
ከ 3 ሰአት በፊት
እስራኤል በጋዛ እያካሄደችው ያለው የማያባራ ጥቃት በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በቀጣናው ሌላኛው እየተነሳች ያለች አገር ኢራን ናት።
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ እየተጫወተችው ያለው ሚና የዓለምን ቀልብ እየሳበ ይገኛል።
ኢራን በጋዛ ባለው ጦርነት ሐማስን እንዲሁም ፍልስጤማውያንን ትደግፋለች።
ከዚህ ቀደምም በኢራቅ፣ በሶሪያ እና በፓኪስታን ላይ ጥቃት ከመሰንዘሯ በተጫማሪ በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ውስጥም በተዘዋዋሪ ተሳታፊ መሆኗ አልቀረም ተብሏል።
በዚህ ሦስተኛ ዓመቱን በያዘው ጦርነት ላይ ሩሲያ የኢራንን ጦር መሳሪያዎች መጠቀሟም ተነግሯል።
ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ በተደረጉ አንዳንድ ጥቃቶች ጀርባ አለችበት መባሏን አታምንም።
ከእነዚህም መካከል በእስራኤል ላይ ከሊባኖስ የተሰነዘረው ጥቃት፣ በዮርዳኖስ በሰፈረው የአሜሪካ ሠራዊት ላይ የተፈጸመ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ይጠቀሳል።
በተጨማሪም በቅርቡ መነጋገሪያ የሆነው እና በቀይ ባሕር ላይ በሚተላለፉ የእስራኤል እና የምዕራባውያን መርከቦች ላይ ከየመን የሚሰነዘር ጥቃት ሌላኛው ነው።
ለእነዚህ ጥቃቶች በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች ኃላፊነቱን ወስደዋል።
- ኢራን በእስራኤል ላይ ለተፈጸመው ጥቃት ድጋፏን ሰጥታ ይሆን?11 ጥቅምት 2023
- ንጉሣዊውን አገዛዝ የገረሰሰው የኢራን እስላማዊ አብዮት ግቡን አሳካ ወይስ. . .?23 መጋቢት 2024
- የዳንስ መድረኮችን እያንቀጠቀጡ ያሉት ኢራናውያኑ ሴት ዲጄዎች10 መጋቢት 2024
ኢራን ለየትኞቹ ቡድኖች ድጋፍ ትሰጣለች?
በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ከኢራን ጋር ግንኙነት አላቸው።
በጋዛ ያለው ሐማስ፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ፣ የየመን ሁቲዎች እንዲሁም መቀመጫቸውን በኢራቅ፣ በሶሪያ እና ባህሬን ያደረጉ ታጣቂ ቡድኖች ይጠቀሳሉ።
እነዚህ ታጣቂ ቡድኖች ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ በመባል የሚጠሩ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በምዕራባውያኑ አገራት በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።
ታጣቂዎቹ ቡድኖች የሚጋሩት መሠረታዊ ጉዳይ “ቀጣናውን ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ስጋት የመጠበቅ ዓላማ” እንዳነገቡም በኢራን ጥናት ላይ ተንታኝ የሆኑት የክራይሲስ ግሩፕ ባልደረባው አሊ ቫኤዝ ያስረዳሉ።
“ኢራን ትልቁ ስጋቴ ናት ብላ የምታስበው አሜሪካን ስትሆን፤ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ ኢራን በቀጣናው የአሜሪካ ተወካይ አድርጋ የምትቆጥራት እስራኤልን ነው” ይላሉ።
“ኢራን እየተጫወተችው ባለው ሚናም ይህንን አስደናቂ መረብ መፍጠሯ የኃይል ማማ ላይ አስቀምጧታል” በማለትም አገሪቷ በቀጣናው ያላትን ስፍራ ያስረዳሉ።
በዚህ ዓመት ጥር ወር መጨረሻ ገደማ በዮርዳኖስ በሰፈሩ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ ከተፈጸመው ጥቃት ጀርባ ኢራን የለሁበትም ስትል አስተባብላለች።
በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ሦስት የአሜሪካ ወታደሮች የተገደሉ ሲሆን፣ በዚህም በኢራን የሚደገፉ ቡድኖችን አቅፏል የተባለው የኢራቁ ‘እስላሚክ ሬዚስታንስ’ ኃላፊነቱን ወስዷል።
የጋዛ የአሁኑ ጦርነት ከተነሳ በኋላም በቀጣናው የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ጆ ባይ ደን አጸፋዊ ምላሻቸው የጠነከረ እንዲሆን ጫናው በርትቶባቸው ነበር።
አሜሪካ በአጸፋው ከሳምንት በኋላ በኢራን አብዮታዊ ጠባቂዎች እና ተባባሪ ሚሊሻዎች ላይ ያነጣጠረ ነው ያለችውን ጥቃትም በኢራቅ እና በሶሪያ ላይ ፈጽማለች።
እንዲሁም አሜሪካ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በመጣመር በኢራን የሚደገፉትን ሁቲዎች ኢላማ ያደረገ ነው በተባለውም ጥቃት በየመን ላይ ተፈጽሟል።
ኢራን በይፋ ጦርነት ውስጥ ከገባች ሦስት አስርት ዓመታት ቢያልፏትም በተዘዋዋሪ ግጭቶች ውስጥ በተደጋጋሚ እጇን ማስገባቷ ይነገራል።
ኢራን የውክልና ጦርነቶች እያካሄደች ነው የሚሉ ክሶችን በተደጋጋሚ ብትክድም፤ አገሪቱ ከ45 ዓመታት በፊት ካካሄደችው አብዮት ጀምሮ ታጣቂ ቡድኖችን እየደገፈች ትገኛለች።
በተለይም በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በኋላ እነዚህ ቡድኖች የኢራን አገዛዝ የብሔራዊ ደኅንነት ስትራቴጂ ዋነኛ አካልም ሆነዋል።

የኢራን ታሪክ እና ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት
በኢራን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በቀጠናው ውስጥ ያላትን ስፍራ እንዲሁም ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሻከረ ግንኙነት ፍንትው አድርጎ ለማሳየት ሁለት ሁነቶች ይጠቀሳሉ።
ኢራን በአውሮፓውያኑ 1979 ያደረገችው አብዮት ከምዕራቡ ዓለም እንድትነጠል አድርጓታል።
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት የጂሚ ካርተር አስተዳደር ኢራን በዓለም አቀፉ መድረክ ልትቀጣ እና ልትገለል ይገባል የሚል መንፈስን አዝሎ ነበር።
ለዚህም ምክንያቱ በኢራን መዲና ቴህራን ታግተው የነበሩት 52 የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ለማስለቀቅ ለአንድ ዓመት ከመሞከሩ ጋር ተያይዞ ነበር የማግለል ፖሊሲ እንዲተገበር የተደረገው። አሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ በሳዳም ሁሴን ትተዳደር የነበረውን ኢራቅን መደገፍ ጀመሩ።
ከዚያም የኢራን ኢራቅ ጦርነት ተቀስቅሶ ከአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ድረስም ዘለቀ።
ጦርነቱ የተቋጨውም ሁለቱ አገራት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው ቢሆንም፣ ኢራን እና ኢራቅን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏቸዋል።
ከስምንት ዓመታት በላይ በተደረገውም ጦርነት አንድ ሚሊዮን ሰዎች ሲገደሉ የኢራንንም ምጣኔ ሀብት አወደመው።
ከዚህም ጦርነት ጋር ተያይዞ ለወደፊቱ የሚከሰቱ ወረራዎችን መከላከል ያስችል ዘንድ የባሊስቲክ ሚሳኤል ፕሮግራምን መንደፍን ጨምሮ፣ የውክልና አጋሮችን መፍጠር የሚል ሃሳብ በኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘንድ ተፈጠረ።
በኋላ በአሜሪካ የሚመራው ኃይል በአውሮፓውያኑ 2001 በአፍጋኒስታን፣ በአውሮፓውያኑ 2003 በኢራቅ ላይ የፈጸማቸው ወረራዎች እና በተለያዩ አረብ አገራት የተቀሰቀሱ ሕዝባዊ አመጾች ይህን የኢራንን እሳቤ እያጠናከሩት መጡ።
ለመሆኑ ኢራን ምን ትፈልጋለች? ለምን?
በወታደራዊ ኃይል ረገድ ኢራን ከአሜሪካ በጣም የደከመች ናት ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ኢራን የምትከተላቸው ስልቶች ለአገዛዙ ኅልውና ቁልፍ ነው ብለው ተንታኞች ያምናሉ።
“ኢራንም ሆነች ‘አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ’ ከአሜሪካ ጋር በፍጹም ጦርነት አይፈልጉም” በማለት በመካከለኛው ምሥራቅ ኢንስቲትዩት (MEI) የኢራን ፕሮግራም መሥራች እና ዳይሬክተር የሆኑት አሌክስ ቫታንካ ያስረዳሉ።
“ኢራን አሜሪካን ከመካከለኛው ምሥራቅ እንድትወጣ ጫና እያደረገች ትገኛለች። ይህ ሌላኛውን ወገን የማዳከም የረዥም ጊዜ ስትራቴጂ ነው” ሲሉ ቫታንካ ይናገራሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘው የሰሴክስ ዩኒቨርስቲ ባልደረባ የሆኑት ካምራን ማርቲን በዳይሬክተሩ ሃሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ ኢራን በዓለም መድረክ ላይ አንደኛዋ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን ትፈልጋለችም ይላሉ።
“ጥንታዊቷ ኢራን ወይም በታሪክ ፋርስ የአስደናቂ ታሪክ ባለቤት እና ምዕራብ እስያንም ከ12 ክፍለ ዘመን በላይ የመራ ሥልጣኔ ያላት አገር ነበረች” ሲሉም የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት ካምራን ይገልጻሉ።
“ኢራን በበለጸገው የፋርስ ሥነ ጥበብ፣ ባህል እና ሥነ ጽሁፍ ያላትን ታላቅነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በቀጣናው እና ዓለም አቀፉ መድረክ ላይ ትልቅ ሚና ሊኖራት እንደሚገባ ታምናለች” ይላሉ።
ኢራን የምትደግፋቸን ቡድኖችን ምን ያህል ትቆጣጠራለች?
የውክልና ጦርነት ታደርግባቸዋለች በሚባሉት ታጣቂ ቡድኖች ላይ ያን ያህል ቁጥጥር እንደሌላት በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ኢራናዊው የፖለቲካ መብት ተሟጋች ያሳሚን ማተር ይከራከራሉ።
ምሁሩ እንደ አብነትም የሚያነሱት በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙትን የየመን ሁቲዎችን ነው።
“ሁቲዎች የኢራንን ትዕዛዝ እየተከተሉ አይደለም። እንደ ኢራን ተወካይ ሳይሆን በቀጣናው ኃይለኛ ቡድን ሆነው የመታየት የራሳቸው አጀንዳ አላቸው” ይላሉ ያሳሚን።
የክራይሲስ ግሩፑ አሊ ቫኤዝም በያሳሚን መከራከሪያ ይስማማሉ “እንደ ኢራን ያለ መንግሥት ሙሉ በሙሉ በማይቆጣጠረው ኔትወርክ የቀጣናውን ፖሊሲ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት ተግባራዊ ማድረጉ ችግር ነው” ይላሉ።
ቫኤዝ የኢራን ኃይል የተጋነነ ነው ብለው ያስባሉ “ይህንን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የሚካሄደውን የቼዝ ጨዋታ በበላይነት የምትመራው ኢራን ናት የሚል አስተሳሰብ አለ። ኢራንም ሆነ አጋሮቿ እስራኤልን ጫና ውስጥ አስገብተው የተኩስ አቁም ስምምነት ውስጥ እንድትገባም ሆነ አሜሪካን ከቀጣናው ጠቅልላ እንድትወጣ በማድረግ ቁልፍ የሚባሉ ዓላማዎቻቸውን ማሳካት አልቻሉም” ይላሉ።
ሆኖም ኢራንን ማሳነስ አይገባም የሚሉት ቫኤዝ፣ ዋቢ የሚያደርጉትም የኑክሌር መርሃ ግብሯን በማንሳት ነው። “ኢራን ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ ከምትገኝበት በላቀ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከአጋሮቿ እና በተወካዮቿ በኩል ከምታደርገው በበለጠ የኑክሌር መርሃ ግብሯ ለእስራኤል እና ለምዕራቡ ዓለም ችግርን ሊደቅን ይችላል” ይላሉ።

“ሦስተኛው የዓለም ጦርነት?”
በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ጥቃቶች እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ተከትሎ በርካቶች “ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” ይከሰት ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች እየተጫረባቸው ይገኛል። በበይነ መረብም ላይ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚሉ ፍለጋዎችም እየተበራከቱ ነው።
አሌክስ ቫታንካ ኢራን በጥንቃቄ ልትራመድ ይገባል ይላሉ፤ ምክንያቱም አገሪቷ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ እና በሴቶች እየተመራ ባለ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች እየተናጠች መገኘቷን በመጥቀስ ነው።
“የኢራን ገዥ በቀጣናው እያካሄደው ያለው ነገር ምንም ትርጉም አልሰጥ ያለው የተቆጣ የኢራን ሕዝብ አለ” ይላሉ።
በተመሳሳይም ምዕራቡ ዓለምም ከኢራን ጋር ጦርነት እንደማይፈልግም በአውሮፓ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ ፕሮግራም ምክትል ኃላፊ የሆኑት ኤሊ ገራንማዬህ ይናገራሉ።
“ለቀጣዩ ምርጫ እየተዘጋጁ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ይህንን ማድረግ አይችሉም። እስራኤልም በአሁኑ ወቅት በጋዛ ከምታደርገው ዘመቻ [ከማያባራ ጥቃት] ጋር በተያያዘ ባላት ተጋላጭነት የተነሳ ግጭት ውስጥ መግባት አትችልም” ይላሉ።
ኤሊም ሆነ ሌሎች ተንታኞች እንደሚያምኑት ጦርነት ውስጥ መግባት የየትኛውም ወገን አጀንዳ አይደለም።
“አሜሪካ እና ኢራን የቀጣናውን ተዋናዮች እርስ በርስ ለመነቋቆር እና ጥቃት ለመፈጸም እየተጠቀሙባቸው ነው። ቀጥተኛ ጦርነት ውስጥ ላለመግባት እና መውጣት ከማይችሉበት ጥፋትም እንዳይደርስ በሚል ነው ሆን ብለው ይህንን ስልት እየተጠቀሙ ያሉት” ሲሉም ያስረዳሉ።
ሆኖም ባለፉት አስር ዓመት የታየው ትርምስ አደጋ እንዳለው አስጠንቅቀው “ ዋሽንግተን እና ቴህራን ጠንከር ያለ ዲፕሎማሲ ማካሄድ ካልቻሉ ወደ ጦርነት መጎተታቸው የማይቀር ነው። እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑት ዋና ዋና ተዋናዮች ቁጥጥር ካልተጠነቀቁ እና ቁጥጥር ካልተደረገባቸው እስካሁን ካየነው የከፋ ሁኔታ መፈጠሩ አይቀርም” ይላሉ ገራንማዬህ።