ታይዋን

ከ 4 ሰአት በፊት

ታይዋን ረቡዕ ዕለት በሬክተር ስኬል 7.4 በሆነ ከፍተኛ ርዕደ መሬት ስትናጥ እስካሁን የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ታውቋል።

ርዕደ-መሬቱ በተለይ በሁዋሊየን ከተማ በርካታ ሕንፃዎችን የወዘወዘ ሲሆን የነብስ አድን ሠራተኞች ሕይወት ለመታደግ እየተሯሯጡ ነው።

ደሴቷ ታይዋን እንዲህ ያለ ጠንካራ የሚባል ርዕደ-መሬት ባለፉት 25 ዓመታት አስተናግዳ አታውቅም።

በዋና ከተማዋ ታይፔይ ሕንፃዎች በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ሲነቃነቁ የሚያሳዩ ቪድየዎች ማሕበራዊ ሚደያዎች ላይ ተለቀዋል።

“የርዕደ-መሬት ለምድር የተጠጋ ነው። በመላው ታይዋን እና በደሴቱ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ተሰምቷል። በ25 ዓመታት ውስጥ ይህ ጠንካራው ነው” ይላሉ የታይፔይ የርዕደ-መሬት ጥናት [ሴይስሞሎጂ] ማዕከል ኃላፊ ዉ ቺዬን ፉ።

ታሮኮ ብሔራዊ ፓርክ በሚባለው ሥፍራ አንድ ሰው ሲሞት ሶስት ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የታይዋን ብሔራዊ እሣት አደጋ ኤጀንሲ አስታውቋል። ብሔራዊ ፓርኩ ከሁዋሊየን ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው።

ኤጀንሲው አክሎ እንደገለጠው በርካታ ሰዎች ሁዋሊየን ውስጥ ባሉ መተላለፊያ ቱቦዎች ውስጥ ተቀብረው ይገኛሉ።

የታይዋን ግዙፉ ‘ቺፕ’ አምራች ኩባንያ ቲኤስኤምሲ ለደኅንነት ሲል በርካታ ሠራተኞቹን ከፋብሪካዎቹ ማስወጣቱን አስታውቋል።

ቲኤስኤምሲ፤ እንደ አፕል እና ንቪዲያ ላሉ ግዙፍ የቴከኖሎጂ ኩባንያዎች ‘ቺፕ’ የሚያመርት ኩባንያ ነው።

ሌላኛው ለአፕል መለዋወጫ የሚያመርተው ፎክስኮን ግን ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

በርዕደ-መሬቱ ምክንያት ሱናሚ ሊነሳ ይችላል የሚል የማስጠንቀቂያ መልዕክት ለደሴቷ ነዋሪዎች እና ለጎረቤት አካባቢዎች ተልኳል።

በመዲናዋ ታይፔይ መኖሪያ ቤቶች ፈራርሰው ሰዎችን የማዳን ሥር ሲከናወን፤ እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ከቤታቸውን ከትምህርት ቤት እንዲወጡ ሲደረግ የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አሳይተዋል።

አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ እንዳስመለከተው በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት መኪናዎች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል እንዲሁም የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች ምስቅልቅላቸው ወጥቷል።

ኔትብሎክስ የተሰኘው የኢንተርኔት መቋረጥ ተቆጣጣሪ ድርጅት እንደዘገበው በታይዋን ኢንተርኔት የተቋረጠ ሲሆን የኤሌክትሪክ ኃይልም የለም።

የመሬት መንቀጥቀጡ ታይዋንን የመታው ረቡዕ ጠዋት በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር 1፡58 ገደማ ነው። ከዋናው ርዕደ-መሬት በኋላ ቢያንስ 9 አነስተኛ ማግኒቲውድ ያላቸው መንቀጠቀጦች ተሰምተዋል።

የአሜሪካው ጊኦሎጂካል ሰርቬይ እንደገለጠው ርዕደ-መሬቱ የተነሳው ከሁዋሊየን ከተማ 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።

በአውሮፓውያኑ መስከረም 1999 ታይዋን 7.6 ማግኒቲውድ ባለው ርዕደ-መሬት ተመትታ 2400 ሰዎቸ መሞታቸው፤ 5 ሺህ ሕንፃዎች ደግሞ መውደማቸው ይታወሳል።

የጎረቤት ሀገር ጃፓን ባለሥልጣናት ረቡዕ ታይዋንን ከመታው ርዕደ-መሬት በኋላ ነዋሪዎች በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የፊሊፒንሰ ርዕደ-መሬት ማዕከል ደግሞ የሱናሚ አደጋ ሊኖር ይችላል ቢልም በኋላ ግን ይህን ማስጠንቀቂያውን ሽሯል።