

ማኅበራዊ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የኮሪደር ልማት ተነሺዎችን በተመጣጣኝ ካሳ ማስተናገዱን አስታወቀ
ቀን: April 3, 2024
- ለካሳ 1.5 ቢሊዮን ብር መዘጋጀቱንም ከንቲባዋ ተናግረዋል
በኮሪደር ልማት እንዲነሱ የተደረጉ የመሬት ባለይዞታዎች 79/2014 በሚባለው የካሳ መመርያና ደንብ መሠረት ተመጣጣኝ ምትክ ቦታና ካሳ እንደተሰጣቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት ተነሺ የሆኑ የመሬት ባለይዞታዎች በ2014 ዓ.ም. በወጣው የካሳና ምትክ አሰጣጥና መልሶ ማቋቋሚያ መመርያ መሠረት ምትክ ቦታና ካሳ እንዲሰጣቸው መደረጉን፣ የአዲስ አበባ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ከትናንት በስቲያ መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ቢሮው የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ለማሻሻልና ለማዘመን የተሠሩ የማሻሻያ ሥራዎችን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሲሳይ የልማት ተነሺዎችን ጉዳይ ቢሮው በቅርበት እየተከታተለው መሆኑን ገልጸው፣ ምትክ ቦታም ሆነ ካሳ ሳይሰጠው የተነሳ ነዋሪ የለም ብለዋል።
የመሬት ባለይዞታዎች እየተስተናገዱበት የሚገኘው የካሳ መመርያ ልማትን ብቻ ትኩረት ያደረገ አይደለም ያሉት አቶ ሲሳይ፣ የዜጎችን መብቶችም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአሠራር አመቺ አይደሉምና ተደራሽ ሊሆኑ አልቻሉም የተባሉ ከ12 በላይ ደንቦችን፣ ‹‹የመብት ፈጠራና የይዞታ አገልግሎት ደንብና የሊዝ ደንብ›› ተብለው ወደ ሁለት ደንቦች እንዲጠቃለሉ መደረጉም ተመላክቷል።
ከሙስናና ከብልሹ አሠራር ጋር በተያያዘ ዜጎች ጥያቄ ከሚያነሱባቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚገለጸው የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ፣ ችግሩን ለመከላከልና ከእጅ ንክኪ ለማላቀቅ ተብሎ 700 ሺሕ ፋይሎችን ዲጂታላይዝ ማድረጉንና 16 አገልግሎቶችን በበይነ መረብ መስጠት መጀመሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሠራተኛ አስተዳደር ደንብ በማዘጋጀት ሕገወጥ ድርጊት በሚፈጽሙ የቢሮው ሠራተኞች ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ተብሏል።
ሕገወጥ የመሬት ወረራ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የሚስተዋል አይደለም ያሉት በቢሮው የመረጃና ማድረስ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ቢቂላ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድርጊቱ በከተማ አስተዳደሩ ጎልቶ ታይቷል ብለዋል፡፡
በዚህም የተለያዩ የኦዲት ሥራዎች መሠራታቸውን፣ በኦዲት ግኝቱም መሠረት በሕገወጥነት የተገኙ ካርታዎች እንዲመክኑ መደረጉን አስታውቀዋል።
ቢሮው በተለያዩ ጊዜያት በሕገወጥ ድርጊቶች ተሰማርተው አግኝቻቸዋለሁ ያላቸው ሠራተኞችና አመራሮች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን መውሰዱን ሲገልጽ ቢደመጥም፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ አሁንም ድረስ የሚነሱ በተለይም በታችኛው መዋቅር ያለው ሕገወጥ ድርጊት ግን አሁንም መኖሩን ብዙዎች ጥያቄ የሚያነሱበት ነው፡፡
በተያያዘም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በመዲናዋ የተከናወኑና በግንባታ ሒደት ላይ የሚገኙ የመልሶ ግንባታ ኮሪደር የልማት ሥራዎችን አስመልክቶ፣ መጋቢት 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ከንቲባዋ በማብራሪያቸው በአዲስ አበባ ለመልሶ ግንባታና የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ተመጣጣኝ የገንዘብና የመሬት ካሳ አቅርቦት ተዘጋጅቶ የማስተናገድ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም የኮሪደር ልማት ጥናት አማካሪዎች ከሰጡት የካሳ ምክረ ሐሳብ በተጨማሪ፣ ነዋሪዎችን በማካተት 1.5 ቢሊዮን ብር ለካሳ ተዘጋጅቶ በሕጋዊ ሒደት እንዲስተናገዱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ምትክ መሬት ለሚገባቸው ዜጎችም እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የቤት ኪራይና የዕቃ የማጓጓዣ ገንዘብን ጨምሮ 8.5 ሔክታር መሬት ቀርቦ የማስተናገድ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የነዋሪዎችን ማኅበራዊ ትስስር ለማስቀጠልም በድጎማ የሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል እንደተፈጠረም አክለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ካለው ስፋት አንፃር በፒያሳ፣ በአራት ኪሎና በቦሌ መስመር የመንገድና የአረንጓዴ ልማት ሥራውን እስከ ግንቦት መጨረሻ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ወ/ሮ አዳነች አስረድተዋል፡፡