
April 3, 2024
እ.ኤ.አ. መስከረም 2020 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ንግግር ያደረጉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አንድ ቃል ገቡ፡፡ የዚያን ጊዜ ገና ወደ ሥልጣን ከመጡ ሁለተኛ ዓመታቸው ነበር፡፡ ‹‹ባለፉት ሁለት ዓመታት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት የምንችለውን ያህል ጥረት አድርገናል፡፡ የዴሞክራሲ መብቶችና የሰብዓዊ መብቶችን አከባበር ለማሻሻል እየሠራን እንገኛለን፡፡ ይህ ሥራ ቀላልና አልጋ በአልጋ እንደማይሆን እንገነዘባለን፡፡ ይልቁንም ከባድ ፈተና እንደሚገጥመን እናውቃለን፡፡ ይሁን እንጂ የፈለገ ፈተናው ቢበዛ ጥረታችንን ለመቀጠልና በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ለማምጣት ከፍተኛ ቁርጠኝነቱ አለን፡፡ ሰላማዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማድረግም ቁርጠኛ ነን፤›› በማለት ነበር የተናገሩት፡፡

ይህ የዓብይ (ዶ/ር) ንግግር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊት ኢትዮጵያን ለማሸጋገር የተገባ ቃል ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ በአሜሪካ በተለይ በዋሽንግተንና በዙሪያዋ ካሉ የዳያስፖራ አባላት ጋር ሲነጋገሩም ስለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቃል ገብተው ነበር፡፡ ‹‹የሽግግር ሒደት፣ ሽግግር፣ ሽግግር፣ የሚባለው አንዴ ከተቀመጡ መነሳት የማይፈልጉ ሰዎች ስላስቸገሯችሁ የምታነሱት ጥያቄ እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ሽግግርን በሚመለከት ችግር የለም እኔ አሻግርላችኋለሁ፤›› በማለት ነበር ለዳያስፖራው ቃል የገቡት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሒደቶች ለኢትዮጵያውያንም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቃል ከገቡ እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ቃል በገቡት መሠረት ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ መከናወኑን የሚጠራጠሩ ዛሬም በርካታ ናቸው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በአንድ የፓርላማ ቆይታቸው ወቅት ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ ከደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የሽግግር ጉዳይ ጥያቄ ተነስቶላቸው ነበር፡፡ ‹‹አሁንም ኢትዮጵያን አሻግራለሁ ይላሉ? ወይስ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ሒደት ለመፍጠር ያስባሉ?›› የሚል ይዘት ያለው ጥያቄ ነበር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹የሽግግር ሒደቱ እኮ እስከ ምርጫው ጊዜ ድረስ የነበረው ነበር፡፡ አሁንማ እሱ አልፎ በምርጫ የሕዝብ ድምፅ ያገኘ መንግሥት ተመሥርቷል እኮ፡፡ ይህ መንግሥት ደግሞ ለአምስት ዓመት እየመራ ይቀጥላል፡፡ ሌላ የሽግግር መንግሥት ባንጠብቅ ጥሩ ነው፤›› የሚል ይዘት ያለው ማብራሪያ ሰጥተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ከተባለም በኋላ ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያን ወዴት አሻገሯት የሚለው ጥያቄ እስካሁንም ይነሳል፡፡ ከትናንት በስቲያ በቤተ መንግሥታቸው ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ባለፉት ዓመታት የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ቃል እንደተገባው ከመስፋት ይልቅ፣ እየጠበበ ሄዷል የሚለው ጥያቄ በአሳሳቢነት እንደተነሳላቸው ታውቋል፡፡
ይህንኑ የተመለከተ ጥያቄ በውይይት መድረኩ ያነሱት የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋና ጸሐፊና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ደስታ ጥላሁን፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩ ጠቧል የሚለውን ማንሳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሚዲያ ነፃነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና የመብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ መገደብ ጀምሮ ሲቪክ ምኅዳሩ ያጋጠሙትን ፈተናዎች የተመለከተ ጥያቄ አንስቼላቸው ነበር፡፡ ይህን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የሲቪክ ምኅዳሩ በጣም መስፋቱም ሆነ በጣም መጥበቡ ጥሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል፤›› በማለት ፖለቲከኛዋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ከባቢ አየር ዙሪያ ጠቃሚ የግማሽ ቀን ውይይት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መደረጉን ወ/ሮ ደስታ ገልጸዋል፡፡ ይህን መሰሉ ውይይት ቢያንስ በየአራት ወሩ እንደሚካሄድ ቃል መገባቱንም አመልክተዋል፡፡ ይህ ገንቢ ስለመሆኑ ቢነገርም ከዚህ ቀደም የተገቡት ቃሎች በፖለቲካው ምኅዳር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዳላመጡት ሁሉ፣ የአሁኑም የፖለቲከኞች ምክክር ከዚህ የተለየ ውጤት እንደማይኖረው አንዳንዶች በቀቢፀ ተስፋ ተመልክተውታል፡፡
ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከሦስት ያላነሱ የፖለቲካ ድርጅቶች (አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ ኦነግ፣ ኦብነግ) ከሽብር መዝገቦች እንዲፋቁ ተደርጎ ነበር፡፡ በውጭ አገሮች መሽገው በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩ ድርጅቶች በነፃነት ወደ አገራቸው ገብተው በሰላም እንዲታገሉ መፍቀዳቸውም አይዘነጋም፡፡ ወደ 250 ሚዲያዎችና የኢንተርኔት ገጾች ከመታፈን ነፃ እንዲወጡ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ በዴሞክራሲ ምኅዳር የተንበሸበሸች አገር ይፈጥራሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ፈንጥቀውም ነበር፡፡
ተቋማትን ለማዘመንና አሠራራቸውን ለማሻሻል ፈጥነው የጀመሯቸው ሥራዎች በኢትዮጵያ የአስተዳደር በደል፣ ብልሹ አሠራርና ምዝበራን በእጅጉ የሚያስወግዱ መሆኑ ታምኖበት ነበር፡፡ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱ ማሻሻያዎች እስከ አስፈሪው የፀረ ሽብር ሕጉ ማሻሻያ ድረስ የሚደርሱ ናቸው መባሉ ኢትዮጵያ ፍትሕና ርትዕ የሚገኝባት ምድር ልትሆን ነው የሚል ምኞትንም ፈጥሮ ነበር፡፡
በምርጫ ቦርድ በኩል የተደረገው ሪፎርም ደግሞ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ በአገሪቱ ለማካሄድ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ታምኖበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ በነበሩ ወራት የታዩ በጎ ለውጦችና ሪፎርሞች በታሰበው ልክ መጓዛቸውን የሚጠራጠሩ አሉ፡፡
አንዳንድ ወገኖች ከዴሞክራሲያዊ ሽግግር ተስፋው ይልቅ የፖለቲካው ቀውስና ምስቅልቅሉ ጎልቶ እንደሚታያቸው ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከተሠራው በጎ ሥራ ይልቅ የፈረሰው እንደሚበዛ ያስረዳሉ፡፡ ለውጡ ወደ ነውጥነት ተቀየረ ሲሉም ይፈርጁታል፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ጭርሱኑ ተፈጥሮ የነበረው የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ብልጭታም ሆነ የሽግግር ተስፋ መጨንገፉን በተስፋ መቁረጥ ይናገራሉ፡፡
የቀድሞ የኢሕአፓ አባልና አንጋፋ ፖለቲከኛ መላኩ ተገኝ (ዶ/ር) በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር በቅርብ ጊዜ ዕውን የሚሆን ይመስልዎታል ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡ ‹‹አሁን ከዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይልቅ የአገሪቱ ህልውና ራሱ ተጠብቆ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች ወይ የሚለው ነው ለእኔ አሳሳቢው ጉዳይ፤›› ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ የሥጋት ደረጃቸው ይለያያል እንጂ ልክ እንደ እሳቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ከመጣው የዴሞክራሲ ለውጥ ተስፋ ይልቅ የአገር ህልውና አደጋው ገዝፎ የሚታያቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም፡፡
በቡራዩ፣ በጌዴኦ፣ በሐዋሳ፣ በሻሸመኔ፣ በአጣዬ፣ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ ወዘተ እያለ ያለማቋረጥ የደረሰው የግጭትና ቀውስ አዙሪት ተስፋ ያስቆረጣቸው መኖራቸው አይካድም፡፡ የጃዋር መሐመድ ቤት ተከበበ መባልን ተከትሎ በኦሮሚያ የደረሰው ደም አፋሳሽ ብጥብጥ በቀላሉ አይረሳም፡፡ የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ የተከሰተው ጭፍጨፋና ጥቃት ደግሞ ሁኔታውን የበለጠ አወሳስቦታል ይባላል፡፡
በሌላ በኩል የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር ገና ወደ ሥልጣን እንደመጣ በጅግጅጋና በተለያዩ የሶማሌ ክልል ከተሞች የቀድሞው የክልሉ አስተዳደር ያስነሳው ሁከትና ብጥብጥ በእጅጉ ፈትኖት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል ተከሰተ የተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ብዙ ደም መፋሰስ መፍጠሩ አስተዳደሩን በከባዱ አስቸግሮት ነበር፡፡
አዲሱ መንግሥት ከእነዚህ ፈተናዎች በተጨማሪም በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳዕረ መኮንን፣ በታላቁ ህዳሴ ግድብ መሐንዲስ ስመኘው በቀለ (ኢንጂነር) ሞትና በሰኔ ስድስቱ የቦምብ አደጋ በመሳሰሉ አጋጣሚዎች በውስብስብ የፖለቲካ ሴራዎች ሲደናቀፍ ማለፉን የሚያነሱም አልጠፉም፡፡
ይሁን እንጂ በመንግሥትና በደጋፊዎቹ ወገን ባለፉት ስድስት ዓመታት አገሪቱ ያለፈችበት መንገድ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ሁኔታ ነው ሲቀርብ የሚታየው፡፡ በቅርቡ የታተመው ‹‹የአዲስ ወግ መድረኮች ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም.›› በሚል ርዕስ የቀረበው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መጽሐፍ የተለያዩ አሳታፊ የውይይት መድረኮችን መንግሥት ስለመፍጠሩና ገንቢ ውጤትም ስለመምጣቱ ይዘረዝራል፡፡
‹‹በ2010 የመጣው የለውጡ መንግሥት የሐሳብ ብልጫ ለማንኛውም አወዛጋቢ የሆኑ ጉዳዮች ፍቱን እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት አመላክቷል፡፡ በፖለቲካ ምኅዳሩ ተለምዶ በማያውቅ መልኩ ለውይይትና ለሐሳብ ክፍት መሆኑን ያሳየው የለውጡ መንግሥት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረኮችን ለሕዝብ ዕይታ ክፍት በማድረግ አስተናግዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ወንድም ወንድሙን ገፍቶ አያሸንፍም፡፡ ተቃቅፈን፣ ተባብረን በሐሳብ ብቻ በመሸናነፍ መጓዙ ይበጃል ብለው እንደተናገሩት ሁሉ በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መንግሥት የውይይት መድረኮችን አዘጋጅቷል፤›› በማለት መጽሐፉ በመቅድሙ ላይ አሥፍሯል፡፡
ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት የተካሄዱ የአዲስ ወግ የውይይት መድረኮችም፣ ከዚህ አንፃር በአገሪቱ ‹‹የውይይት ባህልና የሐሳብ የበላይነት የሚያዳብሩ›› ናቸው ይላል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ተቃርኗዊ እሳቤዎችን ለማቀራረብ፣ የሐሳብ ብዝኃነትን ለማዳበር ብቻ ሳይሆን ለነባርና አዳዲስ ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግም የረዱ ስለመሆናቸው በሰፊው ያብራራል፡፡
ይሁን እንጂ መንግሥት ብዙዎች እንደጠበቁት የሽግግር ሒደትን የሚመራ ሁሉን አቃፊ የሽግግር አስተዳደር ሲፈጥር አልታየም፡፡ መንግሥት በብዙ ወገኖች ቢወተወትም የሽግግር ሒደቱ የሚመራበት ራሱን የቻለ ፍኖተ ካርታ (ሮድማፕ) አላዘጋጀም፡፡ ያም ቢሆን ግን ለውጡን የተሳካ ለማድረግ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ማስተናገዱን መንግሥት ይገልጻል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ በየክልሉ እየዞሩ ሕዝብ ማወያየታቸው በጊዜው የመጣውን ለውጥ በተሻለ መንገድ እንዲጓዝ ያደርገዋል የሚል ሰፊ ግምት ያሳደረ ነበር፡፡ ሕዝብ ማወያየቱም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የውይይት መድረክ መፍጠሩ ግን በተጨባጭ መሬት ላይ የወረደ ለውጥ አላመጣም የሚለው ሐሳብ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
የታሪክ ምሁሩ ህዝቅኤል ጋቢሳ (ፕሮፌሰር) ለውጡ በመጣ ሰሞን ስለዴሞክራሲያዊ ሽግግር አስተዳደር ‹‹Managing Political Transition in Ethiopia the Choice Factor›› በሚል ርዕስ ያስነበቡት ሀተታ፣ ዛሬም ድረስ ብዙዎች እንደ ምሳሌ ያነሱታል፡፡ በተለያዩ እርከኖች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በለውጡ የመጀመሪያ ሰሞን ውይይቶች በርክተው ቢታዩም፣ ዋናውን ‹‹ለውጡን እንዴት በቅጡ እንምራው?›› የሚለው ጉዳይ ግን በቂ የውይይት ትኩረት ሳይገኝ የለውጡ ጊዜ መክነፍ እንደጀመረ ብዙዎች በቁጭት ያነሳሉ፡፡
ህዝቅኤል (ፕሮፌሰር) በትንተናቸው እንዳነሱት እ.ኤ.አ. ከ1974 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት 30 የዓለም አገሮች ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ተሸጋግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ወደ 36 አገሮች ወደ አምባገነናዊ ሥርዓት መሸጋገራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ልምድ በመነሳት አገሮች ወደ ዴሞክራሲ ከመሄድ ይልቅ ወደ አምባገነናዊነት የሚሸጋገሩበት ዕድል በዓለማችን የሰፋ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህን ዋቢ በማድረግም ኢትዮጵያ ለውጡን በቅጡ ማስተዳደር ካልቻለች ተመሳሳይ ዕጣ እንደሚጠብቃት ተንብየው ነበር፡፡ ‹‹በለውጥ ወይ በሽግግር ወቅት የሒደቱን ስኬት ከሚበይኑ ነገሮች አንዱ ቁልፍ ጉዳይ በሽግግሩ የሚሳተፉ ኃይሎች የፖለቲካ አሠላለፍ ነው፤›› የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ በኢትዮጵያ በመጣው ለውጥም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ገንቢ ሚና ካልተጫወቱ ለውጡ እንደሚጨነግፍ አስቀምጠው ነበር፡፡
ይህ ትንተና እንዳብራራው ከሆነ የለውጥ ሒደት መጨንገፍ (አለመሳካት) አምባገነናዊነትን ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም የቀየጠ ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ‹‹Permanently Stalled Democratic Transitions as Semi-authoritarian›› ሲል ትንተናው እንደበየነው ወደ ዴሞክራሲ የማይሸጋገርና ጨርሶ አምባገነናዊ ያልሆነ ‹‹ቆሞ ቀር›› የፖለቲካ ሥርዓት ሊፈጠር እንደሚችል በምሳሌ ተብራርቶ ተቀምጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም (ዶ/ር) ቢሆኑ፣ ‹‹መንግሥት አንዳንዴ ተገዶ ወደ አምባገነናዊነት ይቀየራል፤›› ሲሉ በተደጋጋሚ ጊዜ መናገራቸው ለውጡ ሊገጥመው የሚችለውን ፈተናና መሰናክል ቀድሞ በመረዳት የሰጡት ግምት እንደሆነ በሰፊው ይወሳል፡፡ የዓብይ አስተዳደር በመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ወራት የወሰዳቸው ከሞላ ጎደል በብዙዎች ዘንድ በበጎ የሚታዩ የለውጥ ዕርምጃዎች በተቃራኒው በአንዳንዶች ዘንድ አሉታዊ ምላሽ ይገጥማቸው ነበር፡፡ ይህ መሰናክል ደግሞ መንግሥትን ወደ ተስፋ መቁረጥ እንደወሰደው ይነገራል፡፡
ለውጡ በመጣበት የመጀመሪያ ሰሞናት ‹‹የለውጡ እንቅፋቶች ከራሱ ከገዥው ፖለቲካ መደብ የወጡ ኃይሎች ናቸው›› ሲሉ አንዳንዶች እንደገመቱት ሁሉ፣ ከመንግሥት የተገነጠሉ ኃይሎች ዋነኞቹ የለውጡ ሒደት ተቃዋሚዎች ሆነው መነሳታቸውን የሚናገሩ አሉ፡፡
ይህ ለውጡን በቅጡ ለመምራትና ውጤታማ የሽግግር ሒደት ለመፍጠር ከተደረገው ደካማ ዝግጅት ጋር ተዳምሮ አገሪቱን ወደ ቀውስ እንደከተታት ብዙዎች በቁጭት ያነሳሉ፡፡ የምጣኔ ሀብት ሪፎርም፣ የፍትሕ ሥርዓትና የተቋማት ግንባታ ሪፎርም፣ የግብርና ዘርፍ ሪፎርም፣ የሎጅስቲክስ ዘርፍ ሪፎርም፣ የአገረ መንግሥት ግንባታና ብሔራዊ መግባባት እየተባሉ በተከታታይ ይቀርቡ የነበሩ የሪፎርም አጀንዳዎችን ግጭትና የፖለቲካ ውዝግብ ጉዳይ ጥላ እንዳጠላባቸው፣ መደመር፣ ይቅርታና ዕርቅ፣ ግንቡን አናፍርስ ድልድዩን እንገንባ፣ አረንጓዴ ልማት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወዘተ፣ የሚሉ ሁሉንም ሊያግባቡና ሊያሰባስቡ ይችሉ የነበሩ አጀንዳዎች መወዛገቢያ ሐሳቦች ሲሆኑ ታይቷል፡፡
ከለውጡ ሁለት ዓመታት መቆጠር በኋላ በነበሩት ጊዜያት ደግሞ የፖለቲካ ቅራኔዎች በእጅጉ እየሰፉ መጥተዋል፡፡ የምርጫ ማከናወኛ የጊዜ ሰሌዳን የተመረኮዘው ውዝግብ ከቀዳሚዎቹ እንደ አንዱ ይነሳል፡፡ በሚዲያ ጥላቻ መወራወሩ መጨመሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ በትግራይ ክልል ለአሰቃቂው ጦርነት መጀመር እርሾ ሆናል፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት ለውጥን መናፈቅ ወይም ዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ተስፋ ማድረግ በብዙዎች ግምት ቅንጦት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት መጀመር በኋላ ከሪፎርም (ለውጥ) አጀንዳዎች ይልቅ የአገሪቱ ህልውና ተጠብቆ መዝለቅ አንገብጋቢው አጀንዳ ሆኗል የሚሉ እየበዙ ነው፡፡