
April 7, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የማኅበረሰብረ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከሰሞኑ ከአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ወዘተ እያለ ከሴቶች ተወካዮች ጋር አሥር ተከታታይ የውይይት መድረክ ቪዲዮዎችን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አከታትለው ሲያሠራጩ መመልከት ተችሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ደግሞ 11ኛው የውይይት መድረክ ሥርጭት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተላልፏል፡፡
ይህ መድረክ ደግሞ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የተካሄደ እንደመሆኑ መጠን፣ በመድረኩ ምን ሊነሳ ይችላል የሚለው ጉዳይ ብዙዎች በጉጉት የጠበቁት ነበር፡፡ ከተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ መንግሥትን አይዞህ በርታ ብለው የሚደግፉ፣ ስለሠራቸው የፓርክ፣ መናፈሻና ሪዞርት ፕሮጀክቶች ሙገሳ የሚያቀርቡ ብዙ እንደሚሆኑ የገመቱ ነበሩ፡፡ ይህን አንድ ሰዓት ከ44 ደቂቃ የረዘመ የስብሰባው ቪዲዮ በተደጋጋሚ መመልከት የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒው አገሪቱ የምትገኝበትን ቀውስና አደጋ እንዲሁም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸውን አሳሳቢ ችግሮች ያማከሉ ጥያቄዎችም መቅረባቸውን ከውይይቱ ሥርጭት መታዘብ ተችሏል፡፡
ያም ቢሆን ግን ወደ 19 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጥያቄ ያነሱበት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለግማሽ ቀን የተካሄደው ሰፊ ውይይት፣ በመንግሥት ሚዲያዎች ተመጥኖ ከተለቀቀው ምጥን ሥርጭት በላይ ድባብ ሊኖረው እንደሚችል ይገመታል፡፡ በዚህ የተነሳም በውውይቱ አዳራሽ በአካል ተገኝተው ውይይቱን ከተካፈሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ሪፖርተር በውይይቱ ድባብ ዙሪያ ምጥን ቆይታዎችን በማድረግ የነበረውን ሁኔታ ለማስቃኘት ይሞክራል፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)
በሰላማዊ ትግል ለረጅም ዓመታት ያሳለፉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አጋጣሚው ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለፓርቲዎቹ አገሪቱን በተመለከተ ያላቸውን አረዳድ በቀጥታ ለመነጋገር ዕድል የፈጠረ በጎ ጅምር ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የቀረቡት ጥያቄዎች እንደ ጠያቂ ፓርቲዎች ተወካዮች የግንዛቤ ደረጃ የሚወሰኑ ናቸው፡፡ በጣም የሰከኑና ለሁኔታዎች በቂ ግንዛቤ እንዳላቸው የሚያሳዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ አንዳንድ ከስሜታዊነት የመነጩ አንዳንዶችም ከአገር መሪ ጋር ውይይት ለማድረግ በማይመጥኑ ቃላት የቀረቡ ጥያቄዎች አሉ፤›› በማለት ስለተነሱ ጥያቄዎች ይገልጻሉ፡፡

(ፕሮፌሰር)
ለቀረቡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልሶች ተሰጥቶ እንደሆነ የተጠየቁት በየነ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ለቀረቡት ጥያቄዎች ሁሉ መልስ መጠበቁ የዋህነት ይመስለኛል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ እሳቸው ባሳለፉት ረጅም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ስለፖለቲካ ምኅዳር መጥበብ የተለያዩ መሪዎችን ሲጠይቁ እንደቆዩ በማንሳት፣ ዛሬም ድረስ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ምኅዳሩ ይስፋ ከሚል ጥያቄ አለመላቀቃቸውን እንዴት እንደሚታዘቡት ተጠይቀው ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩ ከዚህ ጎን እሳቸውና አጋሮቻቸው ብሔራዊ ምክክር ያስፈልጋል የሚል አጀንዳ አንግበው ለረጅም ዘመናት ሲጠይቁ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው አገዛዝ ግን ‹‹ማን ከማን ተጣላና ነው ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ የምትሉት›› በማለት ትኩረት ነፍጎት መቆየቱን አውስተዋል፡፡
አሁን ያለው መንግሥት ግን ይህን አጀንዳ በተለየ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ እንደደገፈው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ብሔራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ሲዋቀር እኔም አባል ነበርኩ፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ስላልሠራ ከሦስት ዓመት በኋላ መክኗል፡፡ አሁን ደግሞ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራ እየተሠራ ነው፤›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡
የአሁኑ መንግሥት ለብሔራዊ ምክክርና ለብሔራዊ መግባባት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ተቋም እንዲመሠረት ማድረጉ በራሱ አዎንታዊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ይህን ዕድልና አጋጣሚ ለመጠቀም የሚያስችል ከባቢ አየርና ዕድል የለም፤›› በማለት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙ ትዕግሥት ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰላማዊ ዘዴና ብልኃት ማፍለቅ የሚጠይቅ መሆኑን ከልምዳቸው በመነሳት ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡና ተጠናክረው እንዲቀርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበውን ምክር በተመለከተ፣ ‹‹ሐሳባዊ (Idealistic) ነው›› ይሉታል፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ተቃዋሚዎች ወደ ሦስት አራት ቡድን ሰብሰብ ብለው እንዲቀርቡ መፈለግ፣ ‹‹ከሩቅ ሲያዩት ውኃ ሲጠጉት ባዶ እንደሚሆን ሚራዥ ነው፤›› የሚመስለው በማለት በተጨባጭ እንደማይሳካ ነው ግምታቸውን ያስቀመጡት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኞቹ ‹‹ተበድሏል ለሚሉት ብሔር/ማኅበረሰብ ከመጮኸና ከአድቮኬሲ ሥራ ከመሥራት ይልቅ የርዕዮተ ዓለም መሠረት ኖሯቸው ተጠናክረው የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉ አይደሉም፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩልም ‹‹ሰጥቶ መቀበል በሚል መርህ ከሌሎች ጋር ተባብሮና ተሰባስቦ መሥራትን የሚያስቀድመውስ ማነው?›› ሲሉ የጠየቁት በየነ (ፕሮፌሰር)፣ እሳቸው በፖለቲካ ባሳለፉባቸው ጊዜያት የተለያዩ ኅብረቶችን ለመፍጠር ሲጥሩ መቆየታቸውን በማስታወስ ተሰባሰቡ የሚለው ሐሳብ ፈታኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በአጠቃላይ የውይይት መድረኩ እንደ ጅማሮ በመልካም ሁኔታ እንደታዘቡት ነው የጠቆሙት፡፡
የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የሥራ አስፈጻሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አዲስ መሐመድ
ከውይይቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የጉብኝት ፕሮግራም የፓርቲዎች ተወካዮች እንዳደረጉ የሚያስታውሱት ወ/ሮ አዲስ መሐመድ በዚህ ጊዜም፣ ‹‹ሙዚየምና ፓርኩን ሲጎበኝ ፓ ይህ ሰውዬማ ሺሕ ዓመት ይግዛ›› እያለ የሚመርቅ ሰው መታዘባቸውን በመጥቀስ ነው ውይይቱን የገመገሙበትን መንገድ የሚያብራሩት፡፡ በውይይቱም ከአንዳንድ ጠያቂዎች ከሙገሳና ከውዳሴ የዘለለ ሐሳብ አለመነሳቱን ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ዕድል አግኝተው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ‹‹አንዳንድ ፓርቲዎች እንደ ልጅ ሌሎች እንደ እንጀራ ልጅ ይታያሉ፤›› የሚል ሐሳብ ማንሳታቸው ከሌሎች ጋር ምልልስ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ማነው ልጅ፣ ማነው የእንጀራ ልጅ ብለው የፓርቲ ስም አስጠሩኝ፤›› የሚሉት ወ/ሮ አዲስ ቢሮ ስለሚሰጣቸው፣ ለጠቅላላ ጉባዔ አዳራሽ ስለሚመቻችላቸውና ብዙ ድጋፍ ስለሚያገኙ ፓርቲዎች በመጠየቃቸው በመድረኩ ምልልስ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ግንኙነት ኃላፊ ወ/ሮ አዲስ መሐመድ
‹‹የፓርቲዎች በመድረኩ የሚረባ ነገር አለማንሳት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ደስ የማይል አመለካከት የሚያሳድር ስሜት አለው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ አክለውም ካነሷቸው ሰባት ጥያቄዎች አራቱ ተቆርጠው ሦስቱ ብቻ መቅረባቸውን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ባሏ፣ ልጇ፣ ወንድሟ ስለተገደሉባት ሴት አንስቼ ‹ጌታዬ አንተ እኮ ዝምታህ መብዛቱ የሌለህ ያስመስልሃል› ብላ ፀሎት ማሰማቷን ጠቅሼ፣ መንግሥት ለምን ዝምታው እንደበዛ ጠይቄ ነበር፡፡ ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ የመንግሥት ግዴታ ሆኖ ሳለ ዝምታችሁ የሌላችሁ አስመስሏችኋል ብዬ አንስቻለሁ፡፡ የአገሪቱን ሰላም ማጣት መቆጣጠር አቅቷችሁ ወይስ ዝምታውን ፈልጋችሁት ነው የሚል ጠንካራ ጥያቄ አቅርበን ነበር፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በሁለተኝነት በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር ሕዝቡን ለሥቃይ እንደዳረገው አንስተናል፡፡ በመንግሥትና በታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ፍልሚያ የሰላማዊውን ሕዝብ ኑሮ እንዳመሳቀለው ጠቁመን ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በሦስተኝነት ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻከርም ቀርቧል፡፡ ከሶማሌላንድ ጋር የነበረውን ስምምነት ሒደት ግልጽ እንዲሆን ከመጠየቅ ባለፈ ያመጣውን ውጤት እንዲብራራ ጠይቀናል፡፡ በአራተኝነትም ለከተማ ማስዋብና ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት በሚል የሚፈናቀለውን ሕዝብ ጉዳይ ጠይቀናል፡፡ ስማርት ሲቲ በመገንባት ስም ሕዝቡን ማፈናቀልና ማሳደድ፣ ግንባታው ለማነው የሚካሄደው የሚል ጥያቄ ማስነሳቱን ጠይቀናል፤›› በማለት ፓርቲያቸው የጠየቃቸውና ተቆርጠው ያልተላለፉ ጥያቄዎችን ዘርዝረዋል፡፡
የሕግ ባለሙያዋ ወ/ሮ አዲስ በቅርበት በሕግ የበላይነት ላይ የሚታዘቡትን ዋቢ በማድረግ የፍትሕ ተቋማትን የተመለከቱ ጠንካራ ጥያቄዎችን በማስረጃ አስደግፈው ማቅረባቸውንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤቶች አንድ ጉዳይ ክርክር ተደርጎበት ዳኛ በደለኝ፣ ጠበቃ አበላሸብኝ ወይም ዓቃቤ ሕግ እንዲህ አደረገኝ የሚል ቅሬታ ነበር የሚሰማው፡፡ አሁን ግን ፋይል የሚከፍት እንኳ ጠፍቷል፡፡ ሬጅስትራር ገና ሲኬድ ከከተማ መልሶ ማልማት ፈረሳ ጋር በተያያዘ ፋይል አንከፍትም ትባላለህ፡፡ ካርታ ይዣለሁ እያልክ ካርታውን ያዘው መሬቱ ግን የእኛ ነው እስከ ማለት ተደርሷል፡፡ ግሎባል ኮሊዥን ፎር ጀስቲስ ከሚባል ተቋም ጋር የተወሰኑ ሰዎችን ጉዳይ ይዘን አቅርበን ነበር፡፡ ካርታ የያዙ ሰዎችን እንኳን ፋይል የሚከፍት የለም፡፡ በተለይ በሸገር ከተማ ፈረሳ ጉዳይ የማነው ደፋር ፍትሕ ፍለጋ የመጣው ተብሎ ይሳለቁብሃል፤›› በማለት ኅብረተሰቡ በፍትሕ ሥርዓቱ እየገጠመው ያለውን ፈተናና ምሬት ገልጸው ምላሽ እንዲሰጥበት መጠየቃቸውን አስረድተዋል፡፡
እነዚህን ዓይነት ጥያቄዎቻቸው መቆረጣቸውንና መልስ አለማግኘታቸውን የገለጹት ፖለቲከኛዋ፣ ‹‹ኢትዮጵያ በልጆቿ ትታረቅ›› በሚል ርዕስ ፓርቲያቸው የጀመረውን የሰላም ተነሳሽነት የተመለከተ ጥሪ ለመንግሥትና ለሌሎች ፓርቲዎች ማቅረባቸውንም አመልክተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ
ውይይቱን በሚመለከት ግምገማቸውን ያጋሩት ሌላኛው ፖለቲከኛ አቶ ደስታ ዲንቃ በበኩላቸው፣ አጥጋቢ መልሶች ያልተሰጠበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይህችን አገር የሚያበጣብጣት እኮ የፖለቲካ ምኅዳር ጥበት ነው እንጂ ሌላ ምንም ነገር የለም፤›› ሲሉ የሚያነሱት አቶ ደስታ፣ ለዚህና ለሌሎችም ለተነሱ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ ለመስጠት በሕግ የተቀመጡ የዜጎችን መብቶች ማክበር በመሠረታዊነት እንደሚጠይቅ አውስተዋል፡፡ በተጨባጭ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ ያለው፣ ‹‹የዜጎች መብት በሕግ ሳይሆን በመንግሥት ስለሚገደብ ነው›› በማለት የሚናገሩት አቶ ደስታ፣ መንግሥት የሚያዛቸው የፀጥታ ኃይሎች ጫናና ወከባ እስካልተቀረፈ ድረስ የፖለቲካ ምኅዳር መስፋት ጥያቄ ሁሌም ችግር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የውይይት መድረኩ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተነሳሽነትና ጥያቄ መካሄዱን የተናገሩት አቶ ደስታ፣ በዚህ ላይ ያለው አመለካከት መታረም እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ‹‹ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየታቸውን ተከትሎ የመጣ ሳይሆን፣ በራሳችን ጥያቄ ስለአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ለመንግሥት ለማስረዳትና ለማሳሰብ በሚል በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል በቀረበ ጥያቄ የተካሄደ መድረክ ነው፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡ ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል አብዛኞቹን እንደረኩባቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹የአገሪቱ አንገብጋቢ ያልሆኑ ጉዳዮች ተነስተዋል፣ አንዳንድ አላስፈላጊ የቃላት ልውውጦችም ነበሩ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ያለን ፓርቲ የመተቸትና የማረም ሚና አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ በውይይቱ ላይ በሙስና፣ በመልካም አስተዳደር፣ በፖለቲካ ምኅዳር፣ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ባለው አሠራርና በሌሎችም ጉዳዮች ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ከመድረኩ የተገኙ የተስፋ ቃሎች ባይኖሩምና የተሰጡ አጥጋቢ ምላሾች ባይኖሩም፣ ነገር ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለገዥው ፓርቲ ትልቅ የቤት ሥራ ሰጥተውታል፡፡ ገዥው ፓርቲ (መንግሥት) ትኩረት ሰጥቶ የሚታረመውን እያረመ እንደሚሄድ ተስፋ እናደርጋለን፤›› በማለት አጋጣሚው ምንም ቢሆን ተቃዋሚዎች ግን በተቻለ አቅም ዕድሉን ለመጠቀም ጥረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚያሰባስበው የአመለካከት፣ የትግል መስመርና የሕዝብ ቅቡልነት መመሳሰል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ደስታ፣ ሰብሰብ ብለው ከቀረቡ ለፖለቲካ ምኅዳሩ መስተካከልና ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ይበጃል በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ የሚነሳው ሐሳብ ብዙም እንደማያሳምናቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሌላውን ለእኛ ትተው መጀመሪያ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያስፉት፡፡ ወደ 69 የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኛ ሥር አሉ፡፡ ከእነዚህ 45 ክልላዊ 24 ደግሞ አገራዊ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ስንቶቹ ተሰሚነት ያላቸውና ጠንካራ ናቸው የሚለውን ሕዝቡ የሚያውቀው ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ሁሉም ከእኩል ቦታ ተነስቶ እንዲሮጥ ቢደረግ እያንዳንዱ ለራሱ የሚያዋጣውን አካሄድ በደንብ ያውቃል፡፡ 69 የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ቀን ጠቅላላ ጉባዔ አይጠሩም፡፡ መንግሥት የስብሰባ አዳራሾችን ለመፍቀድ ፈቃደኛ ከሆነ ፓርቲዎቹ የግድ እንዲሰባሰቡ አይገደዱም፤›› በማለት የፖለቲካ ሜዳው መስፋት ጉዳይ አሳሳቢ አጀንዳ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የኢሕአፓ ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረውን መድረክ ፓርቲያቸው እንደገመገመው የሚናገሩት መጋቢ ብሉይ አብረሃም፣ ‹‹የተጠበቀውን ያህል ያልተገኘበትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲያችንን ለመርገም ተገቢ ያልሆነ ርቀት የሄዱበት መድረክ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ኢሕአፓ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ማንሳቱን የተናገሩት ፖለቲከኛው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች በንዴት የተሞላ መልስ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢሕአፓ ያረጀና የሻገተ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡ እኛ እንደ ድርጅት ወደ ውይይቱ ለመግባት ተወያይተን ነው የወሰንነው፡፡ ከመድረኩ የሚገኝ ነገር ባይኖርም ለታሪክ እንዲቀመጥ ገብተን መጠየቁ ይሻላል ብለን ነው የተገኘነው፡፡ እኔ አዋሽ አርባ እስር ቤት ለሦስት ወራት ከ15 ቀን ታስሬ ነው የወጣሁት፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ አስተባበራችሁ በሚል ብዙዎች ያለ ምንም ጥፋት ታስረናል፡፡ አሁን ደግሞ የፓርቲያችን ሊቀመንበር ዝናቡ አበራ (ፕሮፌሰር) ታስረዋል፡፡ እነ ዮሴፍ ተሻገር፣ እዮብ ገብረ ሥላሴና ጠበቃ አበራ ንጉሤ በተመሳሳይ ታስረው ይገኛሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ሰላማዊ ትግልን እያጨነገፈ ካለ መንግሥት ጋር ተቀምጦ መወያየቱ ትርጉም የለውም ብለን ገምግመናል፡፡ ሆኖም ድምፅ ማሰማት አለብን ብለን ጥያቄያችንን በንባብ አቀረብን፡፡ ጥያቄዎቻችንን በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ፣ ፓርቲያችንን መስደብና መርገም ነው እሳቸው የመረጡት፤›› በማለት ከስብሰባው ያገኙት የሚረባ ነገር አለመኖሩን አመልክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሦስት ወራት በኋላ በሌላ ዙር ውይይት እንገናኛለን ማለታቸውን እንደ አንድ ተስፋ ከመውሰድ በዘለለ፣ ከውይይቱ የተገኘ አጥጋቢ ነገር አለመኖሩን መጋቢ ብሉይ አክለዋል፡፡ ‹‹በአጠቃላይ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ ከባድ አደጋ የተደቀነ መሆኑን ተረድተናል፡፡ ሥርዓቱ ጥፋቶቹን ለማረም ዝግጁ እንዳልሆነ ተረድተናል፡፡ ፖለቲከኞች ስንታሰር የሚጮኸልን ብዙ ነው፡፡ በታሰርኩበት ወቅት ግን እንደታዘብኩት ከሆነ ምንም ሳያጠፋ የሚታሰረውና የሚጮህለት ወገን የሌለው ሰላማዊ ሕዝብ ብዙ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ካልቆመ በኢትዮጵያ መቼም ሰላም የሚኖር አይመስለኝም፤›› በማለት የገለጹት ፖለቲካኛው፣ መጪው ጊዜ የበለጠ እንደሚያሠጋ አስረድተዋል፡፡
ባለፈው ምርጫ በአገር አቀፍ ደረጃ የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች 12 መሆናቸውን፣ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ የሚያቀነቅኑት በጣት የሚቆጠሩ እንደሆኑ የሚናገሩት መጋቢ ብሉይ፣ ‹‹ዕውን በኢትዮጵያ ፓርቲ በዝቶ ነው ወይ የብልፅግና መንግሥት ከተፎካካሪዎች ጋር የሚሠራበት ሁኔታ እንደቸገረው ተደርጎ የሚቀርበውና ተሰባሰቡ እየተባለ የሚመከረው?›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሰጡትን ምክር ተችተዋል፡፡ በዓላማ የሚታገሉ ጠንካራ ፓርቲዎችን እያሳደዱ ለእነሱ የተመቹ 200 ፓርቲዎችን ፈልፍለው ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ መምከራቸው አግባብነት እንደሌለው ወቅሰዋል፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ስለሆነ እንጂ 50 ዓመታት የዘለቀ ፓርቲ ትልቅ ከበሬታን በሌላ ቦታ ያገኛል፡፡ የኢሕአፓ 50 ዓመታት መኖር እሳቸውን ለምን ያማቸዋል? ኢሕአፓ 50 ዓመታት በፅናት በመዝለቁ ያረጀና የሻገተ ተብሎ መሰደቡ ፍጹም ተገቢነት የሌለው ነው፤›› በማለት ነበር መጋቢ ብሉይ ሐሳባቸውን የቋጩት፡፡
ከእናት ፓርቲ አቶ ጌትነት ወርቁ
በውይይቱ የፓርቲያቸው አመራሮች የተሳተፉት አንድ ነገር ይገኝበታል በሚል ተስፋ አለመሆኑን የጠቀሱት አቶ ጌትነት፣ ‹‹እስከ ዛሬ በመግለጫዎች የምንጮህባቸው ጉዳዮችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ማቅረብ ከተቻለ›› በሚል ጭላንጭል ተስፋ እንደተሳተፉ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄ ለማቅረብም ሆነ ሐሳብ ለመስጠት የፓርቲያቸው አባላት ዕድል አለማግኘታቸውን አመልክተዋል፡፡ ከፓርቲዎች መካከል ብዙዎቹ፣ ‹‹እንኳን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቶ ለወረዳ አስተዳዳሪም ለመቅረብ የማይመጥኑ ጥያቄዎች ነው ያነሱት፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ ከሦስት ሰዎች በላይ ቤቱ ተንጫጭቶ ጥያቄያቸውን ያቋረጣቸው መኖራቸውን አመልክተው፣ የአንዳንድ ፓርቲዎችን ሁኔታ ማየት መጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካን በሥጋት ለመመልከት የሚጋብዝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተነሱ ጥያቄዎችም ቢሆን አጥጋቢ መልስ አለመስጠታቸውን አቶ ጌትነት ተናግረዋል፡፡ በእሳቸው እምነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት አንደኛ የፀጥታ ጉዳይን በጉልህ የሚያነሳ ቢሆን የተሻለ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
‹‹ልክ እንደ ታይታኒክ መርከብ ኢትዮጵያም እየሰመጠች በተመስጦ ቫዮሊን መጫወትን ለመቀጠል የቆረጡ ሰዎች ያሉባት ትመስላለች፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጌትነት፣ የሰዎች ወጥቶ የመግባት ዋስትና አደጋ ላይ ወድቆና አገር በከባድ ቀውስና የመፍረስ አደጋ ላይ ሆኖ ስለሌላ ነገር መናገሩ እየሰመጡ ቫዮሊን መጫመት እንደሚሆንባቸው አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል ተቋማትን የማጠናከር ጉዳይ በውይይቱ በቂ ትኩረት እንዳላገኘ አክለዋል፡፡ የትግራይና የአማራ ክልሎች በጦርነት አፋፍ ላይ መውደቃቸውም አልተተኮረበትም ይላሉ፡፡ በእምነት ተቋማት ላይ የሚደርሰው ጫናም በትኩረት አለመጠየቁን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች በተጨማሪም፣ ‹‹የኑሮ ውድነት፣ የዶላር እጥረትና የዋጋ ንረትን ጨምሮ አጠቃላይ የአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች በውይይት መድረኩ ተገቢውን ቦታ አላገኙም፡፡ ከተማነት ወይም የከተማ ልማት ምንድነው የሚለው የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳም ተዘሏል፤›› ሲሉ አቶ ጌትነት አብራርተዋል፡፡
የኢዜማ ምክትል መሪ አቶ ዮሐንስ መኮንን
በውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት አቶ ዮሐንስ ፓርቲያቸው ኢዜማ በንባብ ጥያቄውን ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላ በነበሩ ቀናት በውይይቱ መሀል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የኢዜማው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ጠንካራ ቃላት ስለመወራወራቸውና ስለመጋጨታቸው ሲወራ የሰነበተውን መረጃ፣ ‹‹የበሬ ወለደና ጭር ሲል አልወድም ወሬ›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ በውይይቱ ወቅት የኢዜማ መሪ በካቢኔ አባልነታቸው ያስመዘገቡት ስኬት በተነሳበት ወቅት ከተነሳ የቀልድ ሐሳብ ውጪ፣ የተፈጠረ የቃላት መወራወርም ሆነ ግጭት አለመኖሩን አመልክተዋል፡፡

‹‹ውይይቱ በተቃዋሚዎች አነሳሽነትና ጥያቄ የተካሄደ ነው፡፡ ውይይቱ መንግሥትና ተቃዋሚዎች እኩል የአገር ባለድርሻ ሆነው የቀረቡበት እንጂ አዛዥና ታዛዥ ሆነው የቀረቡበት አይደለም፡፡ የሰዓትም ሆነ የአጀንዳ ገደብ ሳይደረግ ዕድል ያገኘ ሁሉ ጥያቄውን ያቀረበበት ነው፡፡ ወደ 19 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም መልስ ያሉትን ተናግረዋል፡፡ መስማማት ሁላችንም አይጠበቅብንም፡፡ ይህን እንደ መነሻ በማድረግ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ አጋጣሚው ይጠቅማል፤›› በማለት ስለውይይቱ ያላቸውን ግምገማ ተናግረዋል፡፡
ኢዜማ ካነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ የአገራዊ ምክክር ስብሰባዎች በተለያዩ አደረጃጀቶች ተሳትፎ ስም በብልፅግና ካድሬዎች እየተሞሉ ነው ለሚለው አሳሳቢ ጉዳይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥጋቢ መልስ እንዳልሰጡ አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወይ አልተረዱትም፣ ወይ መረጃ የላቸውም፡፡ በእኛ በኩሉ ግን በዚህ ጥያቄ ሥጋታችንን አንስተናል፤›› በማለት አክለዋል፡፡ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ራሱ እኛ ያቀረብነውን ሥጋት መሠረት በማድረግ በአዲስ አበባ የጀመራቸውን መድረኮች ማቋረጡን መንግሥት፣ ‹‹እንዴት አልሰማም የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል›› ብለዋል፡፡
‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው አገራዊ ምክክር መድረክ የሚሳተፉት አገራዊ ፓርቲዎች ናቸው ተብሏል፡፡ አገራዊ የሚባሉ ፓርቲዎች ደግሞ ከ20 አይበልጡም፡፡ ብልፅግና በዚህ መድረክ ራሱን ወክሎ ቢቀርብ ደግ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ ወዘተ አደረጃጀት እየተባለ መድረኩን ልሙላው ካለ ችግር ነው የሚሆነው፤›› በማለት የኢዜማን ሥጋት አስረድተዋል፡፡