ልናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ እስልምና አባቶች ጋር ያደረጉት ውይይትና ፋይዳው

አንባቢ

ቀን: April 3, 2024

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

መንደርደሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመጋቢት ወር ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችን እየሰበሰቡ አነጋግረዋል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በጥቅሉ ሲመለከተው፣ የሕዝብ አስተያየት ለመሰብሰብና መንግሥታዊ አቋምንም ለማሳወቅ የተዘጋጀ ይመስላል፡፡ በዚህም ግንዛቤ መሠረት እሳቸው ካነጋገሩት የኅብረተሰብ ውስጥም ነጋዴውን ይወክላሉ ተብለው የታሰቡ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች፣ የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት የሃይማኖት አባቶችና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን የሃይማኖት አባቶች ይገኙበታል፡፡ ከነጋዴዎችና ከሃይማኖት አባቶቹ ከተደረገው ውይይት ከሁለቱም በኩል ጠቃሚ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ ከስብሰባው ሒደትም በአካል እንቅስቃሴና በፊት ገጽታ እንጂ በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡ እያንዳንዱ ተናጋሪ ነፃ ሆኖ መናገር እንዲችል መድረኩ ክፍት ቢሆንለትም፣ በሚቻለው መጠን ሁሉ ራሱን ተቆጣጥሮ ይናገር እንደነበር በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተወካዮች ጋር የተደረገ ውይይት

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አዳራሽ ሲገቡ በቀጥታ ያሉት ‹‹የእናንተን (ስብሰባ) ከሰዓት ያደረግንበት ምክንያት በዚሁ ወደ ኢፍጣር አብረን እንገባለን ብለን ነው፡፡ ያው ሰሞኑን ከተለያየ የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ውይይት እናደርግ ነበር፡፡ ዛሬ የሙስሊም ቀን ነው፡፡ በዚህ ቀን ውስጥ ልታነሷቸው የምትፈልጓቸው ማንኛውም ጉዳዮች ቢኖሩ፣ ማንኛውም ሐሳቦች ካሉ፣ ከእናንተ ለመስማት ለመወያየት፣ ወደፊት ልንሠራባቸው የሚገቡ ነገሮች ካሉ፣ የጋራ የሆነ ሐሳብ ለመያዝ ነው፤›› ማለታቸውን ማስቀደም እወዳለሁ፡፡ ስለሆነም በማንኛውም ጉዳይና ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ለስብሰባ የተወሰነው የጊዜ ገደብ ድረስ ‹‹ማንኛውም ሐሳብና ጉዳይ›› ተወስቷል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአራቱም ስብሰባዎች በላቀ ሁኔታ ስብሰባውን ከፍተው እስከ ሚጨርሱበት ጊዜ ነፃና ዘና ብለው ሐሳባቸውን የሰጡበት በዚህ ስብሰባ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይህ የራሱ የሆነ ፖለቲካዊ ትርጉም ይኖረው እንደሆነ ለፖለቲካ ተንታኞች እተወዋለሁ፡፡

የስብሰባው ቅርፅ ሲታይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራዎች የተሰጡ አጭር ምሥጋናዎች፣ አድናቆትና አጭር አስተያየቶች የተካተቱበት ነው፡፡ ምሥጋናዎቹም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስ እየተጠቀሰ እንደቀረቡት ሁሉ፣ የሙስሊሞች አስተያየትም በቁርዓን ላይ መሠረት ያደረጉ ነበሩ፡፡

በተረፈ እኔ የተከታተልኩት ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ውይይቱን እንዳለ ያቅርበው፣ ያሳጥረው፣ የስብሰባውን ድባብ በራሱ መንገድ ይምራው ባላውቅም በአጠቃላይ 1፡27፡56 ሰዓት ውስጥ የማይሰለች ዝግጅት ቀርቧል ማለት ይቻላል፡፡ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል በሆነው የስብሰባ ጊዜ ውስጥም፣ 45.45 በመቶ ያህሉን ጊዜ 20 ያህል አስተያየት ሰጪዎች ተጠቅመውበታል፡፡ ይህም እያንዳንዱ ተናጋሪ በአማካይ ሁለት ደቂቃ ያህል መናገሩን ሲያመለክትም፣ በጣም ጥቂቱ ከአምስት ደቂቃ በላይ ተናግረዋል፡፡ 54 በመቶው ያህሉን ጊዜ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ፣ ማብራሪያና አስተያየት ለመስጠት ተጠቅመውበታል፡፡ 

ኢትዮጵያውያን ሙስሊም የሃይማኖት አባቶች የቸሩት ምሥጋናና የሰጡት አስተያየት

የመጀመሪያውን አስተያየት የሰጡት ሼክ ሳዲቅ ወጌቦ የደቡብ ምዕራብ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሲሆኑ፣ እሳቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሕጋዊ አካል እንዲኖረው ማድረጋቸውን፣ ወለድ አልባ ባንክ እንዲቋቋም ማስቻላቸውን አመሥግነው፣ ‹‹በ2005 ዓ.ም. በቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የወጣ የአምልኮና የአለባበስ ሥርዓት የሚል በተማሪዎች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መመርያ አለ፡፡ ያ መመርያ ትኩረት ያደረገው በአብዛኛው በሙስሊም ሴት ተማሪዎች ላይ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ መመርያው የሙስሊሙን ማኅበረሰብ በሚመችና ሐቁን በጠበቀ መልኩ እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ ‹‹በጎዳና፣ በማኅበራዊ ቦታዎችና በገበያ ላይ የሚደረጉ አምልኮ ጉዳዮች በቤተ እምነት ቢገደብ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

‹‹ዝርዝር ውስጥ ባልገባም ብዙዎቻችን (ጠቅላይ ሚኒስትሩን) ከልብ የምናመሠግንባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ይህን ሐሳቤን የማቀርበው ከሁሉም አስቀድሞ ይህ መንግሥት መንግሥታችን ነው፣ ይህ አገር አገራችን ነው በሚል በላቀ ስሜት ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን መስጠት የጀመሩት ኡስታዝ ሐሰን ዓሊም፣ ‹‹በቅርቡ ሸገር ከተማን ለማደስና ተስማሚ አድርጎ ለወደፊቱ ለመሥራት በሚል የተለያዩ ሕገወጥ ግንባታዎች እየፈረሱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሕገወጥ ግንባታና ሕገወጥነት እንዲስፋፋ ባንፈልግም ሕገወጥ ግንባታን በማፍረስ ሒደት በአካባቢው ለ20 ዓመታት የኖሩ ስለሆኑ፣ መንግሥት አንድ ነገር ያደርግላቸው ዘንድ ሊታሰብበት ይገባል የሚል ዕሳቤ አለኝ፡፡ ሌላው የዛሬ ዓመት አካባቢ የፈረሱ መስጊዶች መልሰው እንደሚተኩ የሸገር ከንቲባም ባሉበት መጅሊሳችን ተጋግሮ ቃል ተገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ መስጊዶች ተመልሰው አልተሠሩም፡፡ ጉዳዩም ተንጠልጥሎ ቀርቷልና የዚህንም ጉዳይ እንዲከታተሉልን ነው፤›› የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በአፍሪካ ቲቪ ለጥያቄዎች መልስ በመስጠት የሚታወቁት የምክር ቤቱ የዑለማ ጉባዔ ምክትል ሰብሳቢና የፈትዋ ጉዳይ ሰብሳቢ የሆኑት ሼክ መሐመድ ዘይን ዘህረዲን ንግግራቸውን የጀመሩት፣ ‹‹አላሁ ሱብሐነሁ ወተዓላ ፈቃዱ ሆኖ እዚህ እርስዎ ፊት ቀርበን የሙስሊሙን ጉዳይ ለማቅረብ አላህ ለወፈቀን (ዕድል ስለሰጠን) ጌታ ከሁሉም በፊት ምሥጋና ይገባው አልሐምዱሊላህ፡፡ በመቀጠል ደግሞ ለኢትዮጵያ ሙስሊመሞች ለዓመታት ያለቀሱትን ለቅሶ መልስ ለመስጠት የሚችል አቅም አስይዞ እርስዎን እዚህ ቦታ ላስቀመጠው አላህ ምሥጋና ይግባው፡፡ እርስዎም ባለፉት ዓመታት ብዙ ኸይራቶችን (ደግ ሥራዎችን) ብዙ ቁምነገሮችን ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች አሳይተውናል፡፡ ብዙ ችግሮችን ፈትተውልናል፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ዛሬ መነሳት አለባቸው ብዬ ከማስባቸው ጉዳዮች ውስጥ ብዙ ዓመት ያስቆጠሩ ድርጅቶች፣ መሳጂዶችና መቃብሮች፣ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ ሰውነት አላገኙም፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሁኔታዎች በትኩረት አይተውልን የተለመደውን ዕገዛዎትን እንዲያደርጉልን ለማስታወስ ነው፣ ጀዛኩሙላህ ኸይር፤›› በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡ 

የጠቅላይ የምክር ቤቱ የትምህርትና ማኅበራዊ አገልግሎት ኃላፊ አብደላ ኸድር (ዶ/ር) ደግሞ፣ ‹‹በአገራችን ያለው የዓረብኛ ትምህርት በእርስዎ ጊዜ፣ በእርስዎ ዕድሜ ለየት ያለ ሁኔታ እንዲኖረው ትልቅ ዕድገት ላይ እንዲደርስ ያለንን ምኞት ነው ለመግለጽ እወዳለሁ፤›› በማለት ንግግራቸውን ጀምረው፣ ‹‹በመጀመሪያ ፈጣሪ የቸረዎትን አገርን በብልኃት የመምራት፣ የአገራችንን ልማትና ዕድገት ያለዎት ቁርጠኝነት፣ የአገር አንድነትና የሕዝቦቿ አብሮነት ያለዎት ቁርጥ ራዕይ፣ በመደመር ፍልስፍና መሬት ላይ መውረዱን ዛሬና ትናንትና ባደረግነው ጉዞ በደንብ ተገንዝበናል፤›› በማለት አድናቆታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ባለፈው ዓመት የዓረብኛ ትምህርት ከታች ይጀመራል ሲባል የሰማነው መሬት ላይ ወርዶ ብዙ አላገኘሁትም፡፡ ትምህርት በዓረብኛ ለመስጠት አስቸጋሪ የሚሆነው ካሪኩለሙን የሚቀርፅ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን የሚያስተካክል አካል ያስፈልጋል፡፡ ይህ አካል ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ በዓብይ (ዶ/ር) ዘመን ዕውን ሆኖ ማየት እንፈልጋለን፡፡ ይህ ትልቁ ምኞታችን ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄም ነው፡፡ አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ሼክ መሐመድ ኸሊል ወራቂም በበኩላቸው፣ በጎበኙት ነገር ሁሉ መደሰታቸውን የበለጠ ለማየት ይችሉም ዘንድ ፈጣሪ ዕድሜ እንዲቸራቸው የሚሹ መሆናቸውን፣ በዕለቱ የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሠሩት ጥቂቱን ብቻ መሆኑን አስታውሰው፣ ‹‹የአገራችን የሰላም ሁኔታ ትንሽ ገባ ወጣ የማለት ችግር አለ፡፡ በአገራችን በሰሜናዊ ኢትዮጵያ ያስገኙትን ሰላም አይተናል እርሶን ያሸንፎታል ብለን አናምንም፡፡ ይህም ሰላም እንዲደገም እንፈልጋለን፡፡ እኛም ለሰላሙ ታጥቀን ልንሠራ ምኞታችን ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን በአጭሩ አስቀምጠዋል፡፡  

ሼክ ከማል ሙሳ ከኦሮሚያም፣ ‹‹ክቡርነትዎ ለአገርና ለወገን ብዙ ጠቃሚና አስፈላጊ የሆኑ ሰላምና ልማት ማስተካከያዎችን በዕውን አሳይተዋል፣ ሠርተዋል፣ አይተናል፣ ተገንዝበናል፤›› በማለት ምርቃታቸውን ካፈሰሱ በኋላ፣ ‹‹ታላቁ የኦሮሚያ ሙስሊም የአገራችን የጀርባ አጥንት ሆና የተፈጠረችው በመዲናችን ፊንፊኔ ይህ የሚባል ሕዝቡን የሚመጥን፣ ኦሮሚያን የሚመስል ቢሮ የለንም፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስለዚህ ይህ ጉዳይ ታውቆ ታይቶልን፣ የኦሮሚያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት የሚበቃ መሬት ከአዲስ አበባ እንዲሰጠን በአክብሮት እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ቀጣዩ ተናጋሪ አህመድ መሐመድ ሐሚዲን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ዑለማዎች ጉባዔ ዋና ጸሐፊ በኢትዮጵያ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት ከሚታወቁት ዓሊሞች (ሊቃውንት) አንዱና በብዙ መድረኮች እስላማዊ ትምህርት በመስጠት የሚታወቁ ሰው ሲሆኑ እሳቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ ‹‹(እርስዎ) ለኢትዮጵያ ሙስሊም ታላቅ ባለውለታ ነዎት፡፡ ለዘመናት ሲንከባለሉ የነበሩ መሠረታዊ ነገሮች በእርሶ የሚመራው መንግሥት ምላሽ አግኝተዋል፤›› በማለት ምላሽ ካገኙት ጥቂቱን አውስተዋል፡፡ ‹‹ሌሎች ጥያቄዎችም መልስ እንደሚያገኙ ተስፋችን እየለመለመና እያደገ ነው፡፡ ፍላጎቶቻችንና ጥያቄዎቻችን መልስ ባገኙ ቁጥር በአገር ዕድገት ላይ አንድ እሴት ይጨምራሉ፡፡ አሁን አተኩሬ ልናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር ታሪካችን እንደሚመሰክረው በኢትዮጵያ ውስጥ ኢስላማዊ ዕድገት ረጅም ዕድሜ አለው፡፡ ምናልባትም አጎራባች አገሮችን እስልምና ያስተማርነው እኛ ነን፡፡ ዛሬ ዛሬ ግን እነዚያ በባህላዊ ትምህርት ቤቶች ዘመናዊነት እየተገዳደራቸው ባሉበት ሁኔታ ሊቀጥሉ አልቻሉም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ዘመናዊ ዩኒቨርሲቲ ማቋቋምና ትምህርቱን ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ይህም ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከእነዚያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተማሪዎች እንደ አንድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ሊቆጠሩ የሚያስችላቸው ዕውቅና ማግኘት አለባቸው፡፡ ለእነሱም በቂ የሆነ መሬት ያስፈልጋል፡፡ ስለተሰጠኝ የመናገር ዕድልም ሆነ እስከ ዛሬ እያደረጉት ስለሚገኙት፣ እንዲሁም ሕዝቦችዎን በእኩልነት በማየት የሁሉንም መብት ለማስጠበቅ ጥረት ስለሚያደርጉ ለእርስዎና ለመንግሥትዎ ትልቅ ፍቅር አለን፡፡ ከዚያም በላይ ዱዓችን ነው፡፡ በዚህ በረመዷን ዱዓ እናደርጋለን፡፡ ወፈቀከላሁ ሊኩሊ ኸይር ‹‹ለሁሉም ደግ ሥራዎ ፈጣሪምንዳዎትን ይክፈለው፤›› ሲሉ ንግግራቸውን ደምድመዋል፡፡

‹‹የእንስሳት ዙ ሲጎበኙ ዕፅዋትና እንስሳት የተለያየ ባህሪ የተለያየ መልክ ኖሯቸው በአንድ ላይ መኖር እየቻሉ ለምን የተለያየ ጎሳ፣ የተለያየ ብሔር ያለው ሰው በፍቅር መኖር አቃተው?›› የሚል ጥያቄ በልቦናቸው ያደረባቸው የኦሮሚያው ኢስላማዊ ጉዳይ ምክር ቤት አባል ሼክ ዓብዱል ሐኪም፣ ጉብኝቱን በሚመለከት የተሰማቸውን ደስታ በሰፊው ገልጸው፣ ‹‹ለብዙ ዓመታት ኢትዮጵያን የገዙ መሪዎች ያልሠሩትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጭር ዓመታት ውስጥ ሠርተው አሳይተዋል፤›› ሲሉ አድናቆታቸውን በመቀጠል፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ ቡና፣ ሌጦና የቁም እንስሳ ወደ ውጭ በመላክና ዶላር ለአገር በማስገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሕዝብ ነው፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን በዓመት አንድ ጊዜ ወይም በሕይወቱ አንድ ጊዜ ሐጅ ሊያደርግ ከተመዘገበ በኋላ በዶላር እጥረት ምክንያት ከጉዞ እንዲቀር እየተደረገ ለብስጭት ይዳረጋል፡፡ ይህ ችግር ለዘለቄታው የሚፈታበት ሁኔታ ቢኖር እላለሁኝ፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ተወካይ ሼክ አመዴ ደግሞ፣ ‹‹በሃይማኖት ዙሪያ የነበሩ ልዩነቶች እንዲፈቱና ኅብረተሰቡ ለአገሩ፣ ለዕድገቱ፣ ለብልፅግና አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ያደረጋችሁት ሥራ ምሥጋና ይገባዋል፡፡ እንዲሁም በአገር አቀፍ ሁኔታ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየሠራችሁ እንደሆነ አይቻለሁ፡፡ በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ወይ ያለነው የሚል ጥያቄ አጭሮብናል፡፡ ያም ብቻ አይደለም፡፡ ከዚያም በላይ ኢትዮጵያ የማደግ፣ የመበልፀግ፣ ሕዝቦቿንም የመጥቀም በመሪዎቿ አማካይነት ተስፋ እንዳለን  ተሰምቶኛል፡፡ እና እጅግ በጣም እናመሠግናለን፡፡ የመጣሁት ከአማራ ክልል ሲሆን በሙዚየም፣ መታየት ከነበረባቸው ቅርሶች ውስጥ 800 ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የሾንኬ ጥንታዊ መስጊድና 60 የሚሆኑ ቤቶች ከገመድ፣ ወይም ከማሰሪያ፣ ወይም ከሚስማር ውጪ በድንጋይና በእንጨት የተሠሩ ቤቶችን የሚወክሉ ቢኖሩ መልካም ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ቅርሶች ቢለሙ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የኢኮኖሚ ምንጮችም ይሆናሉ፡፡ አገራችንንም ያስተዋውቃሉ፡፡ እነዚህ ምናልባት ወደፊት በባህልና ቱሪዝም ትኩረት እንዲሰጣቸው በክልሉም በፌዴራሉም በኩል ቢታዩ ለማለት ነው፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን እንደሚያሻግሩ በጣም ሙሉ ተስፋ አለኝ፡፡ አላህ ይርዳዎት፡፡ ሐሳብዎንም አላህ እንዲያሳካው ዱዓ እናደርጋለን፡፡ በጣም አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡

ኡስታዝ ዑስማን ዱሬ ደግሞ፣ ‹‹በሐረሪ ክልል ካሉ ችግሮች አንዱ የጫት ንግድ ጉዳይ ነው፡፡  ኮንትሮባንድ በሚል ምክንያት አንድ አርሶ አደር ጫት ከማሳው ወደ ገበያ እንዳያወጣ ችግር ሆኗል፡፡ ሕዝብን እያማረረ ይገኛል፡፡ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ይዞ መንቀሳቀስም አይቻልም፡፡ በተመሳሳይ የቡና ምርትም እንዲሁ፡፡ ይህ እንዴት ይታያል ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ እጅግ በጣም አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ኡስታዝ አብዱራህማን ሡልጣን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው፣ ‹‹በአገራችን በተለይ በአሁኑ ብዙ ለውጦች እያየን ነው፡፡ ፍትሐዊነትን እያየን ነው፡፡ ስለሆነም በጎንደር ከተማ ሊመለሱ ከሚገባቸው ጥያቄዎች ውስጥ የጎንደር ከተማ የውኃ ችግር ነው፡፡ በ15 ቀን አንድ ቀን ይመጣል ለዚያው ከደረሰ ነው፡፡ ሴቶች እንደ ድሮው እንሥራ ተሸክመው ወደ ወንዝ ሲሄዱ እያየን ነው፡፡ በእርግጥ ችግሮን ለማቃለል የሚያስችሉ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ፡፡ ፈጠን ፈጠን ብለው ቢሠሩልን፤›› በማለት ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰዒድ ዓሊ (ዶ/ር) አገሩን ከአፋር ደግሞ፣ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ቀጥሎም እንደ ሙስሊምነቴ በመጨረሻም እንደ አፋርነቴ እርስዎን ማመሥገን እፈልጋለሁ፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊነቴ ይህች አገር እንደ አገር እንድትቀጥል ያደረጋት አላህ ሱብሐነሁ ወተዓላ ማመሥገን እፈልጋለሁ፡፡ በመቀጠል ደግሞ በእርስዎ የተሠሩ ግልጽ የሆኑ ለውጦች ስላሉ እርስዎን ማመሥገን እፈልጋለሁ፡፡ እንደ አፋርነቴ ማመሥገን የምፈልገው ደግሞ፣ እርስዎ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አፋርን ከአጋርነት ወደ ባለቤትነት፣ ወደ ወሳኝነት ወደ እኩልነት፣ ወደ ብልፅግና ስላመጧት ማመሥገን እፈልጋለሁ፤›› በማለት ጀምረው፣ ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ በአፋር ራበኝ ማለት በጣም ነውር ነው፡፡ ስለዚህ ሰው የራበው አይመስለውም፡፡ ነገር ግን ከባድ ችግር ነው ያለው፡፡ ሕዝቡ አርብቶ አደር ነበር፡፡ አሁን አርብቶ አደርነቱን እየለቀቀ ነው፡፡ እርስዎ ከመጡ በኋላ በተለይ በእርሻ ላይ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የአርብቶ አደሩ ጉዳይ ላይ ያን ያህል ትኩረት ተሰጥቷል ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ ወንዞቹ ተገድበው፣ አርሶ አደርም አርብቶ አደርም በአንድነት ማሳተፍ እንደሚቻል፣ እርስዎ ከሠሩት ሥራ ተምሬያለሁ፡፡ በመጨረሻም የአፋር ሕዝብ ድንበር ላይ ያለ ሕዝብ ነው፡፡ በተለይ በተለይ በጂቡቲ ድንበር ያለው አፋር በእነሱ ቤት የሚያልፈው ዘይት፣ ሩዝ፣ የሚበላ ነገር አዲስ አበባ ደርሶ ሲመለስ እጥፍ ዋጋ ነው የሚያስከፍለው፡፡ ይህ ጥያቄ እንዴት ይታያል ለማለት ነው፣ አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ ጊዜያዊና ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት አሳስበዋል፡፡

ኡስታዝ ዑስማን ዱሬም በቀጥታ ወደ ጥያቄው በመግባት የአውሮፓ ኅብረት በአፍሪካና በካሪቢያን፣ እንዲሁም በፓሲፊክ አገሮች መካከል የተፈራረሙትን ‹‹ሳሞዋ›› በመባል የሚታወቀውን የንግድና ኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነትን ለአብነትም በስምምነቱ አንቀጽ 36/2 ላይ የጠቀሰው የወሲብ፣ የሥነ ተዋልዶና የጤና መብቶች በቀጥታ ከግብረሰዶም መብቶች፣ ከፆታ መቀየር፣ ከውርጃ፣ ሁሉን አቀፍ የወሲብ ትምህርቶችን ሕጋዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ፣ ሁለተኛ ስምምነቱ የአፍሪካ ፕሮቶኮል አንቀጽ 40.6 ላይ በአኅጉሪቱ የሚገኙ ታዳጊ ሕፃናት ሁሉን አቀፍ ወይም ደግሞ ‹‹ኢንክሉሲቭ ሴክሹዋል ኢዱኬሽን›› የተባለውን አደገኛ ትምህርት እንዲማሩ የሚያስገድድ በመሆኑ፣ ሦስተኛ የግብረ ሰዶማውያን አስተሳሰቦችን ለማስረፅ በሰነዱ በርካታ ቦታዎች ላይ አካታችነት በሚሉ ቃላት ተሸፍኖ እንዲገባ በመደረጉ፣ አራተኛ ስምምነቱ የወላጆችን መብት የሚጥስና የኢትዮጵያ ቤተሰብ እሴቶችን አደጋ ላይ የሚጥል አንቀጾችን የያዘ በመሆኑ፣ ወዘተ ኢትዮጵያ ራሷን ከዚህ ስምምነት እንድታግድ በዚህ አጋጣሚ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡ አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሼክ አህመድ ሙሐመድ ዓሊ ከሱማሌም፣ ‹‹ባለፉት አምስት ዓመታት እንደ አገር የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ያመጣው ለውጥ እኛም ጋ ደርሷል፡፡ ውጤቱ በሃይማኖቱ፣ በሕዝቡ ኑሮም የሚታይ ነው፡፡ ለዚህም ምሥጋና እናቀርባለን፡፡ በክልሉ ካገኘናቸው ውጤቶች አንደኛው ሰላም ነው፡፡ በተገኘው ሰላም ምክንያት አሁን ላይ በነፃነት መንቀሳቀስ እንችላለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ የማነሳው የተከበሩ ሐጅ ኢብራሂም ቱፋ በሱማሌና በአፋር መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ይህ ጥረት መንግሥት እንዲደግፈው መጠየቅ እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡፡

ኡስታዝ አህመዲን ጀበልም፣ ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ማንኛውም ጥያቄ እንዲጠይቅ እንዲህ ነፃ መድረክ በመክፈትዎ አመሠግናለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ ለሁለት ቀናት ተዘዋውረው በጎበኟቸው መርካታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ዓድዋ ሙዚየም ከዚህ በፊትም ሳያልቅ በተወሰነ መልኩ ጎብኝቸዋለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ሁሉን ያሳተፈ እንዲሆን ጥረት በደንብ እንደተደረገና ከጭቅጭቅ አጀንዳም ለመውጣት ጥረት እንደተደረገ አይቻለሁ፡፡ ቢሆንም ከሙስሊሙ በኩል ደግሞ የሚጎድሉ እንዳሉ ይሰማኛል፡፡ እንደ ሙስሊም እርስዎ ለኢትዮጵያ ሙስሊም ካደረጓቸው ታላላቅ ነገሮች አንዱ ኢስላማዊ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመሠረት የወሰዱት ቆራጥ ዕርምጃ ነው፡፡ ሆኖም የጎደሉ ነገሮችን ዛሬ ለማስታወስ እፈልጋለሁ፡፡ ይህንን ስል በወቀሳ መልክ ሳይሆን በሚመለከተው አካል ትኩረት ስላልተሰጠው ነው ከሚል ነው፤›› ብለው፣ እ.ኤ.አ.  በ2019 የወጣው መመርያ በተለይም አንቀጽ SBB/62ን እና SBB/72  2019 በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ፣ በቀጥታም፣ በተዘዋዋሪም ምንም ዓይነት ኮሽታ እንዲፈጠርና ችግር ውስጥ እንዲገባ አንፈቅድም፣ አንፈልግም፡፡ ለአገር ሰላም፣ ለአገር ልማት የምታደርጉትን የላቀ ጉዞ መላው ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ከጎናችሁ ሆኖ እንዲያግዛችሁ በምክር ቤቱ ስም ለመግለጽ እወዳለሁ፤›› በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼክ ሐሚድ ሙሳ ስለመስጂዶች ችግር ካወሱ በኋላ፣ ‹‹ሐጅ በምናደርግበት አገር የጠነከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ስለሚያስፈልግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዲፕሎማሲ ወይም በአምባሳደር ማዕረግ የሐጅ ጉዳይ ዘርፍ ተጠሪ ይመደብ ዘንድ በእርስዎ አንደበትና በእርስዎ ቀና ልቦና መመርያ ቢተላለፍልን ጥያቄዬን አቀርባለሁ፡፡ በጥቅሉ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በጣም አመሠግናለሁ፡፡ ጀዛኩሙላሁ ኸይረን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ደምድመዋል፡፡

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ ‹‹በአገር ያሉ ልማቶችን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ብዙ መሥራት እንደሚቻልና ለውጤት ማብቃት እንደሚቻል በጥቂቱ ባየናቸውና በምናያቸው እንደ አገርም እየኖርናቸው ያሉ፣ ደግሞም ሲሠሩ ስናያቸው የነበሩ የማይመስሉ በዚህ ፍጥነት እዚያ ደረጃ ላይ ደርሰው ስናያቸው እንደ አገር ኩራት ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ችግሮች የሉም ማለት አይደለም፣ አሉ፡፡ አስተየያት ስንሰጥ ግን ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ መሆን ይኖርበታል፤›› በማለት ጀምረው፣ ‹‹በአገሪቱ ያሉትን የሰላም ችግሮች ለመፍታት እዚህ ያሉ የሃይማኖት አባቶች እንደ ኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም፣ እንደ አባትም ኃላፊነታችንም ግዴታችንም ስለሆነ በእኛ በኩል በሚፈለገው ላይ ዝግጁ መሆናችንን መግለጽ እወዳለሁ፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በመጨረሻም ሼክ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ (ዶ/ር)፣ ‹‹ለዚህ ያበቃን አላህ ምሥጋና ይግባው፣ እኔ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሠገኑበትን ቆጥሬ ሰፍሬ ስለማልጨርስ በዝምታ ነው የማልፈው፡፡ ብዙ አገሮች እሄዳለሁ፡፡ በእነዚህ አገሮች ያሉ ትልልቅ ሰዎች ዱዓ አድርጉለት ይላሉ፡፡ አልፎ ተርፎ የባህር በር ጉዳይ ሲነሳ ኢትዮጵያ ሀቅ አላት ይላሉ፡፡ በተረፈው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያደረጉልን ብዙ፣ የቀሩትም ደግሞ ይበልጣሉ፡፡ በሌላ በኩል የአፋርና የሶማሌ ችግርን ለመፍታት በምናደርገው ጥረት ይሳካ ዘንድ ከጎናችን እንድትቆሙ በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በስተመጨረሻ መጅሊሱን ሥልጣኑን የተረከብነው ለሦስት ዓመት ነው፡፡ አሁን የሚቀረን አንድ ዓመት ከምናምን ነው፡፡ ሥልጣኑን ከሕዝቡ የተረከብነው ኃላፊነት ለሕዝብ መመለስ ስላለብን ከወዲሁ እንዲታሰብ፤›› በማለት ምርጫው በሰከነ ሁኔታ እንዲካሄድ ከወዲሁ አሳስበው፣ የሃይማኖት ተቋማትን በአንድ ላይ ቢያወያዩ መልካም ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም የቀረቡት አስተያየቶች ጠቃሚ መሆናቸውን አውስተው፣ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን እንዲመለሱ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

ማጠቃለያ

ምንም እንኳን በአገራችን ተጠቃሎ የታተመ የሕዝብ አስተያየት (Public Opinion) ታሪክ ይኖር እንደሆነ ባላውቅም የመንግሥታት መሪዎች፣ ‹‹ሕዝቡ ምን ይላል?›› እያሉ ይጠይቁ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የሕዝቡን አስተያየት ወይም አስተሳሰብ ለማግኘትም በየጠላ ቤቱ፣ ሕዝብ ሰብሰብ በሚልበት አካባቢ ሕዝቡን መስለውና ተመሳስለው መረጃ የሚያቀብሉ ሰዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ሆኖም መንግሥታቱ ወይም ሰዎቹን ያሰማሯቸው ባለሥልጣናት መረጃውን ካገኙ በኋላ ተናጋሪዎቹን ያስሯቸውና ያሰቃይዋቸው ስለነበር ሰዎቹ፣ ‹‹በጆሮ ጠቢነት›› ተሰይመው ከእነሱ ፊት አስተያየት የሚሰጥ ጠፋ፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ‹‹ሕዝቡ ምን አለ?›› ብለው ከሚጠይቁት ነገሥታት አንዱ የነበሩ ሲሆኑ፣ የሐረር ዓሚሮችም ራሳቸው ሌሊት እየዞሩ ሕዝብ ምን እንደሚል ያዳምጡ እንደነበር ይነገራል፡፡ ‹‹ያለ ምክር የሚኖር ንጉሥ ያለ አንድ ቀን አይነግሥ›› የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡

የሕዝብ አስተያየት በአዎንታዊ ገጽታው ሲታይ በልዩ ልዩ መንገዶች የሚሰበሰብ ሲሆን አንደኛው፣ ‹‹ይህን የኅብረተሰብ ቡድን ለማግኘት ያስችለኛል›› ተብሎ ከሚታሰብ አካል ጋር የሚደረግ ስብሰባ ነው፡፡ መንግሥታት የኅብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመገንዘብ ከተቻለም በራስ አመለካከት፣ ፍልስፍና፣ ዓላማ ለመምራት የሚያስችል ሐሳብ ለመሰንዘር የሚያስችላቸው አንድ የፖለቲካ መንገድ ነው፡፡ የሕዝብ አስተያየት የፖለቲካ ቡድኖችን ዓላማ ለማስረፅና በራሳቸው መልክ ለመቅረፅም ይረዳል፡፡ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደርና ማኅበራዊ ለውጥን ለማምጣት ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ስለሆነም ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መንግሥታት የሕዝብ አስተያየትን አስፈላጊነት በመረዳት ሕዝብን ሰብስበው ያነጋግራሉ፡፡ የሕዝብን አስተያየት መረዳትና መተንተን የሰፊውን ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት የሚያንፀባርቅ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለማድረግ አስፈላጊ ነው።

የሕዝብ አስተያየትን የሚመለከትበት አንዱ ቁልፍ ምክንያት ባለሥልጣናት ፖሊሲዎቻቸውና ሐሳቦቻቸው ያላቸውን ተወዳጅነት ወይም ተቀባይነት ለመለካት ያስችላቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ የሕዝብ አስተያየትን ችላ ማለት አመኔታ ማጣትን፣ የመራጮችን መራራቅና በመጨረሻም ፖለቲካዊ መዘዞችን ያስከትላል። ሕዝብን ሰብስቦ ማነጋገር ወይም ሐሳቡን እንዲሰጥ ማድረግ አሉታዊ ገጽታም አለው፡፡ ይህን አሉታዊ ገጽታ ከጥንት ሮማውያንና ግሪካውያን የአምባገነንነት ታሪክ ጋር የሚያያይዝ ነው፡፡ በእርግጥም በአጭሩ እከሌ ለእከሌ ሳንል በጥቅሉ የዓለም ታላላቅ አምባገነን መንግሥታት ሕዝቡን ሰብስበው በፈለጉበት ቦይ እንዲፈሱ ለማድረግ ይጠቀሙበት ነበርና ዛሬ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ በጥቅሉ ግን የሕዝብ አስተያየት ሁልጊዜ ተመሳሳይነት ያለው አለመሆኑንና በኅብረተሰብ ውስጥ ጉልህ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ልብ ሊባል ይገባል። ስለሆነም ነገሮችን ከዕድሜ፣ ከፆታ፣ ከማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ከባህል ዳራ አኳያ ማየት ይመከራል፡፡ እነዚህን ልዩነቶች መረዳት ሁሉን አቀፍ የውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶችን ለማረጋገጥና በኅብረተሰብ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ቡድኖችን ፍላጎቶችና ሥጋቶችን ለመገንዘብ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል፡፡ የሕዝብ አስተያየት ኃይል የማይካድ፣ ወደ ፊትም በማኅበረሰባችን ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ የማድረግና ለውጥን የመምራት ችሎታ አለው። ስለሆነም ስብሰባውን በአዎንታዊ ጎኑ ሳየው በጣም ጠቃሚ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡