ጥቃት የተፈጸመበት መኪና

ከ 2 ሰአት በፊት

በጋዛ ሰራተኞቸቻው የተገደሉባቸው የወርልድ ሴንትራል ኪችን የረድዔት ድርጅት ኃላፊ የእስራኤል ኃይል “በታቀደ መልኩ በመኪኖቻቸው ላይ ጥቃት ፈጽሟል” አሉ።

በእያንዳንዱ መኪና ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተፈጽሞም ሰባት ሰራተኞቻቸው እንደተገደሉም የድርጅቱ ኃላፊ ሆዜ አንድሬስ ገልጸዋል።

ሰኞ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት በስህተት እንዳልሆነ የሚናገሩት ኃላፊው፣ ስለ ሰራተኞቻቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለእስራኤል ኃይል ቀድመው ማሳወቃቸውንም በድጋሚ ተናግረዋል።

እስራኤል የረድዔት ሰራተኞቹ ተሳፍረው ይሄዱበት በነበሩ መኪኖች ላይ በፈጸመችው ጥቃት አውስትራሊያዊ፣ ካናዳዊ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካዊ እና ፍልስጤማዊ ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች ተገድለዋል።

እስራኤል ጥቃቱ “ትልቅ ስህተት ነው” ስትል ይቅርታ የጠየቀች ሲሆን ገለልተኛ ምርመራ ለማድረግም ቃል ገብታለች።

እንደ ረድዔት ተቋሙ ገለጻ የእርዳታ መኪኖቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው ዴይር አል ባላህ ከተሰኘው የእርዳታ ማከማቻ በባህር በኩል ለጋዛ የሚሆን ከ100 ቶን በላይ ምግብ አውርደው ሲወጡ ነው።

ጥቃት የተፈጸመባቸው ሦስቱ የእርዳታ መኪኖች የረድዔት ድርጅቱን አርማ በግልጽ የሚያሳዩ ነበሩ።

የወርልድ ሴንትራል ኪችን መስራች ዝነኛው ሼፍ ሆዜ “መጥፎ ዕድል፣ ውይ ቦምቡን በተሳሳተ ቦታ ጣልነው፣ የሚባል አይደለም” ሲሉም ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ሰራተኞች
የምስሉ መግለጫ,በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ሰራተኞች

“በእውነቱ ቀጥተኛ ጥቃት ነው።በተሽከርካሪዎቻችን ላይ ያለው አርማችን በግልጽ ይታያል እንዲሁም የሰራተኞቻችን እያንዳንዷ እንቅስቃሴ በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አባላት ዘንድ ይታወቃል” ሲሉ ሼፍ ሆዜ የተነጣጠረ ጥቃት እንደነበር ከእስራኤል ቻናል 12 ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የተገደሉት የ6ቱ የረድዔት ሰራተኞች አስከሬን ከጋዛ ወደ ግብጽ በኩል እንዲወጣ ተደርጎ ወደየአገራቸው ተወስዷል።

የፍልስጤሙ ሰራተኛ በትውልድ ከተማው ራፋህ ማክሰኞ ዕለት ተቀብሯል።

በግዛቲቷ ዋነኛ የእርዳታ አቅራቢ የሆነው ወርልድ ሴንትራል ኪችን አገልግሎቱን ማቋረጡን ተከትሎም በጋዛ ሰርጥ የሚደርስ ሰብዓዊ እርዳታ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ሁኔታውን ለመገምገም በምሽት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለ48 ሰዓታት አቁሞ እንደነበር አስታውቋል።

እስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጥቃቱን “ያልታሰበ” ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል የረድዔት ሰራተኞችን ደህንነት ለመጠበቅ በቂ ስራ እየሰራች አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል።