አስም

ከ 4 ሰአት በፊት

የዩናይትድ ኪንግደም ሳይንቲስቶች አስም ሳምባ ላይ ከሚያደርሰው ጉዳት ጀርባ አዲስ ምክንያት ማግኘታቸውን ይፋ አድረጉ።

አስም ሲያጋጥም የአየር መተላለፊያዎችን የሚሸፍኑ ሴሎች እንደሚጎዱ ጥናታቸው ያሳያል።

ይህንን ለመከላከል የሚሰጡት መድኃኒቶች የደረሰውን አደጋ ከመቆጣጠር ይልቅ የጉዳቱን ድግግሞሽ ሊያስቀሩ ይችላሉ ሲል የለንደኑ የኪንግስ ኮሌጅ ተመራማሪዎች ለሳይንስ ጆርናል ተናግረዋል።

አስም ያለባቸው ሰዎች የአየር መተላለፊያዎች እንደ አበባ ፍሬ ብታኝ፣ የቤት እንስሳት እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ላሉ ነገሮች ተጠቂ ናቸው። በዚህም በመቆጣት እና በማበጥ የማሳል እና ትንፋሽ ማጣትን ጨምሮ ሌሎች ምልክቶችን ያስከትላል።

የተለመዱት መድኃኒቶች ወይም መተንፈሻን የሚከፍቱና የሚሳቡ ማስታገሻዎች እብጠቱን በመቀነስ የአየር መተላለፊያ ቱቦዎችን ክፍት ለማድረግ ይረዳሉ።

ተደጋጋሚ ጉዳት ግን ቋሚ የሆነ ጠባሳ እና የአየር መተላለፊያ መንገዶች እንዲጠቡ ሊያደርጉ ይችላሉ።

ይህ ሲያጋጥም በመተንፈሻ ቱቦ ዙሪያ ያለው ለስላሳ ጡንቻ መጭመቅ እና መጨናነቅ ይጀምራል። ይህም ብሮንኮኮንስትሪክሽን በመባል ይታወቃል።

የለንደን የኪንግስ ኮሌጅ ተመራማሪዎች አይጦችን እና የሰው የሳንባ ናሙናዎችን በመጠቀም ይህንን ሂደት በዝርዝር አጥንተዋል።

የምርምር ቡድኑ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆዲ ሮዘንብላ ብሮንኮኮንስትሪክሽን የአየር ቱቦዎችን ሽፋን በመጎዳቱ የረዥም ጊዜ እብጠት፣ ቁስሎች እና ኢንፌክሽኖችን በማስከተል ተጨማሪ ጉዳቶችን ያመጣል ብለዋል።

በሽፋኑ ላይ የሚደርሰው ጉዳት እስከ አሁን ችላ ተብሎ አንደቆየ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህ ሽፋን እንደ ኢንፌክሽኖች ካሉ የሚጠብቅ የሰውነት መከላከያዎች የመጀመሪያው ቢሆንም አስም በሚያጋጥመበት ወቅት ይጎዳል” ብለዋል ፕሮፌሰር ሮዘንብላ።

“ይህ የማያቋርጥ መቁሰል እየቀጠለ ከመሆኑም በላይ አስከፊ ዑደት ጭምር ነው።”

“ጉዳቱን መከልከል ከቻልን ይህ ጥቃት ፈጽሞ ሊቆም ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ እያጠኑ ያሉት አንድ የመከላከያ ሕክምና ጋዶሊኒየም የተባለ ንጥረ ነገር ነው። ይህም በያንስ በአይጦች ላይ ውጤታማ መስሏል።

በሰዎች ላይ በመሞከር ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ለማየት ብዙ ተጨማሪ ስራ ያስፈልጋል። ይህም ዓመታትን ይወስዳል።

የአስም እና የሳንባ ዩናይትድ ኪንግደም የምርምር እና ፈጠራ ዳይሬክተር ዶክተር ሳማንታ ዎከር “ይህ ግኝት አስም ላለባቸው ሰዎች በጣም አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ የሕክምና አማራጮችን ለመመርመር አዳዲስ በሮችን ይከፍታል” ብለዋል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አስም ያለባቸው ሰዎች የታዘዙትን መድሃኒት በትክክል መጠቀማቸውን እንዲቀጥሉ ምክሩን አስተላልፏል።

“ነባር የአስም ሕክምናዎች የማይሰሩላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ እናውቃለን። የአስም መንስኤዎችን በተሻለ መንገድ የሚፈቱ አዳዲስ ህክምናዎችን ለማግኘት ለምርምሮች የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።”

በዩናይትድ ኪንግደም ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስም አለባቸው።