በዘር ጭፍጨፋው የተገደሉ ሰዎች ፎቶ
የምስሉ መግለጫ,በዘር ጭፍጨፋው የተገደሉ በርካታ ሰዎች ፎቶ በሙዚየሙ ተሰቅሎ ይታያል

5 ሚያዚያ 2024, 07:18 EAT

ስም፡ ኡሙቶኒ አሪዬን

ዕድሜ፡ 4

የምትወደው ምግብ፡ ኬክ

የምትወደው መጠጥ፡ ወተት

አሟሟት፡ ዐይኗ እና ጭንቅላቷ ላይ በስለት ተወግታ

የኡምቶኒ ግዙፍ ፎቶ ግድግዳው ላይ ተሰቅሏል። ታሪኳ የታተመበት አነስተኛ አትሮነስ ከፎቶው በታች ቆሟል።

ወላጆቿ ንጽህናዋን የምትወድ ልጅ ነበረች ይሏታል።

ይህ የኪጋሊ ጄኖሳይድ ሚሞሪያል (የዘር ማጥፋት መታሰቢያ ሙዚየም) ነው። የሩዋንዳ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች ጭፍጨፋ ቁልጭ ብሎ የሚታይበት።

ይህ ሥፍራ የአሪዬን እና ሌሎች 250 ሺህ ሰዎች አፅም ያረፈበት ነው።

የኪጋሊ ጄኖሳይድ ሜሞሪያል

ምንም እንኳ ወደ ሙዚየሙ ያመራሁበት ቀን ብራ ቢሆንም አሁንም ትዝ የሚለኝ ጭፍግግ ያለ ሰማይ ነው።

ኪጋሊ ጄኖሳይድ ሚሞሪያልን ስጎበኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሩዋንዳ ለሁለት ሳምንታት ብቆይም ወደ ሙዚየሙ ለመሄድ አንድ ሳምንት ፈጅቶብኛል። ለወዳጅ ዘመዶቼ ልጎበኘው ነው ብዬ ስነግራቸው “ብቻህን?” ይሉኛል። ይህ የማላውቀው ፍርሀት ፈጠረብኝ።

አንድ ሐሙስ ጠዋት ለመሄድ ቆረጥኩ። የሥራ ባልደረባዬን አብረን እንሂድ ብለው “እኔ ከዚህ ቀደም አይቼዋለሁ፤ ልደግመው አልፈልግም” አለኝ።

“ብቻ የሕፃናቱ ቦታ ስትደርስ ስሜትህን ለመቆጣጠር ሞክር” የባልደረባዬ ምክር ነበር።

ካሜራ፣ መቅረፀ-ድምፅ እና ሌሎች ምስል እና ድምፅ የሚቀዱ መሣሪያዎች እንደማይፈቀዱ ስለማውቅ ማስታወሻ ደብተሬን ብቻ ነው ይዤ ያቀናሁት።

ፍተሻው ጠንካራ ነበር። እሱን አልፌ ወደ እንግዳ መቀበያው አመራሁ። መግቢያ በነፃ ነው። ነገር ግን እርዳታ ማድረግ ለሚሹ ሳጥን ተቀምጧል። አሊያም ሙዚየምን ጆሮ ላይ በሚሰካ መሣሪያ እየታገዙ ማየት የሚሹ ‘ኢርፎን’ መከራየት ይችላሉ።

እንግዳ ከሚቀበሉ አስተናጋጆች መካከል አንዷ ወደ እኔ ቀረብ አለች።

“ሩዋንዳዊ ነዎት?”

“አይደለሁም።”

“እሺ። ከየት ነው የመጡት?”

“ከኢትዮጵያ!”

የጉብኝቱ የመጀመሪያ ደረጃ ከእንግዳ መቀበያው አጠገብ ካለች አንዲት ጠባብ ክፍል ተቀምጦ አጭር ቪድዮ ማየት ነው።

ቪድዮው ሙዚየሙን ለምን ማቋቋም እንዳስፈለገ ያስረዳል። በዘር ጭፍጨፋው ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ያጡ ሩዋንዳውያን ሙዚየሙን መጎበኝት እንደሚያዘወትሩ እንባ እየተናነቃቸው ያስረዳሉ።

ይህን ቪድዮ ከተመለከትን በኋላ ወደ ሁለተኛው እና ዋናው እንግዳ መቀበያ አመራን።

ዋናው የእንግዳ መቀበያ ሲደርሱ በርካታ አስተናጋጆች አሉ። ሙዚየሙ የት ተጀምሮ የት እንደሚጠናቀቅ ለማስረዳት በተጠንቀቅ የቆሙ ናቸው።

ምን እንደሚጠብቀኝ አላውቅም። ብዕሬን እና ማስታወሻዬን አቀባብዬ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ። የመጀመሪያው ክፍል ቁጥር 15 ነው።

“Before the Genocide” [ከዘር ማጥፋቱ በፊት] ይላል። ያን ሁሉ ነብስ ከቀጠፈው ዘር ማጥፋት በፊት የነበረውን ታሪክ የሚተነትን ክፍል ነው።

ሩዋንዳ በአውሮፓውያኑ 1899 ነው በጀርመን ቅኝ የተገዛችው። ከዚያ በኋላ በ1919 በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ውሳኔ መሠረት የቤልጂየም ግዛት እንድትሆን ተወሰነ።

ከዘር ማጥፋቱ በፊት የሩዋንዳ ሕዝብ በቅኝ ግዛት ሳቢያ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች እንዴት እንደተከፋፈለ የሚያስረዱ ታሪኮች የሙዚየሙ ግድግዳ ላይ ተለጥፈዋል።

ከሩዋንዳ ሕዝብ 85 በመቶው ሁቱዎች ቢሆኑም፣ ቱትሲዎች ለዘመናት የበላይነቱን ይዘው ቆይተዋል። በአውሮፓውያኑ 1959 ሁቱዎች የቱትሲን አገዛዝ ገርስሰው ሥልጣን ሲይዙ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቱትሲዎች ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዱ።

በዘር ጭፍጨፋው ያለቁ ሰዎች አፅም

ስደት ላይ የነበሩ ቱትሲዎች ግንባር መሥርተው ሩዋንዳን ፓትሪዮቲክ ፍሮንት [አርፒኤፍ] የተሰኘ አማፂ ቡድን አቋቁመው በ1990 ሩዋንዳን ወረሩ። ግጭቱ ለሦስት ዓመታት ከቀጠለ በኋላ የሰላም ስምምነት ተደረሰ።

በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 6/1994 ምሽት ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሀቢያሪማና እና የቡሩንዲው አቻቸው ሳይፕሪየን ንታርያሚራን የጫነች አውሮፕላን ተመትታ ወደቀች። ሁለቱም ፕሬዝዳንቶች ሁቱዎች ነበሩ። ሁለቱም ፕሬዝዳንቶች በአንድ ምሽት ተገደሉ።

ይሄኔ ነው አክራሪ ሁቱዎች ይህን የፈፀመው አርፒኤፍ ነው፤ ቱትሲዎችን ከምድረ-ገፅ እናጠፋለን በሚል የተቀናጀ ጭፍጨፋ የጀመሩት። አርፒኤፍ አውሮፕላኗ ተመትታ የወደቀችው በሁቱዎች ነው፤ ይህ የሆነው ለዘር ማጥፋቱ እንዲመች ነው ይላል።

የመንግሥት ተቃዋሚዎች ስም ዝርዝር፤ ገጀራ እና ክላሺንኮቭ ለታጠቁ ሚሊሻዎች ተሰጠ። ሚሊሻዎቹ ወደ ተሰጣቸው አድራሻ አቅንተው ተቃዋሚዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ያለርህራሄ ጨፈጨፏቸው።

ጎረቤት ጎረቤቱን ገደለ። አንዳንድ ሁቱዎች ቱትሲ ሚስቶታቸውን ገደሉ። ካልገደልናችሁ እንገደላለን የሚል ነበር ምክንያታቸው። ሕፃናት፣ ሴቶች እና የዕድሜ ባለፀጋዎች ሳይቀሩ የአክራሪ ሁቱዎች ስለት እና ጥይት ሰለባ ሆኑ።

በወቅቱ መታወቂያ ላይ ጎሳ ምንነት ይጠቀስ ነበርና ሚሊሻዎች መንገድ ላይ ኬላ ዘርግተው ቱትሲዎችን በገጀራ ማረድ ያዙ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ቱትሲ ሴቶች ታፍነው ተወስደው የወሲብ ባሪያ ሆነው እንዲቀመጡ ሆኑ።

800 ሺህ ቱትሲዎች እና ለዘብተኛ ሁቱዎች በሩዋንዳው የዘር ፍጅት ተገድለዋል። በኪጋሊ ጄኖሳይድ ሚሞሪያል ብቻ የ250 ሺህ ሰዎች አጽም አርፏል።

በጅምላ ጭፍጨፋው አካሉ ላይ ጉዳት የደረሰበት ሩዋንዳዊ

በርጩማው

ሙዚየሙን ይህን ሁሉ ታሪክ በፎቶ እና ቪድዮ አስደግፎ አስቀምጧል። አልፎ አልፎ ከቆዳ የተሠሩ በርጩማዎች ተቀምጠዋል። የበርጩማዎቹ ጥቅም የገባኝ አንዲት ምዕራባዊት ጎብኚ ፊቷን በመሀረብ ሸፍና ቁጭ ብላ ስትንሰቀሰቅ ስመለከት ነው።

ይደክማል። በጣም ይደክማል። ጉልበት ሳይሆን ነብስ ትደክማለች። የሰውን ልጅ የጭካኔ ጥግ ቁልጭ ብሎ ሲያዩት እንዴት ነብስን አይደክማት?

ቀጥሎ የገባሁበት ክፍል ቁጥር ሥፍር የሌላቸው ሰዎች ፎቶ በገመድ የተሰጣበት ነው። እኒህ ሁሉ ሰዎች በማንነታቸው ብቻ ሕይወታቸውን አጥተዋል? ቀና ስል ጥቁር ኮርኒስ ይታየኛል። ከጣራው ማዕዘናት ግድግዳው ላይ ያነጣጠሩ አምፖሎች አቅመ ደካማ ብርሃን ይረጫሉ። ዝቅ ብል የሚታየኝ ጨፍጋጋ ቀለም ያለው ምንጣፍ ነው። ውጭው ናፈቀኝ።

‘በሪያል ቻምበር’ [የቀብር ክፍል] የተሰኘው ክፍል ደግሞ የሰው ልጅ የጭንቅላት ቅል እና አጥንት ተደርደሮ የሚታይበት ነው። ይህ ክፍል በግማሽ ጨረቃ መልክ ስለተሠራ አሰቃቂውን ትዕይንት ማየት የማይሹ ሰዎች በጨረፍታ ተመልክተው መሻገር ይችላሉ።

ተሻግሮ ካለው ክፍል በዘር ጭፍጨፋው ያለቁ ሰዎች ሲገደሉ ይዘዋቸው የነበሩ የግል ንብረቶች ተሰቅለዋል። ቲሸርት፣ ሕፃናት ለብሰዋቸው የነበሩ የተለያዩ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች ማሊያዎች፣ ቁምጣ፣ የእጅ አምባር፣ የአንገት መስቀል፣ ጫማ፣ ቦርሳ፣ ቀበቶ፣ ቁልፍ፣ መታወቂያ . . .

* * *

ፍራንሲን፣ በርናርዲን፣ ዴቪድ፣ ፊደል፣ ሻነል፣ አሪዬን. . . የፈራሁት ክፍል ደረስኩ። ጓደኛዬ ያስጠነቀቀኝ ወዶ አይደለም።

ይህ ክፍል ‘የከሰመው ነገ’ አሊያም ‘Tomorro lost’ ይሰኛል። በዘር ጭፍጨፋው ከተገለዱ ሕፃናት መካከል የተወሰኑት ፎቶ እና ታሪካቸው በጉልህ የሚታይበት ክፍል ነው።

ስም፡ ኢንጋቢሬ ፊደል

ዕድሜ፡ 9

የሚወደው ስፖርት፡ እግር ኳስ

የሚወደው ምግብ፡ የተጠበሰ ድንች

የሞቱ ምክንያት፡ ጭንቅላቱን በጥይት ተመትቶ

መቀመጥ አሰኘኝ። ከቆዳ የተሠራውን በርጩማ ፈለግኩት። ብርቱካናማ ቀለም ከተቀባው ክፍል ውስጥ የለም። የሆነ ነገር ያፈነኝ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል። መውጣት አለብኝ።

ጎብኝዎች ሙዚየሙ ውስጥ የተሰቀሉትን ፎቶዎች ሲጎበኙ

ደግነቱ ወደ ማጠናቀቂያው ደርሻለሁ። ሙዚየሙ ለትምህርት እንዲሆን የሌሎች አገራትን ጅምላ ጭፍጨፋ የሚያሳዩ ክፍሎች አሉት።

በጀርመን ቅኝ ግዛት ውስጥ የነበሩት የደቡብ ምዕራብ አፍሪካ የሄሬሮ እና ናማ ሕዝቦች የዘር ጭፍጨፋ፤ በናዚ ጀርመን አይሁዶች ላይ የተፈጸመው የዘር ፍጅት [ሆሎኮስት]፤ የካምቦዲያው የዘር ጭፍጨፋ፤ የባልካንስ. . . እና ሌሎችም የዘር ጭፍጨፋዎች ታሪክ ተመዝግቦ ተቀምጧል።

ሩዋንዳውያን ከዚህ ታሪክ ከማይረሳው የዘር ጭፈጨፋ ለማገገም ብዙ ተራምደዋል፤ ገና ብዙም ይቀራቸዋል።

“ሕይወት ከጄኖሳይድ በኋላ በፍፁም ቀላል አይደለም። ደግሞ ብቻህን ተርፈህ ምንም ነገር ሳይኖርህ ሲቀር። ሁላችንም ደግም፣ ክፉም የማድረግ አቅም አለን። መውደድም፣ መጥላትም እንችላለን። የትኛውን ነው የምንመርጠው የሚለው ነው ወሳኙ። አንድ ሰው ጥላቻን ከመረጠ ጥላቻ ያጭዳል። ፍቅርን ከመረጠ ደግሞ ፍቅርን ያጭዳል” ይላል ከዘር ጭፍጨፋው የተረፈው ካሬንዚ ቴዎኔስቴ።

ካሬንዚ፣ ሁስ አኒ ሞኒክ እና ሌሎችም ከዘር ጭፍጨፋው የተረፉ ሩዋንዳዊያን ታሪክ በቪድዮ ተቀረፆ ጎብኚዎች እንዲመለከቱት ተዘጋጅቶ ተቀምጧል።

“ጎረቤትህን መውደድ አለብህ። ጊዜ ደግሞ አስተማሪ ነው። ይኸው ገዳዮቻችን ምንም እንዳላተረፉ እያየን ነው። ይኽው አብረን እየኖርን ነው” ትላለች ሁስ አኒ ሞኒክ።

የጭፍጨፋው ሰለባዎች አፅም ያረፈበት ሥፍራ
የምስሉ መግለጫ,ዘመድ አዝማዶች እንዲሁም ጎብኝዎች በሙዚየሙ ቅጥር ግቢ በሚገኘው ጅምላ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ያስቀምጣሉ

ድኅረ-ጄኖሳይድ

ተባበሩት መንግሥት እና ቤልጂየም በሩዋንዳ ጦረ ቢኖራቸውም ግድያውን የማስቆም ኃላፊነት አልተሰጣቸውም። 10 የቤልጂየም ወታደሮች ከተገደሉ በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት እና የቤልጂየም ኃይሎች ሩዋንዳን ጥለው ወጡ።

የሁቱ መንግሥት ወዳጅ የነበረችው ፈረንሳይ ዜጎቿን ለማስወጣት ልዩ ኃይል በመላክ የራሷን ካምፕ ብታቋቁምም በሥፍራው የነረበውን ግድያ ባለማስቆም ትወቀሳለች።

አሜሪካ ደግሞ በሶማሊያ ከደረሰባት ኪሳራ በኋላ በአፍሪካ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ ላለመግባት የቆረጠችበት ጊዜ ነበር።

የሩዋንዳ ፓትሪዮቲክ ግንባር [አርፒኤፍ] በኡጋንዳ ጦር ታግዞ እስከ ሐምሌ 1994 ወደ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ ገሰገሰ።

ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ በዘር ጭፍጨፋው የተሳተፉ እና ያልተሳተፉ ሁቱዎች በወቅቱ ዛየር ትባል ወደነበረችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሸሹ።

ሌሎች ደግሞ ወደ ታንዛኒያ እና ቡሩንዲ አቀኑ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአርፒኤፍ ኃይሎች ሥልጣን ላይ ሲወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሁቱዎችን ገድለዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።

የተባበሩት መንግሥታት፤ ዓለም አቀፍ የሩዋንዳ ወንጀለኞች ችሎት የሚል አቋቁሞ በዘር ማጥፋቱ ትልቅ ሚና ነበራቸው ያላቸው ሰዎች ላይ ክስ መሠረተ።

ሩዋንዳዊያን ለፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ያላቸውን ድጋፍ ሲገልጡ

ሩዋንዳ ውስጥ ደግሞ ጋቻቻ የተባሉ አገር በቀል ሸንጎዎች ተቋቁመው በዘር ጭፍጨፋው እጃቸው አለበት የተባሉ ሰዎች ፍርድ እንዲሰጣቸው ተደርጓል።

ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በዘር ጭፍጨፋ የላሸቀችውን ትንሿን አገር አሁን ወዳለችበት በማብቃታቸው ብዙ ውዳሴ ይቸራቸዋል። ሩዋንዳ በምጣኔ ሀብት እንድትዳብር፣ በጤና፣ በቴክኖሎጂ እና በቱሪዝም የላቀች እንድትሆን ጥረው እየተሳካላቸው ነው።

ነገር ግን ተቺዎቻቸው ደግሞ የተቃዋሚዎችን ድምፅ ያፍናሉ ሲሉ ይወቅሷቸዋል።

የዘር ጭፍጨፋው ሩዋንዳ ውስጥ በጣም በጥንቃቄ ከሚታዩ ጉዳዮች አንዱ ነው። በአገሪቱ ስለብሔር ማውራት በሕግ ሊያስቀጣ ይችላል።

መንግሥት ይህን ያደረግኩት የጥላቻ ንግግርን ለማራቅ እና ደም መፋሰስን ለማስወገድ ነው ይላል። ሌሎች ደግሞ ይህ እውነተኛ እርቅ እንዳይመጣ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

ዩኒሴፍ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በሩዋንዳ በዘር ጭፍጨፋው ምክንያት 95 ሺህ ሕፃናት ወላጅ አልባ ሆነዋል።

እነሆ የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ 30 ዓመታት ሞላው። ከአሰቃቂው ግድያ የተረፉ ሕፃናት ዕድሜያቸው ላይ 30 ዓመታት ጨመሩ ማለት ነው።

አንዳንዶች ወደ ኪጋሊ ጄኖሳይድ ሚሞሪያል መግባት ይፈራሉ። የሚገጥማቸው ምን እንደሆነ አያውቁምና።

የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ በቁጥሮች