ማኅበራዊ
ከሥነ ተዋልዶ ጤና መብት ጋር የተቆራኘው የኦቲዝም ወር

የማነ ብርሃኑ

ቀን: April 3, 2024

የኦቲዝምና ተዛማጅ ችግር ያለባቸው ሰዎች መሠረታዊ መብትና ነፃነታቸው እንዲጠበቅ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድም ትኩረት እንዲያገኙ ለማስቻል በየዓመቱ የኦቲዝም ቀን በዓለም ደረጃ እንዲከበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2007 መወሰኑ የሚታወቅ ነው፡፡

በዚሁ መሠረት ‹‹ድምፅ አልባ የኦቲዝም ልጆችን ማብቃት›› (Empowering Autism Voices) በሚል መሪ ቃል፣ የኦቲዝም ወር በኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል እየተከበረ ይገኛል፡፡

ከሥነ ተዋልዶ ጤና መብት ጋር የተቆራኘው የኦቲዝም ወር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኒያ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ እሌኒ ዳምጠው

‹‹የሥነ ተዋልዶ ጤና መብት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ፅንስ የማቋረጥና ፆታዊ ጥቃት ከኦቲዝም አንፃር›› በሚል ሐሳብ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በተደረገ ዓውደ ጥናት ላይ የጤና ሚኒስቴር ተወካይ ጎበና ጎዳና (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የኦቲዝም ቀን መከበሩ ኦቲዝምና ተዛማጅ እክል ያለባቸውን ሰዎች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው እንቅፋት የሚሆኑባቸውን ተግዳሮቶች ለመቀነስና አካታችና እኩል ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ለማስቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

ጤና ሚኒስቴር የኅብረተሰቡን ጤና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽፋን እንዲኖረው በታለመው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከእንቅስቃሴዎቹ መካከልም ኦቲዝምና ተዛማጅ የአዕምሮ ዕድገት እክል ጉዳዮችና የአወላለድ እንከን (የበርዝ ዲፌክት) ራሱን በቻለ መዋቅር እንዲመራ፣ በሜዲካል ሰርቪስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በስፔሻሊቲና ሪሀብሊቴሽን ፎስክ ደረጃ እንዲደራጅ በመደረግ ላይ ነው፡፡

በተለይም ከኒያ ፋውንዴሽን ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ባለፉት ዓመታት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን በተናገሩት ተወካዩ አገላለጽ፣ የኦቲዝምን ችግር ከጤና ሚኒስቴር ዕቅድ ውስጥ ለማካተት የሚያስችል የዕቅድ ማናበብ ሥራ ሌሎችም መሰል ድርጅቶች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡

ሚኒስቴሩ በተለይም ከኒያ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን የኦቲዝም ቀንን በማስመልከት፣ ግንዛቤው ብዙም ባልሰፋባቸው ክልሎች በኦሮሚያ ክልል ጅማ፣ በትግራይ ክልል መቀለ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ሶዶ እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የማስገንዘቢያ መድረኮችን ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ነው፡፡

በበለፀጉና ባደጉ አገሮች የኦቲዝምና ተዛማጅ እክል ያለባቸው ሰዎች መሠረታዊ መብትና ነፃነት ተረጋግጧል፡፡ የትምህርት፣ ሥልጠናና የማገገሚያ አገልግሎቶች ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፉ በመሆናቸው አመርቂ ውጤቶች ተመዝግቦባቸዋል፡፡

እንደ ጎበና (ዶ/ር)፣ በአገሪቱ ከዚህ አንፃር የሚታዩ ጉድለቶችን ለማሻሻል የሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በአትኩሮት መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ዓላማ መሳካትና ለተግባራዊነቱ እያንዳንዱ ዜጋ የበከሉን ኃላፊነት በመወጣት የእነዚህን ድምፅ አልባ ዜጎች መብትና ደኅንነት ለማረጋገጥና ተጠቃሚ ለማድረግ መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኒያ ፋውንዴሽን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ እሌኒ ዳምጠው እንደተናገሩት፣ ዘንድሮ የኦቲዝም ቀንን ስናከብር የኦቲዝም ተጠቂ ወጣቶችን የሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ትኩረት በመስጠት ሊሆን ይገባል፡፡

ኒያ ፋውንዴሽን አገልግሎት ሲጀምር፣ የኦቲዝም ልጆች ‹‹ቤት ታፍነው አይቀመጡ፣ ተደብቀው መኖር የለባቸውም፤›› የሚል አቋም ይዞ የተነሳና ይህንንም ዓላማውን ሌሎች እንደ አርዓያ ተከትለው በርካታ ድርጅቶች በኦቲዝም ላይ እንዲሠሩና የተወሰነ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል፡፡

እንደ ወ/ሮ እሌኒ፣ በማዕከሉ ላሉ ልጆችና ቤተሰቦች ከኦቲዝም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግር ከሥነ ተዋልዶ ጤና አንፃር ነው፡፡ የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ልጆች ሐሳባቸውን አደራጅተው መግለጽ የማይችሉ፣ የማይናገሩና የማይሰሙ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ እንደ አስገድዶ መደፈር ላሉ ፆታዊ ጥቃቶች ተጋላጭ ናቸው፡፡

ኒያ ፋውንዴሽንም ይህንን ችግር በመረዳት የሥነ ተዋልዶ ጤና መብት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት ፅንስ ማቋረጥና ፆታዊ ጥቃትን ከኦቲዝም አንፃር የችግሩ ስፋት ምን እንደሚመስል ለማሳየትና በጉዳዩ ላይም የመፍትሔ ሐሳብ ለማስቀመጥ ከጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ዓውደ ጥናቱን ሊያዘጋጅ ችሏል ብለዋል፡፡