የፊንላንድ ወታደሮች

ከ 1 ሰአት በፊት

በፊንላንድ ቫንታ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት የ12 ዓመት ታዳጊ ሶስት ተማሪዎችን በጥይት ማቁሰሉን ፖሊስ አስታወቀ።

ፖሊስ ቪየርቶላ በተሰኘው ትምህርት ቤት ከጥዋቱ ሶስት ሰዓት በፊት ለተፈጠረው ክስተት ምላሽ ለመስጠት እንዳቀና እና የአካባቢው ነዋሪዎችም በቤት ውስጥ እንዲቆዩ አሳስቧል።

ተጠርጣሪው የ12 ዓመቱ ታዳጊ መጀመሪያ ቢሸሽም በኋላ ግን በፖሊስ ቁጥጥር መዋሉ ተገልጿል።

በትምህርት ቤቱ 800 ተማሪዎች የሚማሩበት ሲሆን 90 ሰራተኞችም አሉት።

ከጥቃቱ በኋላም ተማሪዎቹ ከክፍሎቻቸው እንዳይወጡ እንደተነገራቸው ዋይ ኤልኢ የተሰኘው ሚዲያ ዘግቧል።

ተማሪዎቹ የስቅለት፣ ፋሲካ በዓላትን አክብረው ከዋናዋ መዲና በስተሰሜን ቫንታ በሚገኘው ትምህርት ቤታቸው የተመለሱት በዛሬው ዕለት ነበር።

ፖሊስ እንደተናገረው ተጠርጣሪው ታዳጊ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ ሮጦ የሸሸ ቢሆንም በመጨረሻም በሰሜን ሄልሲንኪ በሚገኝ ወንዝ አካባቢም በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል።

ታዳጊው የጦር መሳሪያም ይዞ የነበረ ሲሆን በቁጥጥር ስር ከዋለም በኋላ መሳሪያውን እንደተወሰደበትም ተነግሯል።

ሶስቱ ህጻናት የደረሰባቸውን ጉዳት በተመለከተ እስካሁን ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔቴሪ ኦርፖ የደረሰው ጥቃት በጣም እንዳሳዘናቸው ገልጸው፤ ከተጎጂዎች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከትምህርት ቤቱን ማህበረሰብ ጎን ነኝ ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ ከ7-15 ዓመት የሚሆኑ የአንደኛ እና የመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚማሩበት ነው።

የጥቃቱ ዜና መውጣቱን ተከትሎም ወላጆች ከ9-12 ዓመት የሆናቸው ተማሪዎች በሚማሩበት ጆኪራንታ በተሰኘው ስፍራም ተሰብስበው ታይተዋል።

ፖሊስ መጀመሪያ ላይ ጥቃት የደረሰባቸውና እና ጥቃት አድራሹ ዕድሜ 13 ነው ቢልም በኋላ ላይ ግን ሁሉም 12 ዓመታቸው መሆኑን ገልጿል።

ትምህርት ቤቱ የሚገኝበት ቫንታ 240 ሺህ ነዋሪዎች ያሏት የፊንላንድ አራተኛዋ ትልቅ ከተማ ናት።

ፊንላንድ በአውሮፓውያኑ 2007 እና 2008 ሁለት የከፉ የትምህርት ቤት ተኩሶችን ማስተናገዷን ተከትሎ አገሪቷ የጦር መሳሪያ ህጓን ጠበቅ አድርጋለች።

ነገር ግን አዳኞች እና የጦር መሳሪያ አፍቃሪዎች በበዙባት ፊንላንድ ከ5.5 ሚሊዮን ነዋሪዎቿ ውስጥ 430 ሺህ የሚሆነው ህዝቧ የጦር መሳሪያ ፈቃድ እንዳለው ከመንግሥት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ነዋሪዎች ምን ያህል የጦር መሳሪያ መያዝ እንደሚችሉ ህጉ በግልጽ የማይደነግግ ሲሆን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር 1.5 ሚሊዮን የጦር መሳሪያዎች በስርጭት እንዳሉ አስታውቋል።

በአውሮፓውያኑ 2007 አንድ የ18 ዓመት ተማሪ ቱሲላ በተሰኘችው ከተማ ሰባት ተማሪዎችን እና መምህሩን በጥይት ገድሏል። በቀጣዩ ዓመትም ሌላ ተማሪ በካውሃጆኪ ከተማ ዘጠኝ ተማሪዎችን እና አንድ መምህርን በጥይት መግደሉ ተገልጿል።