ጋዜጠኛ ልጁ የተገደለበት የአል ጀዚራው ጋዜጠኛ ዋኤል አል-ዳህዱህ

ከ 6 ሰአት በፊት

የእስራኤል መንግሥት አል ጀዚራን ጨምሮ ሌሎች የቴሌቭዥን ጣብያዎችን ማገድ የሚያስችለውን ስልጣን ከአገሪቱ ፓርላማ አግኝቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በአገሪቱ የሚገኘውን የቴሌቭዥን ጣብያውን ቢሮ “በፍጥነት” እንደሚዘጉ ገልጸዋል።

አሜሪካ በበኩሏ በጉዳዩ ዙሪያ ያላትን ስጋት ገልጻለች።

የውጭ ዘጋቢዎች ወደ ጋዛ እንዳይገቡ መከልከሉን ተከትሎ በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የተወሰኑ አል ጀዚራ ጋዜጠኞች በአካባቢው የሚካሄደውን ጦርነት በመዘገብ ለዓለም እያሳወወቁ ይገኛሉ።

ክኔሴት (የእስራኤል ፓርላማ) ለአገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ስጋት ናቸው የተባሉ መገናኛ ብዙሃን “በጊዜያዊነት” እንዲታገዱ የሚፈቅደውን መመሪያ አጽድቋል።

እገዳው በአንድ ጊዜ ለ45 ቀናት የሚዘልቅ ሲሆን ቀነ ገደቡ ሲጠናቀቅም ለተጨማሪ ጊዜ የሚራዘም ይሆናል።

“አል ጀዚራ ከዚህ በኋላ ከእስራኤል ምድር አይዘግብም” ሲሉ ኔታንያሁ ኤክስ ላይ አስፍረዋል።

ተቋሙንም “የሽብር ጣብያ” ብለውታል።

ጣብያው “ጸረ እስራኤል” አቋምን ያራምዳል በሚል ለዓመታት በእስራኤል ባለስልጣናት ሲወቀስ ቆይቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ደግሞ ወቀሳው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ድርጅቱ ከሐማስ ጋር ቁርኝት አለው ሲሉ የእስራኤል ባለስልጣናት ቢከሱም ጣብያው ግን ውድቅ አድርጎታል።

“ኔታንያሁ አል ጀዚራን እና የፕሬስ ነጻነትን ለማጥቃት የሚያበቃቸውን አንድም ማስረጃ ለዓለም ማቅረብ አይችሉም። ይልቁንም የሚሳካላቸው በጣብያው እና በሠራተኞቹ ላይ ሐሰተኛ እና ቀስቃሽ ክሶችን ማቅረብ ነው” ሲል አል ጀዚራ መግለጫ አውጥቷል።

“ያቀረቡትን ቀስቃሽ እና ሐሰተኛ ውንጀላ ተከትሎ በመላው ዓለም በሚገኙ የድርጅቱ ቢሮዎች እና ጣብያዎች ላይ ለተደቀነው አደጋ አል ጀዚራ ጠቅላይ ሚንስትሩን ተጠያቂ ያደርጋል” ብሏል።

እስራኤል ሆን ብላ ጋዜጠኞቹን ዒላማ እያደረገች ነው ሲል ጣብያው ጨምሮ ከሷል።

የአል ጀዚራ የጋዛ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ዋኤል አል-ዳህዱህ ልጅ የሆነውን ጋዜጠኛ ሐምዛ አል-ዳህዱህን ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

ቴል አቪቭ ግን ጋዜጠኞችን ዒላማ አላደረኩም በማለት አስተባብላለች።

የአል ጀዚራ መቀመጫ የሆነችው ኳታር ለስድስት ወራት ገደማ ያስቆጠረው ጦርነት እንዲያበቃ እስራኤል እና ሐማስን እያሸማገለች ትገኛለች።

ቀደም ሲል አገሪቱ ባሸማገለችው መሠረት ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም ከመደረሱም በላይ 105 እስራኤላዊያን ታጋቾች እንዲለቀቁ ሆኗል።

የአሁኑ የእስራኤል እርምጃ በድርድሩ ላይ ስለሚያሳርፈው ተጽዕኖ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

እስራኤል ከዚህ ቀደም አል ማያዲን የተባለን አነስተኛ የሊባኖስ ጣብያ አግዳለች።

በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ካሪን ጂን-ፒዬር “ውሳኔው እርግጥ ከሆነ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።

የጋዛ የአሁን ጦርነት የተጀመረው ሐማስ መስከረም መጨረሻ ባደረሰው ጥቃት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ገድሎ 253 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው። 130 የሚጠጉ ታጋቾች አሁን እንደተያዙ ሲሆን 34 ሚሆኑት ሳይሞቱ እንዳልቀረ ይገመታል።

እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ በማስገባት እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት ከ32 ሺህ 800 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና 75 ሺህዎቹ ደግሞ መቁሰላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከተገደሉት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በአውሮፓውያኑ 1996 የተቋቋመው አል ጀዚራ በአካባቢው አገራት እና መሪዎች ዙሪያ በሚያቀርበው ትችት የመካከለኛው ምስራቅን የመገናኛ ብዙሃን ምህዳር ለማነቃነቅ ችሏል።

አንዳንድ የአካባቢው አገራት በጣብያው ዘገባ ላይ ቅሬታ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ሳዑዲ አረቢያ፣ ዮርዳኖስ እና ግብጽን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ቢሮው ተዘግቷል ወይም ታግዷል።

እስራኤላዊያን ባለስልጣናት እና ተንታኞችን ያቀረበ የመጀመሪያው የአረብኛ ጣብያ መሆኑን አል ጀዚራ ይገልጻል።