

ማኅበራዊ የዓለም ባንክ በአየር ንብረት ለውጥ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን የ340 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ
ቀን: April 3, 2024
የዓለም ባንክ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት በደረሰባቸው በቆላማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሦስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን፣ አኗኗራቸውን የሚያሻሽሉበትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚቋቋሙበት የ340 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ፡፡
በአብዛኛው አርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በሚገኙባቸው በድርቅ የሚጠቁና በከፊል ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በድጋፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የዓለም ባንክ አካል የሆነው ዓለም አቀፍ ልማት ማኅበር (International Development Association – IDA)ነው ድጋፉን ያቀረበው፡፡
በርካታ የአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በአየር ንብረት ለውጥና ተከታትለው በሚከሰቱ የድርቅና ጎርፍ ክስተቶች እየተጠቁ መሆናቸው ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
በተወሰኑት የአፋርና የሶማሌ ክልሎች የሚገኙ አካባቢዎችና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ አርብቶ አደሮች የሚኖሩባቸው ቦረናን የመሳሰሉ በአብዛኛው ቆላማ ሥፍራዎች በአየር ንብረት ለውጥ መጎዳታቸው ይነገራል፡፡ የሰዎችና የእንስሳት ሞት፣ እንዲሁም ከፍተኛ የንብረት ውድመት እንደገጠሟቸው ይገለጻል፡፡
የዓለም ባንክ ባለፈው ሳምንት ያፀደቀው የ340 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እ.ኤ.አ. ከ2024 እስከ 2029 ድረስ የሚቆይ የቆላማ አካባቢዎችን ማልማት ላይ ያተኮረ ሁለተኛ ፕሮጀክት ነው፡፡
የመጀመሪያው እ.ኤ.አ. በ2019 ፀድቆ ሲሠራበት የቆየ የ326 ሚሊዮን ዶላር ተመሳሳይ ዕቅድ ያለው ፕሮጀክት ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በመጪው ዓመት እንደሚጠናቀቅ የዓለም ባንክ የፕሮጀክቶች ሒደት መከታተያ ያሳያል፡፡
ሁለተኛው ድጋፍ ቴክኖሎጂን፣ ፈጠራን፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ የሚረዱ ልምዶችን ማሳደግ፣ እንዲሁም አመራረትና ሥነ ምኅዳር ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሥራ የዓለም ባንክ የድጋፉን መለቀቅ ይፋ ባደረገበት መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ በበይነ መረብ በመታገዝ ከባቢንና መሬቱን የሚቆጣጠር ሲስተም የሚያበለፅግና ተግባራዊ የሚያደርግ ሲሆን፣ ሲስተሙም የመሬቶችን ምርታማነት እንደሚያሳድግና አርብቶ አደሮቹ የአየር ንብረት ለውጥን እንዲቋቋሙ እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡
የአየር ንብረት ተፅዕኖን የሚላመዱ የግብርና ምርቶችንና የእንስሳት ዕርባታን የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎች፣ ፈጠራዎችና ልምዶች እንዲኖሩ ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ፣ አረንጓዴና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የምግብ ሥርዓት በማኅበረሰቡ ውስጥ እንዲበረታታ እንደሚደረግም ተጠቁሟል፡፡
ድርቅ በኢትዮጵያ እያስከተለ ያለውን ጉዳት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት በተደጋጋሚ ከሚያወጧቸው ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው፣ ጉዳቱ እየተባባሰ እንደሆነ ነው፡፡
የተመድ የሰብዓዊ ድጋፎች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) በየካቲት ወር አውጥቶት በነበረው ሪፖርት እንደገለጸው ኤልኒኖ ያስከተለው ድርቅ በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ፣ እንዲሁም በተወሰኑ የደቡብ ክልሎች ላይ አስከፊ ጉዳት አስከትሏል፡፡
ሰባት ሚሊዮን ያህል ዜጎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጾ የነበረው የማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት፣ 74 ሺሕ ያህል አዳዲስ ተፈናቃዮችም ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ዘንድሮ ጥር ወር ድረስ በድርቅ ምክንያት መፈናቀላቸውን አስታውቆ ነበር፡፡