

ዜና ጁምዓና ከተራን ጨምሮ አራት ቀናት ሥራ ዝግ ሆኖ እንዲከበሩ ጥያቄ ቀረበ
ቀን: April 3, 2024
ጁምዓ፣ ከተራና ቃና ዘገሊላ የአደባባይ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች፣ እንዲሁም የካቲት 12 የሰማዕታት መታሰቢያ በዓላት ሥራ ዝግ ሆነው እንዲከበሩ በፓርላማ ጥያቄ ቀረበ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በተባባሪነት ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ የተመራውን፣ የሕዝብ በዓላትንና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ የሕዝብ ውይይት መድረክ ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲካሄድ፣ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ ምሁራንና ሌሎች ተቋማት ተሳትፈው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በመወከል የተገኙት ኡስታዝ አህመዲን ጀቢል፣ በእስልምና እምነት አንድ ሰው ሦስት ተከታታይ ጁምዓ ካልተገኘ በመናፍቅነት የሚያስፈርጅ ከባድ ጉዳይ በመሆኑ፣ ዓርብ (ጁምዓ) ቀን ሥራ ዝግ እንዲሆን፣ ወይም ደግሞ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ከአምስት ሰዓት ተኩል እስከ ሰባት ሰዓት ተኩል በአዋጁ መካተት አለበት ብለዋል፡፡
ሃይማኖታዊ በዓል የሚለው አገላለጽ በሙስሊሞች ከሆነ ዓመታዊና ሳምንታዊ በዓላት በመኖራቸው፣ ዓመታዊ የሚባሉት በአዋጁ የተጠቀሱት የኢድ አልአድሃ (አረፋ) በዓል፣ የመውሊድና የኢድ አልፈጥር በዓል ሲሆኑ፣ ሳምንታዊው ደግሞ ጁምዓ መሆኑ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡
አዋጁ የበዓላት አከባበርን ሃይማኖታዊ፣ ብሔራዊና ታስበው የሚውሉ በማለት በዝርዝር የጠቀሰ ቢሆንም፣ በዓላቱ የሚከበሩበትን የተለየ ቀን ገልፆ የሙስሊም በዓላትን ግን አልገለጸም ብለዋል፡፡
‹‹በአዋጁ መስከረም 1 እና 17፣ እንዲሁም ሚያዚያ 27 እየተባለ ሲጠቀስ፣ የእስልምና በዓላትን ለመጥቀስ የተቸገረበት ምክንያት፣ የሙስሊም በዓላት የሚከበሩበት ቀን በኢትዮጵያውያን ካላንደር በጨረቃ ከታየ ወይም ካልታየ በሚል ብዥታ ስለሚፈጥር በመሆኑ፣ አዋጁ መላ ኢትዮጵያውያን የሚገለገሉበት እንዲሆን ከተፈለገ የሂጂራ ካላንደር አቆጣጠርን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኡስታዝ አህመዲን አክለውም፣ በአዋጁ የመጀመሪያውና የመጨረሻ ገጽ ላይ የተቀመጠው ቀን ዓመተ ምሕረት (ዓ.ም.) ሙስሊሞችን የማይመለከት በመሆኑ፣ የሙስሊም ካላንደር አብሮ ገብቶ በዓሉ ሲጠቀስ በሂጂራ በተቀመጠው ቀን መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በአዋጁ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያሪክ የሕግ መምርያ ኃላፊ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ጌትነት፣ እየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ባህረ ዮርዳኖስ ሄዶ መጠመቁን የሚያሳየው የቃል ኪዳኑን ታቦት በመያዝ ጥር 10 ቀን የሚከበረው ከተራና ከጥምቀት በኋላ ጥር 12 ቀን የሚከበረው ቃና ዘገሊላ ክብረ በዓላት ከሥራ ዝግ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ሠራተኞች የከተራ በዓል ከሰዓት በኋላ ሲከበር ግልጽ መብት ካልተሰጣቸው በስተቀር፣ ሥራውን ትተው ቢሄዱና በመሥሪያ ቤት ስለሚፈጠረው አለመግባባት ኃላፊነት የሚወስደው አካል በግልጽ መቀመጥ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ታስቦ ከመዋል ይልቅ ከሥራ ዝግ ሆኖ መከበር ይገባዋል ያሉት ደግሞ፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
‹‹የካቲት 12 ቀን ከደርግ ዘመነ መንግሥት በፊት ቀኑ ዝግ ሆኖ ይከበር የነበረ ሲሆን፣ በ1967 ዓ.ም. የደርግ መንግሥት ሲቋቋም በዓላትን እንደ አዲስ በረቂቅ በማቅረቡ፣ በወቅቱ የነበሩት የአርበኞች ማኅበር አመራሮች ተጠርተው ቀኑ ከሥራ ዝግ መሆኑ ቀርቶ እየታሰበ እንዲውል ከተነገራቸው በኋላ፣ በወቅቱ ፍርኃትም ስለነበር ወዲያውኑ ታስቦ እንዲውል ተደርጓል፤›› ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘር፣ ፆታ፣ ዕድሜ ሳይለይ በአዲስ አበባ ጥቁር ማቅ የተለበሰበት በመሆኑ፣ ቀኑን ከሥራ ዝግ በማድረግ ተከብሮ መዋል አለበት ሲሉ አበባው (ረዳት ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡
ከላይ በተጠቀሱት ሦስት ተቋማት የተነሱትን የሥራ ዝግ መደረግ ጥያቄን በተመለከተ በፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉት አቶ ጠገነኝ ትርፌ፣ ‹‹ጁምዓ፣ ከተራና ሌሎች አዳዲስ በዓላት ሥራ ተዘግቶ የሚውሉበትን ቀን ባበዛን ቁጥር፣ የሥራ ቀናትን ማጣበብና ድህነትን ለመታገል ችግር ይፈጥራል፤›› ብለው ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊና ከባህል አኳያ ሊያመጡት የሚችሉት ፋይዳ ታይቶ ቋሚ ኮሚቴው ይመለከተዋል ብለዋል፡፡
‹‹አዋጁ በዓላትንና አከባበራቸውን ለመወሰን የወጣና የእረፍት ቀናትን በተመለከተ የራሱ ማዕቀፍ ያለው ቢሆንም፣ እንደ አገር የራሳችን መዳረሻ ዓላማ ያለን በመሆኑ በጋራ ሊያስተሳስሩን የሚችሉ እሴቶችን አስጠብቆ፣ አዳዲስም ካሉ የጋራ ዓላማ የሚሰንቅ መሆን አለበት፤›› ሲሉ የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር አቶ አዲስ ጌትነት ገልጸዋል፡፡
አዋጁ መሠረት ያደረገው በዋናነት በዓላትን ዕውቅና መስጠትና አከባበር ላይ እንጂ፣ የእረፍት ቀን መሰየም አለመሆኑ ታሳቢ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በኡስታዝ አህመዲን የተነሳው አዋጁ ውስጥ ‹ዓ.ም.› የሚለውን በተመለከተ፣ በአዋጁ የተገለጸው የዘመን አቆጣጠር አገሪቱ እየተከተለች ያለውን በመሆኑ ነው እንጂ የእስልምና እምነት አቆጣጠርን ችላ ተብሎ አይደለም ብለዋል፡፡
መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ባቀረቡት ተጨማሪ ሐሳብ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጎችን ሲያወጣ ቤተ እምነቶችን የማሳተፍ ግዴታ እንዳለበት፣ ቤተ እምነቶችም በሁሉም አዋጆች ላይ ሐሳባቸውን ቢሰጡ ይጠቅማሉ እንጂ አይጎዱም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሕግ ማውጣት ችግር የሌለባት አገር ብትሆንም ሕግ ከወጣ በኋላ ሁሌም እንደሚሻሻል፣ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከዜጎች ግብዓት ስለማይወሰድ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት የመንግሥት የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን የፀጥታና የደኅንነት ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው በረቂቅ አዋጁ መኖሩን፣ ነገር ለሌሎች በዓላት ለምን የፀጥታ ጥበቃ አይደረግም በማለትና ማናቸውንም በዓላት የመጠበቅ ኃላፊነት በሚል በረቂቅ አዋጁ መስተካከል አለበት ሲሉ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ አሳስበዋል፡፡
አበባው (ረዳት ፕሮፌሰር) ጥቅምት 15 ቀን የመከላከያ (የሠራዊት) ቀን አዲስ በፀደቀው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም፣ ቀኑ ታስቦ እንዲውል በማድረግ የጀግኖች ቀን መኖር አለበት ብለዋል፡፡
በተለያዩ ወቅቶች ጀግና የነበሩና ስማቸው የማይታወቁ ያልተዘመረላቸው ሰዎች፣ አካላቸው የጎደለ፣ ሕይወታቸውን የሰጡ፣ በተለያየ መንገድ ለአገር በውትድርና አስተዋጽኦ ያደረጉ የሚታሰቡበት ቀን ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጤና፣ የማኅበራዊ ልማት፣ የባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ወርቀሰሙ ማሞ፣ ረቂቅ አዋጁ ኢትዮጵያውያንን እንዲመስል ዘላቂነት ያለው ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የተሰጡ አስተያየቶችም ረቂቅ አዋጁን ለማጎልበት እንደሚያግዙ ገልጸው፣ የመንግሥት ተቋማት ገለልተኛ ሆነው የተጣለባቸውን ሕዝብን የማገልገል ኃላፊነት ብቻ እንዲወጡ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።