
ዜና በመተከል ዞን በተፈጸመ ጥቃት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
ቀን: April 7, 2024
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጉሙዝና የሸኔ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የንፁኃን ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
የቦሮ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበርና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የገጠር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ሊያካሂድ ያሰበውን ምርጫ ተገን በማድረግ የክልሉን ሰላም የሚያደፈርሱ ታጣቂዎች መብዛታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለይ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) የሚባል ታጣቂ ቡድን በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ውስጥ ግጭት በመፍጠርና ጥቃት በመፈጸም ንፁኃን ዜጎችን እየገደለ መሆኑን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ታጣቂዎቹ ከመንግሥት ድጋፍ እያገኙ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከመንግሥት ለታጣቂዎቹ ስለተደረገው ድጋፍ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ግን በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
በመከተል ዞን የተፈጸመው ጥቃት ሳምንት ቢሞላውም፣ የተባባሰው ግን ከሐሙስ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ገልጸው፣ ፓርቲው ግን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ታጣቂዎቹን መንግሥት አደብ ማስገዛት አለበት የሚል አቋም በመያዝ መግለጫ ማውጣቱን ገልጸዋል፡፡
መከላከያና ፌዴራል ታጣቂዎችን ማስቆም እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ለክልሉ መንግሥት ማሳሰባቸውን ያስታወሱት አቶ አመንቴ፣ ችግሩን ለመፍታት ከመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ዕርምጃ አለመወሰዱን ጠቁመዋል፡፡
በመተከል ዞን በሁሉም ወረዳዎች ምርጫ ይካሄዳል? አይካሄድም? የሚለውን ለማጤን ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎችና ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን የክልሉን የሰላም ሁኔታ እያጣራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፓርቲዎችም ሆኑ የክልሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማንዱራ ወረዳ ያለው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ መሆኑ እንዳሳሰባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በጉለንና በድባጤ ወረዳዎች የምርጫ ማዕከላት በሰባት ወይም በስምንት ቀበሌዎች ውስጥ የሸኔ ታጣቂዎች በመኖራቸው፣ ምርጫ ለማካሄድ ሥጋት አለ ብለዋል፡፡
ታጣቂዎቹ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አምስት ሰዎችን ሲገድሉ፣ ከ53 በላይ ከብቶችን ከአርሶ አደሩ መንጠቃቸውን አቶ አመንቴ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ምንም ዓይነት ምርጫ አለመካሄዱን የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ እስካሁን በ2007 ዓ.ም. የተመረጠው ምክር ቤት ለዘጠኝ ዓመታት ያህል እየመራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ምርጫ መደረግ አለበት የሚሉት አቶ አመንቴ፣ በአጠቃላይ በክልሉ ሰላም የሚያደፈርሱ ታጣቂ ኃይሎችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ መንግሥት የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በተለይ መተከልን አስመልሳለሁ በሚል በአማራ በኩል የሚንቀሳቀስ ኃይል እንዳለ ገልጸው፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዥው ፓርቲ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚካሄደውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ በየሁለት ቀናት ውይይት ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሱን አብራርተዋል፡፡
ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከአራት ቀናት በፊት ከምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን በክልሉ ምርጫ ለማድረግ ያስችላል ወይ የሚለውን በመገምገም፣ የፀጥታ ችግሩን አሳሳቢ ሊያደርገው እንደሚችል መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በክልሉ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ የጊዜ ሰሌዳ ካወጣ በኋላ፣ በመተከል ዞን እንደ አዲስ የፀጥታ ችግሩ ማገርሸቱን፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ዘርፍ ኃላፊና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አባል መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከመንግሥት ወገን ምርጫ እንዲደረግ የማይፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦች ማኅበራዊ የትስስር ገጾች በመጠቀም ግጭት እየፈጠሩ እንደሆነ፣ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በግልገል በለስ ከተማ አራት ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
ሐሙስ መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በዳንጉር ወረዳ በጉሙዝ ታጣቂዎች አንድ አርሶ አደር መገደሉን መስማታቸውን ገልጸው፣ ችግሩም በጣም አሳሳቢ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ተቸግረዋል ብለዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ሰላም ማምጣት ካልተቻለ ምርጫው ሊራዘም እንደሚችል ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት ያለውን ችግር ለመፍታት በፓርቲ ደረጃ መግለጫ በማውጣትና ለመንግሥት ደብዳቤ በመጻፍ ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በመተከል ዞን ውስጥ ሰላም እያደፈረሱ ያሉት ታጣቂዎች መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ በተለይ ደግሞ የማንዱራ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ የጉሙዝ ተወላጆች ድርጊቱን እየፈጸሙ መሆናቸው አብራርተዋል፡፡
በቅርቡ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ከአቶ አሻድሊ ሐሰን ጋር ክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና ሌሎች ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ በወቅቱም ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ ምክር ቤቶች በዞንና በወረዳ የሚጠናከሩበትን ሁኔታ ለመደገፍ መስማማት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌና በትግራይ ክልሎች ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንና በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ቡድኖችን በመላክ ዳሰሳ እያደረገ መሆኑን፣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የምርጫ ቦርድ ባልደረባ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በክልሉም እስካሁን ባለው የዳሰሳ ጥናት ምርጫ ለማድረግ ምንም ዓይነት አስፈሪ ነገር እንደሌለ የዳሰሳ ጥናት ለማድረግ ወደ ክልል ከሄዱ ቡድኖች ሪፖርት እንዳልቀረበ አክለዋል፡፡
በክልሉ የፀጥታ ችግር እንዳለ አለመስማታቸውን ገልጸው፣ የፀጥታ ችግር ካለ ምርጫው ሊራዘም እንደሚችልና ቦርዱ ሙሉ ለሙሉ ለመተው እንደሚገደድ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ የመከተል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋወያን በስልክ ለማነጋገር ጥረት ቢደረግም፣ ስለጉዳዩ መናገር እንደማይፈልጉ በመግለጽ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡