
2 ሚያዚያ 2024, 07:09 EAT
ተሻሽሏል ከ 7 ሰአት በፊት
ከመሐል ከተማዋ ሩቅ አይደለም። እንዲያውም የከተማዋ ማዕከል እንደሆነ ይታመናል። ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ የሰዎች እንቅስቃሴ የበዛበት፣ በአንጻሩ የተሽከርካሪዎች ፍሰት የተገደበበት ነው።
በአንድ ጊዜ አምስትና ከዚያ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግዱት የከተማዋ ፈጣን እና ዘመናዊ መንገዶች በዚህኛው የከተማዋ ክፍል የሉም። መንገዶቹ ጠባብና ሁለት ተሽከርካሪ ብቻ የሚያሳልፉ ናቸው።
ተጠጋግተው የተሠሩት ሕንፃዎች አንዱ ከሌላው በማይለዩበት ሁኔታ እርስ በርስ የተደጋገፉ ናቸው። ከአረብኛ እና እንግሊዝኛ በተጨማሪ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በሌሎች ቋንቋዎችም የተፃፉበት ነው። ከሌሎች ቋንቋዎች አኳያ አማርኛ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ይመስላል።
የኢትዮጵያ የምግብ ቅመሞች፣ የሐበሻ ልብሶች፣ የጀበና ቡና መሸጫዎች፣ የመዋቢያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ቤቶች ማስታወቂያዎቻቸውን በር ላይ በአማርኛ ጭምር ጽፈዋል። አማርኛ ከጽሑፍ ባሻገር በብዛት የሚነገርበት ሰፈርም ነው። የደማቋ ዱባይ ሌላኛው ገፅታ ‘ፍሪጅ አል መረር’. . .
ፍሪጅ አል መረር ሦስት አራት ጎዳናዎች አሉት። በጎዳናዎቹ ግራ እና ቀኝ የቆሙት ሕንፃዎች ዲዛይናቸውና ቁመታቸው ተመሳስሎ የቆመ ነው። ሁሉም ባለ አራት ወለል ናቸው። የሕንፃዎቹ ሁሉም የምድር ቤቶች እና የተወሰኑት ደግሞ አንደኛ ወለልን ጨምሮ የንግድ ቤቶች ናቸው።
የተለያዩ አገራት ዜጎች የተለያየ ሥራ ይሠሩባቸዋል። የባንግላዲሽ ሬስቶራንት፣ የሕንድ ባሕላዊ ምግብ፣ የፓኪስታን ባህላዊ ትኩስ መጠጦች የሚሸጡበት አካባቢ ነው። በእርግጥ የእነዚህ ነጋዴዎች ቁጥር ከኢትዮጵያውያን አንፃር ሲታይ ምንም ሊባል የሚችል ነው። ከአምስት የንግድ ቤቶች ቢያንስ ሦስቱ የኢትዮጵያውያን ናቸው. . .
- በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ትልቁ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሚገነባባት አረብ አገር11 መጋቢት 2024
- የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለምን ተመራጭ ሆነች?5 መጋቢት 2024
- አረብ ኤምሬትስ በየመን ፖለቲካዊ ግድያዎችን በገንዘብ መደገፏን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ24 ጥር 2024
የኢትዮጵያ “ኮፊ ሐውስ” በፍሪጅ አል መረር. . .
በብዛት በኢትዮጵያውያን የተያዙት እነዚህ የንግድ ቤቶች አብዛኞቹ የኢትዮጵያ የጀበና ቡና እንደሚሸጡ ምልክቶች አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚታዩት የጀበና ቡና ማድመቂያ ፖስተሮች በእነዚህ ቡና ቤቶችም ተለጥፈዋል። በእርግጥም ቡና ይሸጣል።
ቤቶቹ በዋናነት ሁለት ሥራዎች አሏቸው፤ አንደኛው ቡና መሸጥ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሺሻ ማስጨስ። ሺሻ ማጨስ በአገሪቱ ሕግ የማይከለከልና በይፋ የሚሠራ በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑ የሚሠሩት ሕጋዊ ሆነው ነው። የሥራው ሁኔታ ግን በደማቋ እና ሽቅርቅሯ ዱባይ በሚመጥን ደረጃ የሚሠራ አይደለም።
ፍሪጅ አል መረርን ያየነው በምሽት ነበር። በምሽት ለአዲስ ሰው በቀላሉ የሚደፈር ድባብ የለውም። እነዚህ ጠባብ የንግድ ቤቶች [ምናልባት 4 ሜትር በ4 ሜትር ይሆናሉ] በምሽት የቤት ውስጥ መብራታቸውን ያደበዝዛሉ፣ ከሦስት እስከ አምስት ደንበኛ ከገባ ቤቶቹ ይሞላል። በሮቹ ሁል ጊዜ ክፍት ስለሚሆኑ ከአላፊ አግዳሚው ዕይታ ውጪ መሆን አይቻልም።
እዚህም እዚያም የሺሻ እሳት ለማቀጣጠል የሺሻ ዕቃውን ውጪ ላይ የሚወዘውዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ይታያሉ። እነዚሁ ኢትዮጵያውያን መንገደኛ ባለፈ ቁጥር “…ቡና ጠጡ” እያሉ ይጋብዛሉ። ደንበኞች በግልም በቡድንም ሆነው በሁለቱም አቅጣጫዎች ወደ ቡና ቤቶቹ እያማተሩ ይርመሰመሳሉ። በዚህ ሁኔታ እንኳን በእግር ለመንቀሳቀስ መኪና ውስጥ ሆኖ እንቅስቃሴውን ለመቃኘትም አስፈሪ ነው. . .
ፍሪጅ አል መረር እንደሌላው የዱባይ አካባቢ ሁሉ ጠዋት ላይ ዘግይቶ ነው የሚከፋፈተው። በዱባይ ከጠዋት አራት ሰዓት በፊት የሚጀመሩ አገልግሎቶች ውስን ናቸው። የግል የንግድ ተቋማት ሌሊቱን ሙሉ ስለሚሠሩ የቀን ሥራቸውን የሚጀምሩት በአብዛኛው ከጠዋቱ 5:00 ሰዓት በኋላ ነው።
የብዙዎቹ ባለቤቶች በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ናቸው። ደንበኛ በራሱ ምርጫ የሚሄድባቸው ቡና ቤቶች አሉ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ግን በር ላይ ቆመው አላፊ አግዳሚውን በመጥራት የሚያስገቡ ናቸው።
ተጠጋግተው በተገነቡት የፍሪጅ አል መረር ሕንጻዎች የግርጌ በር ላይ ቆመው ወይም እየተንቀሳቀሱ ከሚታዩት ሴቶች 90 በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ናቸው. . .

አንዱ ቡና ቤት የሜላት እና ጓደኛዋ ነው። ጠባቧ ቡና ቤት መሐል ላይ በመጋረጃ ለሁለት ተከፍላለች። ከጀርባ ያለው የግብዓት ማዘጋጃ ሲሆን፣ የፊት ለፊቱ ደግሞ የደንበኞች መቀመጫ ነው። ቡና ቤቷን ለሁለት ነው የሚሰሩባት። የማስተናገጃ ቦታው የመያዝ አቅሙ አምስት ሰው ብቻ ነው። ሁለቱን ባለቤቶቹ ይዘውታል።
በፍሪጅ አል መረር ቡና ቤቶች ውስጥ ቡና ብቻ ከሚያዝ ደንበኛ ሁለቱንም በአንድ ላይ [ቡና እና ሺሻ] የሚያዝ ይመረጣል። የአንድ ቡና ዋጋ 10 ድርሃም (150 ብር አካባቢ) ነው። አንድ ሺሻ ደግሞ 20 ድርሃም ይሸጣል። ሺሻው ዳጎስ ያለ ትርፍ ስለሚያስገኝ የሺሻ ደንበኞች የተሻለ ተፈላጊነት አላቸው።
ሱዳኖች ሺሻ ያዛሉ፣ ቡናም ይጠጣሉ። ትዕዛዛቸውም በአንድ ብቻ አያበቃም፣ ይደጋግማሉል። ወደ ቡና ቤቱ ሲሄዱም ሰብሰብ ብለው ነው። ለዚህ ነው “ሱዳናውያን ደንበኞችን የምናከብረው” ትላለች ሜላት። ብዙ ሱዳናዊ ደንበኛ ያለው ከፍ ያለ ገቢ እንደሚሰበስብ ይታመናል። ብዙዎቹም ግባቸው ብዙ ሱዳኖችን ደንበኛ ማድረግ ነው።
ሜላት የሌሎች አገራት ዜጎችም አገልግሎታቸውን እንደሚጠቀሙ ትናገራለች። በአካባቢው በብዛት ቢኖሩም ቡና የማይጠጡት ሕንዶችና ፓኪስታኖች ናቸው።
“እነርሱ ጋር ጉርብትና እንጂ የቢዝነስ ደንበኝነት የለንም” ትላለች ሜላት። ከሁሉም ጋ እየተቀመጡ ሺሻ ማጨስ የሥራው ባሕሪ ስለሆነ ይህንን ማድረግ ያልተጻፈ ግዴታ ነው። ይህም በሁሉም ቡና በሚሸጡ ኢትዮጵያውያን የተለመደ ሥራ ነው።
ሜላት ከጓደኛዋ ጋር በመሆን በዚህች ጠባብ ቤት ከአራት ዓመት በላይ ሠርታለች። አገር ቤት ያለ ልጇን እና ቤተሰቦቿን የምትረዳው ከዚህ ሥራ በምታገኘው ገቢ ነው። እንዲያም ሆኖ ሥራውን አትወደውም። ማስታወስ የማትፈልጋቸው አስቀያሚ ገጠመኞች አሏት። በደንበኞቻቸው የሚሰጣቸው ግምት ያናድዳታል። “ከሱቅ ዕቃ እኩል ነው የሚያዩን” ትላለች።
ሥራ ለመቀየር ብዙ ጊዜ አስባ አልተሳካላትም። ገንዘብ አጠራቅማ ወደ አገር ቤት ተመልሳ ከልጇ እና ቤተሰቧ ጋር ለመኖር ከአንዴም ሁለት ጊዜ ተሰናድታ ነበር። ነገር ግን በየጊዜው የሚደፈርሰው የኢትዮጵያ የሰላም ዋስትና ሊሰጣት አልቻለም። እንዲያውም በጦርነት ምክንያት ከሥራ ውጪ የሆኑ ቤተሰቦቿን ለመደጎም በዚሁ ሥራ መቀጠል ብቸኛ አማራጭ ሆኖባታል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ውስጥ ለሚኖር ማንኛውም ሰው የአገሪቱን ሕግ ማክበር የሕልውና ጉዳይ ነው። በሆነ አጋጣሚ ሕግ ጥሶ መገኘት ከአገር ሊያስባርር ይችላል።
ለእነሜላት እና ጓደኛዋ ደግሞ ከሥራቸው አንጻር ስጋቱ እጥፍ ነው። የአገሬው ሰዎች ከደንበኞቻቸው መካከል ናቸው። አንዳንዴ ፖሊሶች ያለ ደንብ ልብስ ጎራ ብለው ቡና ጠጥተው ወይም ሺሻ አጭሰው የሚሄዱበት አጋጣሚ አለ።
ይህ ከገበያ አንጻር መልካም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የዛሬው ደንበኛ “ትክክል አይደለም” ብሎ ያመነበት ነገር ካለ ነገ በደንብ ልብሱ ሊመጣ ይችላል። የአገሪቱ ሕግ ጥብቅ በመሆኑ ለእነ ሜላት የመኖሪያ ፈቃድ መያዝ ስጋትን ሙሉ በሙሉ አያስቀርም. . .
በፍሪጅ አል መረር የሚሠሩ ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው እና በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ናቸው።
ብዙዎቹ በሕጋዊ መንገድ ለቤት ሠራተኛነት ወደ ዱባይ የሚሄዱ ናቸው። ዱባይ ከደረሱ በኋላ ግን በተለያየ ምክንያት ከአሠሪዎቻቸው ይጠፉና ሕጋዊነታቸውን ያጣሉ። በዚህ ሁኔታ ሕጋዊነታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን እንደ አማራጭ የሚወስዱት አንዱ ፍሪጅ አል መረር ውስጥ ቡና [ሺሻ] መሸጥን ነው።
ለዚህም ቡና መሸጥ ከጀመረች ሁለት ዓመት ሊሞላት የተቃረበችው ቤዛ አንድ ምሳሌ ናት። ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የላትም፤ ፈቃድ ካላት ጓደኛዋ ጋር በመተባበር ነው የምትሠራው። ፓስፖርቷ እና የመኖሪያ ፈቃዷ አሠሪዋ ጋር እንደተቀመጠ ነው ጠፍታ ከቤት የወጣችው።
ፖሊስ አካባቢውን ሲያስስ በተደጋጋሚ አምልጣለች። አሁንም በር ላይ የምትቆመው ለሁለት ነገር ነው። አንድም ደንበኛ ወደ ቤቷ እንዲገባ ለመጋበዝ፣ ሁለትም ፖሊስ በአካባቢው መኖሩን ለመቃኘት።
በሰው ቤት ተቀጥራ በምትሠራበት ወቅት ቤዛ የተሻለ ነጻነት እንደነበራት ትናገራለች። አሠሪዎቿንም በክፉ ማንሳት አትፈልግም። ምናልባትም ሐሳቧን ብታስረዳቸው የመኖሪያ ፈቃዷን እና ፓስፖርቷን ሰጥተው ሊያሰናብቷት ይችሉ እንደነበር ትገምታለች። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ስላልነበረች መጥፋትን መርጣለች።
ፍሪጅ አል መረር ከገባች በኋላ ከምትሠራው ገንዘብ ቆጥባ የመኖሪያ ፈቃዷን ለማስተካከል ሁልጊዜ ታልማለች። ነገር ግን በጓደኞቿ የደረሰውን በመስጋት እስካሁን የጀመረችው ነገር የለም። ደላሎች “የመኖሪያ ፈቃድ እናሰጣችኋላን” እያሉ እንደቤዛ ያሉ ሴቶችን ከፍተኛ ገንዘብ ተቀብለው ይጠፉባቸዋል።
ቤዛ ወደ ፍሪጅ አል መረር ያመራችው የተሻለ ክፍያ ይኖራል በሚል ነው። በእርግጥም ተቀጥራ ትሠራ ከነበረበት ደመወዝ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ገንዘብ ያገኘችባቸው አጋጣሚዎች አሉ። እንዲያም ሆኖ ግን የቆጠበችው ገንዘብ እንደሌላት ትገልጻለች።
“እየተሳቀቅን እንሠራለን ግን ደግሞ ያ ገንዘብ የት እንደሄደ አይታወቅም” የምትለው ቤዛ፣ በዚህ ሥራ መቀጠል ምርጫዋ አይደለም። የመኖሪያ ፈቃዷ ቢስተካከልላት የሐበሻ ምግብ ቤት ከፍቶ የመሥራት ሕልም አላት. . .

የአገሪቱ ፖሊስ ጥናት በማድረግ ያለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ላይ አሰሳ ያደርጋል። ፍሪጅ አል መረር በተደጋጋሚ ፖሊስ አሰሳ የሚያደርግበት አካባቢ ነው። ቤዛ እና ሜላት ብዙ ጓደኞቻቸው በዚህ አሰሳ ታፍሰው መወሰዳቸውን ይናገራሉ።
እነሱ እንደሚሉት አሁን በአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀንሷል። ከዓመት በፊት በአካባቢው የሌላ አገር ዜጎች የሌሉ እስኪመስል ድረስ ሁሉም ቦታዎች በኢትዮጵያውያን የተያዙ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት ከሞላ ጎደል በሥራ ላይ ያሉት የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ብቻ ናቸው።
በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሐሰን ኢትዮጵያውያን በቡና ቤቶች እና ሺሻ ቤቶች በስፋት ስለመሰማራታቸው መረጃ አላቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ይህ ሥራ ዱባይ ብቻ ሳይሆን በአቡ ዳቢ እና በአል ዓይን ከተሞችም የተለመደ ነው።
በዚህ ሥራ መሠማራት በአገሪቱ ሕግ የማያስጠይቅ ቢሆንም “በሺሻ ሽፋን ግን የአገርን ክብር የሚያጎድፉ ተግባራት ይፈጸማሉ” ይላሉ። በአብዛኛው ከግንዛቤ ማነስ እና በደላሎች በመታለል ኢትዮጵያውያኑ ወደዚህ ሥራ እንደሚገቡም ያነሳሉ።
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ከሆነ ዱባይ ከተማ ውስጥ ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሴቶች በብዛት ወደ ፍሪጅ አል መረር በማምራት “የቡና ቤት” ሥራ ይጀምራሉ። ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ሕግ መሠረት የቱሪስት ቪዛ ስለማይከለከል “ይህንን ሥራ ለመሥራት አቅደው የሚመጡም አሉ” ብለዋል አምባሳደሩ።
ሌሎች በአካባቢው ያገኘናቸው ሰዎች ደግሞ ስለ ፍሪጅ አል መረር ሌላ አስተያየት ይሰጣሉ። አካባቢውን እናውቀዋለን የሚሉ ነዋሪዎች እንደሚሉት አካባቢው የሺሻ እና ቡና መሸጫ ቦታ ብቻም አይደለም።
“የወሲብ ንግድ” የሚጧጧፍበት አካባቢ ነው ይላሉ። የወሲብ ንግድ ደግሞ በአገሪቱ ሕግ የተከለከለ ድርጊት ነው። በመሆኑም ብዙዎች ይህንን ተግባር በእነዚህ ቡና ቤቶች ውስጥ ደብቀው የሚሠሩ እንደሆኑ ይገልጻሉ።
ይህንን በተመለከተ እርግጠኛ ያለሆኑት ቤዛ እና ሜላት፤ ራሳቸው ይህንን ድርጊት እንደማይፈጽሙ ነገር ግን ሌሎች ሊኖሩ ይችላሉ ይላሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ከቡና እና ከሺሻ ደንበኞቻቸው ወደዚህ ድርጊት የሚገፉ ጥያቄዎች እንደሚቀርብ ላቸው አልሸሸጉም።
በፍሪጅ አል መረር ከቡና ቤቶቹ በተጨማሪ ሌሎች የንግድ ቤቶችም በብዛት በኢትዮጵያውያን የተያዙ ናቸው። የባህል ልብስ መሸጫ ሱቅ፣ የቅመማ ቅመሞች እና የመዋቢያ ዕቃዎች ሱቆች በብዛት ይገኛሉ።
በተጨማሪም የውበት ሳሎኖቹ በታዋቂ ኢትዮጵያውያን አርቲስቶች ፎቶ ደምቀው እራሳቸውን ያስተዋውቃሉ። ኢትዮጵያውያኑ የንግድ ቤት ማስታወቂያዎቻቸውን የሚጽፉትም በሦስት ቋንቋ ነው። በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ።
ከጽሑፍ ባሻገርም አማርኛ በፍሪጅ አል መረር በስፋት የሚነገር ቋንቋም ነው። አንዳንድ የአማርኛ ቃላትን ከኢትዮጵያውያኑ በተጨማሪ የሌሎች አገራት ዜጎችም እዚም እዚያም ጣል ያደርጋሉ።
