የአየር ጥቃት የተፈጸመበት መኪና

ከ 6 ሰአት በፊት

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው የአየር ጥቃት የረድዔት ሰራተኞች መገደላቸው ተነገረ።

አውስትራሊያዊ፣ እንግሊዛዊ እና ፓላንዳዊ ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ ሰራተኞቹ በእስራኤል መከላከያ የአየር ጥቃት እንደተገደሉበት ወርልድ ሴንትራል ኪችን የተሰኘው የረድዔት ተቋም መስራች ሼፍ ሆዜ አንድሬስ ገልጸዋል።

በጋዛ በሃማስ የሚመራ ሚዲያም ጥቃቱን ያደረሰችው እስራኤል መሆኗን ዘግቧል።

የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ቢቢሲ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ “ጥልቅ ግምገማ” እያካሄደ መሆኑን አስታውቋል።

በማዕከላዊ ጋዛ ሰርጥ የሚገኘው የአልአቅሳ ሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ እንደገለጹት የፍልስጤማዊ አሽከርካሪያቸውን ጨምሮ የአራቱ የረድዔት ሰራተኞች አስከሬን ወደ ሆስፒታሉ መምጣቱን ገልጸዋል።

ምንጩ እንደተናገሩት ሰራተኞቹ ዲር አል በላህ በተሰኝችው የባህርዳርቻ ከተማ በመኪና እየተጓዙ እያለ ነው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።

የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ የረድኤት ሰራተኛ የሆነው ዜጋቸው ላልዛውሚ ፍራንክኮም ከተገደሉት መካከል አንዱ መሆኑን አረጋግጠው ለቤተሰቡ እና ወዳጅ ዘመዶቹ መጽናናትን ተመኝተዋል።

“በጋዛ ውስጥ በከፋ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ላሉ ነዋሪዎች እርዳታ ለማቅረብ በበጎ ፈቃደኝነት ተሰማርቶ ሲሰራ የነበረ ሰው ነው። ይህ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው” በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አክለውም አገራቸው ለዚህ ጥቃት ሙሉ ተጠያቂነትን እና ኃላፊነትን” እንደምትጠብቅ ተናግረዋል ይህ “በፍጹም መደረግ ያልነበረበት አሳዛኝ ክስተት ነው” ብለዋል።

የረድዔት ሰራተኞቹ የተቋማቸው አርማ ያለበትን የጥይት መከላከያ ጃኬቶችን ለብሰው እንደነበር የፍልስጤም የሆስፒታል ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ተገደሉ የተባሉትን የረድዔት ሰራተኞች የተለያየ አገር ዜግነት፣ የፓስፓርት ምስሎችን እና ቪዲዮዎችን በኢንተርኔት ላይ ያጋሩ ሲሆን ዝርዝር መረጃዎች እስኪወጡ እየተጠበቀ ነው።

ተቋሙ ባወጣው መግለጫ ሰራተኞቹ በጋዛ የሰብዓዊ የምግብ አቅርቦትን ለመደገፍ እየሰሩ ባለበት ወቅት “በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ጥቃት መገደላቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እንደደረሱት” ገልጿል።

“ይህ አሳዛኝ ነገር ነው። የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች እና ሲቪሎች መቼም ቢሆን ዒላማ መሆን የለባቸውም። ሁሉንም መረጃዎች ሰብስበን ስንጨርስ ተጨማሪ መረጃዎች እናካፍላለን” ሲል መግለጫው አክሏል።

የተቋሙ መስራች እና ታዋቂ የሆኑት አንድሬስ በበኩላቸው የእስራኤል መንግሥት “የዘፈቀደ ግድያውን እንዲያቆም” በኤክስ ላይ በለጠፉት ጽሁፍ ጠይቀዋል።