April 2, 2024

በተስፋለም ወልደየስ
በመኖሪያ ቤቶች የሚደረገው የኪራይ ዋጋ ጭማሪ፤ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ እንዲሁም በክልሎች የሚቋቋም ተቆጣጣሪ አካል በሚወስነው መሰረት እንዲከናወን የሚያደርግ አዋጅ ዛሬ በፓርላማ ጸደቀ። የተቆጣጣሪ አካሉ “የሀገሪቱን ነባራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች” ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በየዓመቱ ከሰኔ 30 ጀምሮ ለአንድ ዓመት የሚጸና የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግ በአዲሱ አዋጅ ተደንግጓል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ዕለት ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆነው ይህ አዋጅ፤ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደርን ለመደንገግ የተዘጋጀ ነው። በስድስት ክፍሎች እና በሰላሳ ሁለት አንቀጾች የተዋቀረው አዋጁ፤ ስለመኖሪያ ቤት ኪራይ እና ዋጋ፣ ውል የሚቋረጥባቸውን አካሄዶች፣ የተቆጣጣሪ አካል ስልጣን እና ተግባር እንዲሁም የጥቆማ እና ቅሬታ አቀራረብ ስነ ስርዓትን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን በውስጡ አካትቷል።
“የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር” የሚመለከተው ይህ አዋጅ ከያዛቸው ድንጋጌዎች መካከል፤ “ነባር የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውልን” የተመለከተው ይገኝበታል። “አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በጹሁፍ የተደረገ ማንኛውም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ውል፤ በአከራይ እና ተከራይ ስምምነት እንዲቋረጥ ካልተደረገ በስተቀር፤ በአግባቡ መረጋገጥ እና መመዝገብ እንዳለበት” በአዲሱ አዋጅ ላይ ሰፍሯል።

ውሉ መመዝገብ እና መረጋገጥ ያለበት፤ በዛሬው ዕለት በጸደቀው አዋጅ መሰረት የሚቋቋመው “ተቆጣጣሪ አካል” በተሰየመ በ30 ቀናት ውስጥ እንደሆነ በአዋጁ ተቀምጧል። ሆኖም የመኖሪያ ቤት ኪራይን ውል እና ዋጋን እንዲቆጣጠር በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎች የሚመሰረተው አካል፤ የውል ማረጋገጫ እና የምዝገባ ጊዜውን እንዳስፈላጊነቱ እስከ ሶስት ወር ድረስ ሊያራዝም እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጓል።
በዚህ አካሄድ መሰረት የተመዘገበ “የኪራይ ውል ያለው ቤት” አሁን ያለው የኪራይ ዋጋ፤ “የቤቱ ኪራይ ዋጋ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚወሰድ” በአዋጁ ላይ ተመልክቷል። “አከራይ በነባር ተከራይ ወይም አዲስ ተከራይ ላይ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የሚችለው፤ ተቆጣጣሪው አካል ነባራዊ ሁኔታውን እያየ የሚወስነውን ጭማሪ መሰረት በማድረግ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል።
“ይህም አከራዮች እንደፈለጉ አላግባብ የሚያደርጉትን ጭማሪ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የኑሮው ሁኔታ ኪራይ ለመጨመር አስገዳጅ ሲሆን ተቆጣጣሪው አካል ከሚያስቀምጠው ጣሪያ ሳያልፉ መጨመር እንዲችሉ ዕድል የሚሰጥ ነው” ሲል ማብራሪያው ያክላል። የተቆጣጣሪው አካል በቤት ኪራይ ላይ የሚደረግን የዋጋ ጭማሪ ለህዝብ ይፋ የሚያደርገው በየዓመቱ “ሰኔ አንድ” መሆኑን አዋጁ ደንግጓል። በአዲሱ አዋጅ መሰረት፤ በዚህ መልክ የሚደረገው ጭማሪ “ከሰኔ 30 ጀምሮ ለአንድ ዓመት የጸና ይሆናል”።

በአዋጁ ከተዘረዘሩ ድንጋጌዎች ውስጥ “የመኖሪያ ቤት የኪራይ ውል ዘመንን” የሚመለከቱት የሚጠቀሱ ናቸው። “የመኖሪያ ቤት ኪራይ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ አይችልም” ሲል የደነገገው አዋጁ፤ ይህ የተደረገበትን ዋነኛ ምክንያት በማብራሪያው ላይ አስፍሯል። “የአዋጁ ዓላማ የመኖሪያ ቤት ኪራይ የተረጋጋ እንዲሆን ለማድረግ በመሆኑ፤ [ውሉ] ከሁለት ዓመት ያነሰ ቢሆን አከራዩ ውሉን ለማደስ ፍቃደኛ ላይሆን ስለሚችል፤ ተከራይ በየጊዜው በቀጣይ ስለሚከራየው ቤት በመጨነቅ የተረጋጋ ህይወት እንዳይመራ ያደርገዋል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ አትቷል።
“ከሁለት ዓመት ያለፈ ዘመን ይኑረው ቢባል ደግሞ የአከራይን መብት እንዳይጫን፤ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የውል ዘመኑ ከሁለት ዓመት ያላነሰ ጊዜ እንዲሆን” መደረጉን የአዋጁ ማብራሪያ አስገንዝቧል። “አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከሁለት ዓመት በታች የተደረጉ የቤት ኪራይ ውሎች ላይ ይህንን አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ ፍትሐዊ ስለማይሆን፤ በውላቸው ላይ ያጸደቁት ቤት ኪራይ የውል ዘመን ተቀባይነት እንዲያገኝ ተደርጓል” ሲልም ማብራሪያው አክሏል።
በሶስት የፓርላማ አባላት ድምጸ ተዐቅቦ የጸደቀው “የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ”፤ ለአከራይ የሚሰጡ ማበረታቻዎችንም ይዟል። አዲስ የመኖሪያ ቤት ሰርቶ ለኪራይ ያቀረበ አንድ አከራይ፤ በአዋጁ መሰረት ከሚወጡ “የቤት ኪራይ ዋጋ ጣሪያ ግዴታዎች” ለአራት ዓመታት ነጻ እንደሚሆን ተደንግጓል። እነዚህ ዓመታት የሚቆጠሩት፤ አከራይ የመጀመሪያውን የቤት ኪራይ ውል ካስመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ መሆኑን አዋጁ ጠቁሟል።

አንድ አከራይ “ነባር እና ተከራይቶ የማያውቅ የመኖሪያ ቤትን” ለኪራይ ካቀረበም፤ በተመሳሳይ መልኩ ማበረታቻዎች እንደሚደረጉለት በአዋጁ ተመላክቷል። እነዚህ መሰል አከራዮች የቤት ኪራይ ውላቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ካስመዘገበቡት ጊዜ ጀምሮ፤ በአዋጁ መሰረት ከሚወጡ የቤት ኪራይ ዋጋ ጣሪያ ግዴታዎች “ለሁለት ዓመት ነጻ ይሆናሉ”።
ሆኖም የመኖሪያ ቤትን ሳያከራዩ ያለ ምንም አገልግሎት ከአንድ ዓመት በላይ የሚያስቀመጡ የቤት ባለቤቶች ላይ፤ የቤቱ የንብረት ግብር ተመን 25 በመቶ የሚያህል ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስገድድ አሰራር ሊዘረጋ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። ይህ አሰራር በመመሪያ ተግባራዊ ሊያደርጉ እንዲችሉ አዋጁ የፈቀደላቸው፤ “ከፍተኛ የቤት እጥረት ያለባቸው” የከተማ አስተዳደሮችን ነው።
“ለስምንት ዓመታት ያህል ጥናት ሲደረግበት ነበር” የተባለለት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅ፤ ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 24፤ 2016 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባልተለመደ ሂደት ነው። የአዋጁ ረቂቅ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበረው ከቀናት አስቀድሞ ለፓርላማ አባላት እንዲሰራጭ አልተደረገም።
ይልቁንም የገዢው ፓርቲ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ዛሬ ጠዋት ተሰብስበው፤ አዋጁን በተመለከተ በፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና በከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ አማካኝነት ገለጻ እንደተደረገላቸው ሁለት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ የገለጻ እና ውይይት ወቅት ለተነሱ ጥያቄዎች፤ ከምሳ ሰዓት በኋላ በነበረው ክፍለ ጊዜ በሁለቱ ሚኒስትሮች እና አዋጁን ባዘጋጁ ባለሙያ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

ይህን ማብራሪያ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች፤ በመቅረጽ ድምጽም ሆነ በካሜራ እንዳይቀርጹ ተከልክለዋል። በዚህ ወቅት የአዋጁ ረቂቅ ሰነድም ለፓርላማ አባላት እንዲሰራጭ ተደርጓል። ማብራሪያው ካለቀ በኋላ መደበኛ ስብሰባውን ያከናወነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ አዋጁን አስመልክቶ በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የቀረበለትን “ሞሽን” አዳምጧል።
አቶ ተስፋዬ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት በዚሁ የውሳኔ ሃሳብ፤ ፓርላማው አዋጁን ያለ ሁለተኛ ንባብ በቀጥታ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል። የእርሳቸውን የውሳኔ ሃሳብ በመደገፍ ሁለት የፓርላማ አባላት አስተያየታቸውን ካስደመጡ በኋላ፤ የዛሬውን የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባን የታደሙ 244 አባላት በአዋጁ ላይ ድምጽ ሰጥተዋል። በስተመጨረሻም አዋጁ በሶስት ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
አዋጁ በዚህ መልክ የጸደቀው “ህጋዊ አካሄድን” ተከትሎ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል። የፓርላማው የህግ አወጣጥ ስነ ስርዓት “አንዳንድ ህጎች በመጀመሪያ ንባብ የሚጸድቁበትን አግባብ” ማመላከቱን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የቤት ኪራይ ውልን የሚመለከተው አዋጅ በዚህ አካሄድ እንዲታይ መደረጉን ተናግረዋል።
“[አዋጁን] ያለ አግባቡ ሰው ከተረዳው፣ ብዥታ ከተፈጠረ፣ በተጣመመ መንገድ ወደ ማህብረሰቡ ከወጣ፣ አሁን ያለውን የአከራይ ተከራይ ውል ያደፈርስና ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል”– ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ፤ የፍትህ ሚኒስትር
“[አዋጁን] ያለ አግባቡ ሰው ከተረዳው፣ ብዥታ ከተፈጠረ፣ በተጣመመ መንገድ ወደ ማህብረሰቡ ከወጣ፣ አሁን ያለውን የአከራይ ተከራይ ውል ያደፈርስና ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል። በተዛባ አሉባልታ ሰው ወደ ሌላ ነገር እንዳይገባ፣ ከአዋጁ ዓላማ የተቃረነ ውጤት እንዳይኖረው በመጀመሪያ ንባብ መጽደቁ የተሻለ ነው” ሲሉ ዶ/ር ጌዲዮን በማብራሪያቸው አስገንዝበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]