊዋን ያገቡት።
ምንም እንኳ በርካታ ትችት እየዘነበ ቢሆንም የማሕበረሰብ መሪዎች፤ ሰዎች ባሕል እና ወጋችን አይገባቸውም የሚል ምላሽ እየሰጡ ነው።
በጋና ከ18 ዓመት በታች ጋብቻ መፈፀም ሕጋዊ አይደለም። ምንም እንኳ በሀገሪቱ ያለዕድሜ ጋብቻ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም በአንዳንድ ሥፍራዎች ይህ ሲከናወን ይታያል።
‘ገርልስ ኖት ብራይድስ’ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት እንደሚለው በጋና 19 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች 18 ሳይሞላቸው ነው ትዳር የሚመሠርቱት።
5 በመቶ ደግሞ ገና 15 ዓመት ሳይሆናቸው ይዳራሉ።
ቅዳሜ ዕለት የነበረውን ፕሮግራም የሚያሳዩ ቪድዮዎች እና ፎቶዎች እንደሚጠቁሙት በርካታ የማሕበረሰብ መሪዎች ታድመዋል።
ቪድዮዎች እና ፎቶዎች ማሕበራዊ ሚድያዎች ላይ በስፋት መሰራጨታቸውን ተከትሎ ጋናዊያን ቁጣቸውን እያሰሙ ነው።
በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት አንዲት ጋ በተሰኘው ቋንቋ ንግግር ያሰሙ ሴት፤ ታዳጊዋ ባሏን በሚማርክ መልኩ እንድትለብስ ሲመክሩ ይደመጣሉ።
አክለው የሚስት ተግባራትን ለመከወን እንድትዘጋጅ እና በስጦታ የተሰጣትን ሽቶ ተቀብታ ለባሏ ወሲብ ቀስቃሽ ሆና እንድትገኝ ሲናገሩ ይደመጣሉ።
- ፍሪጅ አል መረር፡ የኢትዮጵያውያን “ቡና ቤቶች” በዱባይከ 7 ሰአት በፊት
- የሶማሊያ እና ፑንትላንድ ፖለቲካዊ እሰጣ ገባ መነሻው ምንድን ነው?1 ሚያዚያ 2024
- አሜሪካውያን የደኅንነት ሠራተኞችን ዒላማ ከሚያደርገው ‘ሃቫና ሲንድረም’ ጀርባ ሩሲያ አለች ተባለ1 ሚያዚያ 2024
ይህ ንግግር በጋናዊያን ዘንድ ያለውን ቁጣ እጅግ ያጋለው ሲሆን ጋብቻው እንዲሁ ለወግ ብቻ የተዘጋጀ አይደለም ማለት ነው የሚል ሐሳብ ጭሯል።
ብዙዎች መንግሥት ጋብቻውን እንዲያፈርስ እና ትሱሩን የተባሉትን የሐይማኖት አባት እንዲመረምር ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
ታዳጊዋ እና የሐይማኖት አባቱ አባል የሆኑበት ኑንጋ የተባለው ጥንታዊ ብሔረሰብ መሪዎች ከተቀረው የጋና ክፍል የቀረበባቸውን ትችት አስተባብለው ትችቱ “ካለማወቅ የመነጨ ነው” ብለዋል።
ኒ ቦርቴ ኮፊ ፍራንክዋ 2ተኛ የተባሉ አንድ የማሕበረሰብ መሪ እሑድ ዕለት ታዳጊዋ የሐይማኖት አባቱ ሚስት ሆና የምትጫወተው ሚና “ባሕላዊ እና ወጋዊ ብቻ ነው” ብለዋል።
አክለው ታዳጊዋ የሐይማኖት አባቱ ሚስት ለመሆን የታጨችው ከ6 ዓመት በፊት መሆኑን ተናግረው ነገር ግን ይህ ከትምህርቷ እንዳላገዳት ይናገራሉ።
ታዳጊዋ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄድ ሥነ-ሥርዓት የሐይማኖት አባቱ ሚስት ለመሆን የሚያስችላት ንፅሕና እንዳላት ይረጋገጣል። ይህ ሥነ-ሥርዓት ልጅ ወልዶ ማሳደግን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን የምትለማመድበትን ነው ሲሉ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ትሱሩ በጥንታዊው የኑንጋ ብሔረሰብ “ግቦርቡ ዉሎሞ” የተሰኘ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሐይማኖት አባት ሲሆኑ ነዋሪነታቸው በዋና ከተማዋ አክራ ነው።
ብሔረሰቡን ወክለው መስዋዕት ይፈፅማሉ፤ ይፀልያሉ፤ ባሕላዊ ልማዶች እንዲፈፀሙ ያደርጋሉ።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለአከራካሪው ጋብቻ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
ምንም እንኳ የጋና ሕግ ባሕላዊ ጋብቻዎችን ቢፈቅድም በባሕል ስም የሚደረጉ ከዕድሜ በታች የሚፈፀሙ ጋብቻዎችን አይፈቅድም።