በትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በጦርነትና ድርቅ ሳቢያ ባኹኑ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነው እንደሚገኙ ዋዜማ ካሰባሰበችው መረጃ ተረድታለች።
የትግራይ ትምህርት ቢሮ፣ ከጦርነቱ በኋላ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳልተመለሱ ለዋዜማ ተናግሯል።
105 ትምህርት ቤቶች አኹንም የተፈናቃዮች መጠለያ እንደኾኑንና የክልሉ 88 በመቶ ትምህርት ቤቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ እንደወደሙ ቢሮው ተናግሯል።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም፣ በግጭቱ ሳቢያ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ገደማ ተማሪዎች ዘንድሮ ወደ ትምህርት ቤት እንዳልተመለሱ ገልጧል።
3 ሺሕ 500 የአንደኛና 225 የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስከ ዓመቱ አጋማሽ ዝግ ኾነው እንደቆዩና 300 ትምህርት ቤቶች በግጭቱ እንደወደሙም ቢሮው ጨምሮ ገልጧል።
የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፣ ዘንድሮው 131 ሺሕ 338 ተማሪዎች ከአንድ ሳምንት እስከ ወር የዘለቀ የትምህርት መቆራረጥ አጋጥሟቸዋል ብሏል። ዋዜማ