
5 ሚያዚያ 2024, 19:02 EAT
ከመመረቂያ ጊዜ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ይዘው ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ የወጡ የመቀለ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፖሊስ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው እና እንደታሰሩ ተማሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
በትግራይ በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ከሁለት ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት ለማካካስ ተጨማሪ ሴሚስተር እንዲሰጣቸው የጠየቁ ተማሪዎች ናቸው ዛሬ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም. አደባባይ የወጡት።
በዚህም ፖሊስ የተማሪዎቹ ሰልፍ ያልተፈቀደ እና ሕገወጥ እንደሆነ በመግለጽ እንዲበተኑ በወሰደው አርምጃ ተማሪዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙን እና አስከ 20 የሚደርሱ ታስረው እንደነበር ቢቢሲ ያናገራቸው ተማሪዎች ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ በጦርነቱ ጊዜ የባከነባቸውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ በዚህ ዓመት የሦስት ሴሚስተር ትምህርት ተሰጥቷቸው እንደሚመረቁ ተነግሯቸው እንደነበር እና አሁን ይህ ቃል በመታጠፉ ቅሬታቸውን ለመግለጽ ሰልፍ መውጣታቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው ሁለት ተማሪዎች ገልጸዋል።
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞቹን ፎቶ በቅርንጫፎቹ በር ላይ ይፋ ማድረግ ጀመረ5 ሚያዚያ 2024
- “ከትግራይ በኩል በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” – መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት4 ሚያዚያ 2024
- የአማራ እና ትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡበት ራያ አላማጣ በተከሰተ ግጭት የሰዎች ሕይወት ጠፋ27 መጋቢት 2024
ተማሪዎቹ የባከናባቸው ጊዜ ከግምት ውስጥ ገብቶ ተጨማሪ ሴሚስተር በመማር ተፈትነው ትምህርታቸውን በዚህ ዓመት አጠናቀው ለመመረቅ እየተዘጋጁ የነበረ ቢሆንም፣ ትምህርታቸው የሚያበቃው እና የሚመረቁት በሚቀጥለው ዓመት እንደሚሆን ተነግሯቸዋል።
ስለጉዳዩ በቢቢሲ የተጠየቁት የዩኒቨርስቲው ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ትካቦ፣ በተማሪዎቹ ሰልፍ ላይ ስለተከሰተው ነገር መረጃ እንደሌላቸው ገልጸው፣ ተማሪዎች ከመመረቂያ ጊዜ ጋር በተያያዘ ጥያቄ እንዳላቸው እንደሚያውቁ እና ጥያቄው በዩኒቨርስቲው ሕግ መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ ለዩኒቨርስቲው አስተዳደር እና ፕሬዝዳንቷ ጉዳዩን በተደጋጋሚ ቢያነሱም ምላሽ እንዳላገኙ እና አቤቱታቸውን ለማሰማት ከዩኒቨርስቲው ውጪ ሰልፍ መውጣታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ እንደሚሉት ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ የሚጠይቁባቸውን ባነሮች ይዘው ሰልፍ እያደረጉ ሳለ የከተማዋ ፖሊስ አባላት እንዲበተኑ በማዘዝ፤ በድብደባ እንደበተኗቸው እና ወደ ሰማይም ጥይት መተኮሱን ተናግረዋል።
በድብደባ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች እንዳሉ እና 20 የሚሆኑ ተማሪዎች በፖሊስ ታስረው እንደነበረ እና አሁንም ሰባት ተማሪዎች በእስር ላይ መሆናቸውን በሰልፉ ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቢቢሲ ስለ ክስተቱ ከትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም ከመቀለ ከተማ ፖሊስ ምላሽ እና ማብራሪያ ለመግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።