
April 3, 2024

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአገሪቱ ከሚንቀሳቀሱ ከተለያዩ የሴት አደረጃጀቶችና ማኅበራት ጋር በመጣመር አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አገራዊው የሴቶች ንቅናቄ የሴቶችን የፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ፣ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ሴቶች በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችልና በጋራ በመጮኸ ለሴቷ ድምፅ ለመሆን የታቀደ ነው፡፡ ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከምሥረታው ጀምሮ ባከናወናቸው ተግባራትና ስለታቀደው አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ መድረክ የማነ ብርሃኑ የድርጅቱን መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ተስፋነሽ በላይን (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያን ለማቆም መነሻው ምንድነው?
ተስፋነሽ (ዶ/ር)፡- ድርጅታችን በወጣቶች ጤናና ሥነ ተዋልዶ፣ በፆታ እኩልነትና የሴቶችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በሚያቀሉ ተግባራት ላይ በመሳተፍ ለውጥ ለማምጣት እ.ኤ.አ. በ2011 የተቋቋመ ነው፡፡ በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና የሕፃናት ጤና መምሪያ ኃላፊ ሆኜ በምሠራበት ወቅት በሴቶች ጤናና እንደ አጠቃላይ በሴቶች ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን በመመልከቴ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የድርሻዬን ለማበርከት ነው ድርጅቱን ያቋቋምኩት፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ በሴቶች ጤናና ማኅበራዊ ችግሮቻቸውን በማቃለል ዙሪያ የሠራቸው ሥራዎች ምን ይመስላሉ?
ተስፋነሽ (ዶ/ር)፡- ፓሽኔት በአፋር ክልል፣ ኮሪ፣ ኤልዳር፣ አፋምቦ፣ አሳይታ በተባሉ አካባቢዎች በቤተሰብ ዕቅድና በሥነ ተዋልዶ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በተጨማሪም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ከጤና ጣቢያዎቹ ጋር በማስተሳሰር ታች ማኅበረሰቡ ዘንድ የወረደ የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን አድርገናል፡፡ በትግራይ ክልል በአዲግራት፣ በሀዛባ፣ ፀአዳትና ሃዋይ በተባሉ ቦታዎች ‹በአካባቢ ጤና የሴቶች ሚና› በሚል ከፋርም አፍሪካ እና ከስዊድኑ ሲዳ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የንቅናቄ የሠራነው ሥራ ሠርተናል፡፡ በዚህም፣ የአካባቢው ሴቶች በመስኖ ሥራ ተሳታፊ በመሆን የጓሮ አትክልቶችን በማልማት ቤተሰቦቻቸውን ከመመገብ ባሻገር ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡ በዶሮና በበግ ዕርባታ በመሰማራት ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ በማድረግ በኩል ድርጅታችን በሰፊው ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም የተገኘው ውጤት አስደሳች ነበር፡፡ የተራቆቱ መሬቶችን ከሰውና ከእንስሳ ንክኪ ነፃ እንዲሆኑ በመከላከልና ችግኝ በመትከል መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ሠርተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው በአፋርና በትግራይ ክልል ብቻ ነው ወይስ በሌሎችም ክልሎች ትንቀሳቀሳላችሁ?
ተስፋነሽ (ዶ/ር)፡- ድርጅታችን በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለመሥራት ፈቃድ አለው፡፡ ከዚህ ቀደም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች መድኃኒት አከፋፍለናል፡፡ እናቶች በሚወልዱበት ጊዜ ደም እንዳይፈሳቸው እና ውርጃ ሲከሰት ምን ማድረግ እንደሚገባ በሕክምና ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሴት ማኅበራትን በማደራጀትና በማጠናከር በኩልም ድርጅታችን ሰፊ ሥራ ሠርቷል፡፡ በተለይም መልካም ቤተሰብን ከመፍጠር አንፃር፣ በትዳር ለረጅም ዓመታት የኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመጋበዝ ለወጣቶች አርዓያና ምሳሌ እንዲሆኑና ልምዳቸውን እንዲያስፋፉ አድርገናል፡፡ ሌላው ለነጋዴ ሴቶች የኮምፒዩተር ሥልጠና በመስጠት ንግዳቸውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ እንዲያዘምኑና ግብይታቸውን እንዲያሳልጡ የአቅም ግንባታ ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በአሌልቱ፣ ሸኖና ቅምብቢት ወረዳ የኤች አይቪ ሥርጭትን ለመከላከልና ለመግታት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና ሥልጠናዎችን ከትምህርት ቤቶችና ከወረዳው የመንገድ ትራንስፖርት መምሪያ ጋር በመተባበር ሰጥተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን በመከላከልና ለሴቷ ድምፅ በመሆን ረገድስ?
ተስፋነሽ (ዶ/ር)፡- ድርጅታችን ፕሮጀክቱን በሚያንቀሳቅስባቸው አካባቢዎች ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ሲያጋጥሙት የሥነ ልቡና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ከዚህም ባለፈ ጥቃት የደረሰባት ሴት የሕግም ሆነ ሌሎች የሚያስፈልጉ ዕገዛና ዕርዳታዎችን እንድታገኝ ከሴቶች ቅንጅት ማኅበራት ጥምረት፣ ከዩኤን ውሜን፣ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ማኅበር፣ ከኢትዮጵያ ሴቶች ኔትወርክ አሶሴሽንና ከሌሎችም በሴቶች ዙሪያ ከሚሠሩ ማኅበራት ጋር እንድትገናኝ እናደርጋታለን፡፡ ፓሽኔት የገንዘብ ድጎማ በመስጠት፣ ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበትና የሚከታተሉበትን መንገድ በመፍጠርና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሰው የሚቀላቀሉበትን ሁኔታም ያመቻቻል፡፡
ሪፖርተር፡- ድርጅታችሁ ከሌሎች በሴቶች ዙሪያ ከሚሠሩ ማኅበራት ጋር በመጣመር አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ስለእንቅስቃሴው ቢያብራሩልኝ?
ተስፋነሽ (ዶ/ር)፡- አሁን ባለንበት ዘመን ሴቶች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን ይገባቸዋል፡፡ ይህ ትልቁ የሴቶች ጥያቄ ነው፡፡ የሴቶች ብድር የማግኘት፣ የእኩልነት፣ በፖለቲካው ዘርፍ እኩል የመሳተፍና ሌሎችም ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ ከተለያዩ በሴቶች ዙሪያ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር የጋራ አጀንዳ በመቅረፅ ዳር እንዲደርሱ የማድረግ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ዛሬም አነስተኛ ነው፡፡ በአመራር ደረጃ ምንም እንኳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቁጥር መሻሻሎች ቢኖሩም፣ በሚፈለገው ደረጃ የሴቶች ተሳትፎ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶች አሁንም እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡ አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ፣ የፆታ እኩልነትን ማረጋገጥና በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያላቸው ታዋቂ ሴቶችን ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሴቷን መብት ሊያስከብሩ የሚችሉ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡ በዚህም ቀላል ሊባል የማይቻል ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሆኖም ግን የወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎችን ሙሉ በሙሉ ወደ መሬት አውርዶ በመተርጎም በኩል ክፍተት አለ፡፡ ሴቶች ዛሬም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ውስጥ እያለፋ ነው፡፡
ሴቶች ላይ እንደ አስገድዶ መድፈር፣ የአሲድ መደፋትና ሌሎችም ፆታዊ ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል፡፡ የፍትሑ ሁኔታም ያዝ ለቀቅ ነው፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በሴቶች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር ላይ ናቸው፡፡ ዛሬም የሴቶች ግርዛት የሚደረግባቸው ክልሎች አሉ፡፡ ሩቅ ሳይኬድ እዚሁ አዲስ አበባ እንጥል የሚቆረጥባቸው ሥፍራዎች እንዳሉ ይሰማል፡፡ ይኼ ሁሉ ድርጊትና ተግባር የሴቷን መብት የሚጥስ፣ የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥር፣ በማኅበራዊ ሕይወት ያላትን ክብር የሚያፋልስና ዝቅ የሚያደርግ በመሆኑ በጋራ ለመታገልና ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለማሰማት የታቀደ ነው፡፡ በተናጠል የሄድንባቸው መንገዶች የራሳቸው የሆነ ውጤት የተመዘገበባቸው ቢሆንም፣ የሚጠበቀውን ግን ለማሳካት በኅብረት መቆም ወሳኝ በመሆኑ ይህንን ለመተግበርና ድምፃችንን ለማሰማት አገራዊ የሴቶች ንቅናቄ ለመፍጠር እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡