
ከ 2 ሰአት በፊት
የአስራ አንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት (ሲኦፒ) ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ለመወያየት የቀረበለትን ጥሪ ውድቅ ያደረገው መንግሥት በአገሪቱ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር ፍላጎት ስለሌለው መሆኑን ገለጸ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ከተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ሰኞ መጋቢት 23/2016 ዓ.ም. ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ የጥምረቱ አባላት ግን ሳይሳተፉ ቀርተዋል።
የጥምረቱ አባላት በውይይቱ ላለመገኘት የወሰኑት “መንግሥት አሳሳቢ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ስለማይፈልግ” መሆኑን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር መረራ እንዳሉት ውይይቱ “ዝም ብሎ የለበጣ እና ከፎቶ ባለፈ ምንም ቁም ነገር እንደማያመጣ ሰለተረዳን እና ተቃዋሚዎችን አናገርኩ የሚል የይምሰል በመሆኑ” ላለመሳተፋቸው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባለፉት ስድስት ዓመታት በአገር ውስጥ እንዲሁም ኔዘርላንድ እና ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በውጭ አገራት ከእሳቸውም እንዲሁም ከተወካዮቻቸው ጋር ድርድር ቢደረግም ፍሬ አላፈራም ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
ከገዢው ፓርቲ ጋር በተደረጉ በርካታ ንግግሮችም የተረዱት መንግሥት “መሠረታዊ እና አሳሳቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መደራደርም ሆነ መነጋገር አይፈልግም” ሲሉም ፕሮፌሰር መረራ አጽንኦት ይሰጣሉ።
እሳቸው መሠረታዊ ብለው ከሚያነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን ጨምሮ በአገሪቱ ለበርካታ ሰዎች እልቂት የእየሆኑ ያሉትን ግጭቶች እና ጦርነቶችን ነው።
እነዚህ ጦርነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዴት ይቋጩ? በሚለው ጉዳይ ላይ “መንግሥት መነጋገርም ሆነ ወደ መደራደር አይሄድም” ይላሉ።
በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነው “የመገደደል ፖለቲካን ማቆም” ዋነኛ እና መሠረታዊ ጉዳይም እንደሆነም ነው የሚገልጹት።
ሌላኛው ፖለቲከኛው የሚጠቅሱት ጉዳይ አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲ የምታደርገው ሽግግር መክሸፉን በመጥቀስ፤ ይህንን የአገሪቱ የዲሞክራሲ የመቀልበስ ሂደት ላይም ገዢው ፓርቲ መወያየት አይፈልግም ይላሉ።
- “ኢትዮጵያ ከመገዳደል ፖለቲካ ወደ መደራደር ፖለቲካ መሻገር አለባት”- ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና30 መጋቢት 2022
- ኦፌኮ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ሁሉን ያሳተፈ ብሔራዊ ምክክር እንዲካሄድ ጥሪ አቀረበ28 መጋቢት 2022
- “መንግሥት አይወክለኝም ለሚሉ ወገኖች ምርጫ ምላሽ ይሰጣል” ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና4 ሀምሌ 2019
“መነጋገር ደግሞ ውል እና ማሰሪያ ያለው ነገር ይዞ መሠረታዊ ነገሮችን አንስተን ሰጥቶ በመቀበል ፖለቲካ ችግሮችን መፍታት ካልቻልን ንግግሩ ብዙም ትርፍ ስለሌለው ሕዝቡንም ላለማሳሳት ያደረግነው ነው” ብለዋል።
አገሪቷን እየናጧት ያሉ ግጭቶችንም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ ያሏቸውን ጉዳዮች ፊት ለፊት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በማንሳት መነጋገር አይቻልም ነበር ወይ? በሚል ቢቢሲ ፕሮፌሰር መረራን ጠይቋቸዋል።
እሳቸውም ከዚህ በፊት የተደረጉ በርካታ ንግግሮች ፋይዳ እንዳልነበራቸው እና ወደየትም ያልተራመዱ መሆናቸውን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ጦርነቱን ማስቆም አልተቻለም። መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ካልተወያየን ከፎቶ ባለፈ ምንም ቁም ነገር ስለማያመጣ መሳተፍን አልመረጥንም እንጂ መነጋገርንም ሆነ መደራደርን ጠልተን አይደለም” ሲሉም መልሰዋል።
አክለውም “በእነዚህ ንግግሮች የመጣ ለውጥ፣ የምናስተካክለው ነገር ወይም የምንፈይደው ነገር ስለሌለ ነው። ሕዝቡን በማይሆን መንገድ እየተነጋገርን ነው፤ በውይይይ እየተፈታ ነው የሚል አጉል ተስፋ ላለመስጠት እኛ የመሰለንንን እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረውን ውይይት ግብዣ ላለመቀበል የመወሰናቸው እርምጃ ዋጋ የሚያስከፍላችሁ አይመስላችሁም ወይ በሚልም ቢቢሲ የጠየቃቸው መረራ “ከዚህ በላይ ዋጋ ከፍለናል” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ባደረገችው ምርጫ የእሳቸው ፓርቲ እና ኦነግ “ተገፍተው” ከምርጫው እንደወጡ በመጥቀስ የከፈሉት ዋጋ መሆኑን አንስተዋል።
ኦፌኮ ብቻ ሳይሆን በምርጫው ተሳታፊ የነበረው አብን አንዳንድ አመራሮች ለእስር መዳረጋቸውንም ያነሱት ፕሮፌሰር መረራ “ሌሎቹም አልተጠቀሙም” ይላሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉት የአንድ ቀን ውይይት ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት ላይ አስተያየቶችን እና ትችቶችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
መንግሥት እያከናወናቸው ያሉ ልማቶችን በተመለከተ ለተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ገለጻ መደረጉም ተጠቅሷል።
መረራ በበኩላቸው በእነዚህ ልማቶች ላይ ጥያቄ በማንሳትም “የሚለማው ሕዝብ ነው መሬት አይደለም። ይሄንን ገዢው ፓርቲ እንዲረዳ ካልፈለገ? ምን ማድረግ ይቻላል?” ሲሉም ይጠይቃሉ።
ሁለቱ ሰፊ የኢትዮጵያ ክልሎች የድሮኖችን ጥቃት ጨምሮ ሰፊ እልቂት እና ጦርነት እያስተናገዱ እንደሆነም የሚያነሱት መረራ፤ እነዚህን እልቂቶች “ወደ ጎን ትቶ ይሄ ህንጻ ተሠራ፣ መንገድ ተሠራ በማለት ያለውን የሕዝብ ትግል ዝቅ ማድረግ ተገቢ አይደለም” ብለዋል።
አክለውም “በግልጽ ለመንግሥት፣ ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለሕዝቡ እያልን ያለው እየተካሄደ ያለው ጨዋታ የትም አያደርስም። ኳሱ ያለው በገዢው ፓርቲ ነው እኛ ጋር አይደለም” ብለዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ለፖሊሲ ግብዓት አስፈላጊ የሆኑ እርማቶች እና ማስተካከያዎች ተለይተው ወደፊት ለመቀጠል በሚያስፈልጉ የትብብር ዓይነቶች ላይ ምክክር መካሄዱንም የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት የተመሠረተው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ የኦጋዴን የነጻነት ግንባር፣ ህብር ኢትዮጵያ፣ አረና ትግራይ ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የአፋር ሕዝቦች ፓርቲን የያዘ ሲሆን ከዚህ ቀደምም አንዳንድ የመንግሥት ውሳኔዎችን በመቃወም ይታወቃል።
በአማራ ክልል እንዲሁም በሌላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተግባራዊ ይሆናል የተባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መራዘም ተቃውሞም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።