ክርስቶፈር ከተሰጠው ዕውቅና ጋር

4 ሚያዚያ 2024, 09:38 EAT

ተሻሽሏል ከ 1 ሰአት በፊት

ሩሲያ ላይ የሳይበር ጥቃት ያደረሰ የመረጃ መንታፊዎች ቡድን ከዩክሬን ጦር የዕውቅና ሽልማት ተበረከተለት።

‘ዋን ፊስት’ የሚባለው ቡድን የሩሲያ የጦር መሣሪያ ፋብሪካዎችን እና ካሜራዎችን በመጥለፍ መረጃዎችን ሰርቋል።

ዕውቅናው አወዛጋቢ እና ዘመናዊውን የጦርነት አካሄድ ያሳያል ተብሏል።

መንግስታት ሲቪል መረጃ መንታፊዎችን የሚያበረታቱበት አካሄድም ስጋት የጫረባቸው በርካቶች ናቸው።

ከመረጃ መንታፊዎቹ አንዱ የሆነው “ቮልቴጅ” ሥራውን የሚያጧጡፈው አሜሪካ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ነው።

በትክክለኛ መጠሪያ ስሙ ክሪስቶፈር ኮርትራይት የሚባለው መረጃ መንታፊ የአይቲ ባለሙያ ሲሆን መቀመጫውን ሚቺጋን አድርጓል።

የ53 ዓመቱ መረጃ መንታፊ ለዩክሬን ያደረገው ጥረት ዕውቅና በማግኘቱ መደሰቱን ገልጿል።

‘ዋን ፊስት’ ዩናይትድ ኪንግደም፣ አሜሪካ እና ፖላንድን ጨምሮ ከስምንት አገራት የተወጣጡ የመረጃ መንታፊዎች ያቋቋሙት ነው። በደርዘን የሚቆጠር የሳይበር ጥቃት ያደረሱ ሲሆን ደስታቸውንም በማህበራዊ ሚዲያ ይገልጻሉ።

“ለሠራዊቱ ዕድገት እና ወሳኝ እንቅስቃሴ ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ” የሚሉት የምስክር ወረቀቶቹ ለሁሉም አባላት ተልከዋል። የዩክሬን የአየር ኃይል አዛዥም ፊርማቸውን አኑረውበታል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።

ዩክሬን ወደ ጦርነት ከገባች ጀምሮ በአወዛጋቢ ሁኔታ በጎ ፈቃደኛ መረጃ መንታፊዎች ሩሲያን እንዲያጠቁ እያበረታታች ትገኛለች። ኦፊሴላዊ ሽልማቶችን ለሌላ አገር ዜጎች መላኳ አወዛጋቢ ከመሆኑም በላይ የዘመኑ ማሳያ ተደርጎም እየታየ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካን ጨምሮ በርካታ አገራት ለመልካም ነገር መረጃ ለሚመነትፉ ኦፊሴላዊ ሽልማት ቢኖራቸውም ለጥፋት እና ምናልባትም ለወንጀል የሚደረግን የመረጃ ምንተፋ ዕውቅና በመስጠት ዩክሬን የመጀመሪያው እንደሆነች ይታሰባል።

በዩክሬን እና በጋዛ ግጭት ውስጥ የተስፋፋውን የምንተፋ ተግባር ተከትሎ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (አይሲአርሲ) የሲቪል መንታፊዎችን በመጠቀም እና ማበረታታት ዙሪያ ባለፈው ጥቅምት ማስጠንቀቂያ አውጥቷል። የጄኔቫ ስምምነቶች ላይ የተቀመጡትን የጦርነት ሕጎች እንዲተገበሩ በማለትም አትሟቸዋል።

የፖላንድ የመረጃ መንታፊ ቡድን አባል

ዩክሬን ለውጭ መረጃ መንታፊዎች የሰጠችው ሽልማት ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ የሳይበር ደህንነት ፍልስፍና ደራሲ የሆኑት ዶ/ር ሉካስ ኦሌይኒክ ተናግረዋል።

“ሽልማቶችን መስጠት በወታደሮች እና በሲቪሎች መካከል ያለውን ልዩነት የበለጠ ሊያደበዝዝ ይችላል,። ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በጦርነት ውስጥ የሲቪሎችን ተሳትፎ ለመገደብ እና ለማቆም ያቀረበውን ጥሪ ሊያኮሰምነው ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ መሸርሸር በረጅም ጊዜ አደገኛ ውጤት ይኖረዋል” ብለዋል።

ዶ/ር ኦሌይኒክ አክለውም ሳይበር ጥቃት እንደ ጦርነት መቆጠሩ እና ማንም ሰው በበይነ መረብ ትግሉን መቀላቀል የሚችልበት ዕድል መኖሩ “የዘመናችን ማሳያ” ነው ብለዋል።

ሩሲያን ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት መረጃ መመንተፍ የጀመረው ክሪስቶፈር፤ ለዓላማው ማደሩን እና ብዙ መስዋዕትነት መክፈሉን ይገልጻል።

“ለዚህ ብዬ ሥራዬን አጥቻለሁ። ዩክሬን እንድታሽንፍ ህይወቴን በሙሉ የቆጠብኩትን ገንዘብ አጥፍቻለሁ። ሽልማት እውነተኛ የሞራል ማበረታቻ ነው” ሲል ከመኖሪያ ቤቱ ቢሮ ሆኖ ገልጿል።

ሽልማቶቹ የትኞቹ የሳይበር ጥቃቶች በጣም ጠቃሚ እንደሆኑ አይገልጽም። ቮልቴጅ ግን እጩዎች እንደሆኑ የሚያስባቸው ሦስቱን ነው።

የዩክሬን ወረራ እንደተጀመረ ዋን ፊስት በዩክሬን የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የደህነነት ካሜራዎችን አካላዊ እና የሳይበር ደህንነት ሲለይ ለወራት አሳልፏል።

በኋላም ካሜራዎቹን ተጠቅመው የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን ወታደሮችን ለመከታተል እየተጠቀሙባቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በዚህም ቡድኑ ካሜራዎቹን ከሥራ ውጭ እንዲሆኑ እገዛ አድርጓል።

በሩሲያ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ክሪሚያ የሚገኙ ካሜራዎችን ሰርጎ በመግባት የሩስያ ታንኮችን እና መሣሪያዎች ድልድይ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያሳየውም ዋን ፊስት ነው።

ዋን ፊስት የሩሲያን ታንኮች እንቅስቃሴ ለመመንተፍ ችሏል

በቅርቡ ክሪስቶፈር እና ሌሎችም መረጃ መንታፊዎች ታዋቂ የሆነውን የሩሲያ የጦር መሣሪያ አምራች ጠልፈው 100 ጊጋባይት መረጃዎችን ሰርቀዋል። የዩክሬን ባለስልጣናት በዚህ ተግባር በይፋ ደስታቸውን ገልጸዋል።

“ወደ ዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የተላለፈው መረጃ ነባር እና ተስፋ ሰጭ ወታደራዊ እድገቶችን የሚያመለክቱ ስዕሎችን፣ ዝርዝር መረጃዎችን፣ የፈጠራ ባለቤትነትን እና ሶፍትዌሮችን ይዟል” ብሏል።

የተሰረቀው መረጃ ለሞስኮ “ትልቅ ጉዳት” ነው ስትል ዩክሬን ገልጻለች። አሃዙ ላይ እንዴት እንደደረሰች ባታሳውቅም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ አለው ስትል አክላለች።

የዩክሬን ግጭት የሳይበር ምንተፋ እንዲጨምር አድርጓል። በአብዛኛው ደግሞ ከዩክሬን ደጋፊዎች በኩል የተደረገ ነው። እንደ አኖኒመስ ያሉ የመረጃ መንታፊ ቡድኖች ሩሲያ ላይ ቢያነጣጥሩም ሞስኮ ግን ጉዳዩን አጣጥላዋለች።

በአንዳንድ አጋጣሚዎች የቴሌቭዥን እና የራዲዮ ጣቢያዎች ተጠልፈው በድረገጽ ላይ ያሉ መረጃዎች ተበላሽተዋል።

የሩሲያ ባለስልጣናትም ዩክሬንን ለማጥቃት እንደ ኪልኔት ካሉ መንታፊ ቡድኖች ጋር በመተባበር ተከሰዋል። ሩሲያ ግን ከመንታፊዎቹ ጋር ምንም ኣይነት ግንኙነት እንዳላት አላመነችም።

ኪልኔት መሪ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት የለንም ይላል

በሁለቱም ወገን ያሉ መረጃ መንታፊዎች ጦርነቱ መጓተቱን ተክትሎ እየተበታተኑ ነው። ዋን ፊስት ግን ሩሲያን ማጥቃቱን ከመቀጠሉም በላይ ዒላማዎችን በመምረጥ ረገድ ከዩክሬን ኃይሎች ጋር በቅርበት እየሠራ ነው።

የኦክስፎርድ ኢንፎርሜሽን ላብስ ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የቻተም ሃውስ ሳይበር ፖሊሲ ጆርናል አዘጋጅ የሆነችው ኤምሊ ቴይለር የምንተፋ ሽልማቶች የበጎ ፍቃደኞች የሳይበር ጥቃት በግጭቶች ውስጥ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የነበረውን እሳቤ የሚቀይር እንደሆነ ይስማማሉ።

“መንግሥታት ብዙውን ጊዜ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት በሳይበር-ጥቃት ውስጥ ቀጥተኛ እርምጃ እንዳይወስዱ ያበረታታሉ። ይህም መጋጋልን ወይም ያልተፈለገ ውጤትን በመፍራት የሚደረግ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ጦርነት ያልተለመደ የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚከናወንበት በመሆኑ የዩክሬን ወረራም ከዚህ የተለየ አይደለም” ብላለች።

“አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ክስተቶች ቀደም ሲል የተከለከሉ ጉዳዮችን እንደገና እንዲጤኑ ያስገድዳሉ።”

ቡድናቸው ከዩክሬን ጦር ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፈጠሩን ክሪስቶፈር ተናግሯል። “እነሱ ሐሳቦችን ይልኩልናል እኛ ደግሞ አማራጮችን እንልካቸዋለን። ነገር ግን ምንም አይነት እርዳታ ወይም የገንዘብ ድጋፍ አይሰጡንም ምክንያቱም ይህ የሚያልፈው መስመር አለ ብዬ አስባለሁ” ብሏል።

ክሪስቶፈር ወታደራዊ ዕውቅናውን መቀበል አከራካሪ እንደሆነ ቢገነዘብም፤ ለዩክሬን ሲል መረጃ መመንተፉን እንደሚቀጥል ገልጿል።