
ተሟገት የአዲስ አበባ ነፍስና ‹‹የመንገድ ኮሪዶር ልማት››
ቀን: April 7, 2024
በአዲስ አበቤው
በዚህ ርዕስ ላይ ትንሽ ነገር እንድል ያነሳሳኝ በሰሞኑ በአዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደ ያለው “አዲስ አበባን የማዘመን” ዘመቻ ነው። አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም ከተሞቻችን መዘመን እንዳለባቸው ማንም ቢሆን የሚስማማበት ይመስለኛል። ዝመና ግን እንዴት ነው መካሄድ ያለበት? “ዝመና” ማለት ራሱ ምንድነው? ዝመና እስከ ምን ድረስ ነው? የአንድ ከተማ ነዋሪዎች በከተማቸው ለውጥ ውስጥ ያላቸው ይሁንታ እስከምን ድረስ ነው? ዝመናና የሰዎች መብትስ እንዴት ይያያዛል? ዝመናና አካባቢ (Environmentent) እንዴት ይታያል? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች በጭንቅላቴ ተመላለሱብኝ። ቢያንስ የተሰማኝን ማሥፈር እንዳለብኝ በማመኔ ይህችን አጭር መጣጥፍ ለማሥፈር ተነሳሁ። ከላይ ያነሳኋቸውና ተያያዥ ጥያቄዎች ጠብሰቅ ያለ መጽሐፍ ሊወጣቸው ስለሚችል ወደ ዝርዝር አልገባም። ሆኖም ዋና ዋና ያልኳቸውን ጉዳዮች አነሳለሁ።
በመጀመሪያ የመጣጥፉን ርዕስ በተመለከተ አንድ ከተማ ነፍስ አለው ወይ? የሚለውን በመጠኑ መነካካት ያለብኝ ይመስለኛል። ብዙ ከተሞች የከተማ እምብርት ወይም ‹‹ሴንተር›› የሚሏቸው ቦታዎች አሏቸው። እነዚያ ቦታዎች ከተማው ሲቆረቆር መጀመሪያ ሰዎች የሰፈሩበት፣ ወይም በተቆረቆረው ከተማ እንደ ዋና መሠረት የሚታየው ቦታ ወይም ከጊዜ በኋላም ቢሆን ትኩረት እየሳበ የመጣ አካባቢ ሊሆን ይችላል። እነዚያ ቦታዎች ከጊዜ በኋላ የከተማው ነፍስ ወይም ዋና የትኩረት ማዕከል እየሆኑ ይሄዳሉ። በአገራችንም ሆነ በውጭ አገሮች የከተሞቻቸው ዋና የትኩረት ማዕከል ወይም ነፍስ የሆኑ ቦታዎች አሏቸው። በውጭም አገሮች እነ ለንደን፣ ፓሪስ፣ ኒውዮርክ፣ ሎስአንጀለስ፣ ቺካጎ፣ ሮማ፣ በርሊን፣ ቪየና፣ ዴሊሂ፣ ቶኪዮ፣ ቤጂንግ፣ ወዘተ የየራሳቸው ነፍሶች አሏቸው። እነዚህን ከተሞችም ሆነ ሌሎች ስሞቻቸውን ያልጠቀስኳቸው ከተሞች የሚጎበኝ ሰው የከተሞቹን ዋና ነፍስ የሆኑ ቦታዎች ሳይመለከት ከተሞቹን አየሁ ብሎ መናገር አይችልም።
አዲስ አበባም የመጣ ጎብኚ ፒያሳንና መርካቶን ካልጎበኘ አዲስ አበባን አይቼ መጣሁ ማለት አይችልም፣ ሌላው ቢቀር ይቸገራል። ፒያሳ የአዲስ አበባ ነፍስ ነበረች። አራዳ፣ ፒያሳ፣ መርካቶ የአዲስ አበባ መሠረታዊ ነፍሶች ናቸው። ነፍሳቸውን ይማረውና አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ የአዲስ አበባ ስታዲዮም በተሠራ ጊዜ ከከተማው ውጪ አደረጋችሁት ተብለው የተወቀሱትን በአንድ ቃለ ምልልስ ሲናገሩ ሰምቻለሁኝ። ፒያሳ/አራዳ ብዙ ተጽፎላታል፣ ተዘፍኖላታል፣ አዲስ አበባን በሚያውቁ፣ በተወለዱባትም፣ ባደጉባትም፣ በኖሩባትም የአዲስ አበባ ነፍስ እንደሆነች ማንም አይጠራጠርም። የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩ ጊዜ ሲደክመን ወይም ጥናት ሲሰለቸን፣ ከጓደኞቼ ጋር ሆነን በናዝሬት ትምህርት ቤት በሰባ ደረጃ ወርደን ወይ በአራት ኪሎ አድርገን፣ በጆሊ ባር፣ በራስ መኮንን ድልድይ አድርገን ፒያሳን መሀል ለመሀል አቋርጠን ደጎል አደባባይ ድረስ እያወራንና እየተሳሳቅን፣ ሲያሻንም መኮንን ባር፣ ገብረ ትንሳዔ፣ ክርያዚዝ፣ አፋር፣ ቲ ሩም ገብተን ሻይ ጠጥተን፣ ኬክ ወይ ባቅላባ በልተን ራሳችንን አነቃቅተን እንመለስና ጥናታችንን እንደ ገና እንቀጥላለን።
አንዳንዴ ደግሞ ረዘም ያለ ዕረፍት ሲኖረን ወይ ፈተና የጨረስን እንደሆነ ፋሲካ ሆቴል፣ አንድነት፣ ጥቁር አባይ፣ ኃይሉ ማሩ፣ ኮረብታ፣ ሻላ (አፍሪካ መጻሕፍት ቤት ፎቅ ላይ) ጎራ ብለን አንድ ሁለት ቢራ ወይም ድራፍት ብለን ወደ ካምፓስ እንመለሳለን። ምን ያህል ገንዘብ ቢኖረን፣ ጊዜ ቢተርፈን ግፋ ቢል ከደጃች ውቤ ሠፈር፣ ከፍሎሪዳ፣ ወዘተ አናልፍም። ዞረን ዞረን ወይ ፒያሳ ወይ አራት ኪሎ ነን። ከዚያም በኋላ ለረጅም ጊዜ ፒያሳ ትናፍቀኛለች፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጣሁ በኋላ እነኳን ለረጅም ዓመታት ቢያንስ በሳምንት ቢያንስ አንዴ ወይም ሁለቴ ፒያሳን ሳልጎበኛት አልሰነብትም። ከዚያም ወዲህ ሁልጊዜ ለፒያሳ የተለየ ፍቅርና ስሜት አለኝ። ምክንያቱም የዛሬን አያድርገውና የአዲስ አበባ ነፍስ ፒያሳ ነቻ። ይህን ትዝታዬንና ፍቅሬን እንዴት ልረሳው እችላለሁ? እቴጌ ጣይቱ በቤተ መንግሥቱ መኳንንት ከሥልጣን ተገልለው እንጦጦ እንደወጡ፣ ‹‹ለካ ነበርም እንዲህ ቅርብ ነበር›› አሉ ይባላል። ፒያሳን ለሚያውቁና ለሚረዱ ሰዎች ይህ ምን ማለት እንደሆነ ይገባቸዋል። ዛሬ ፒያሳ ነበር ተብላለች።
እርግጥ ነው፣ ‹‹ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም›› የሚባለው ከተሞች ሲገነቡ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ፣ ከተሞች ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የቀስ በቀስ ዕድገትና ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ ነው። ሮም የተቆረቆረችው ከክርስቶስ ልደት ሰባት መቶ ዓመት በፊት እንደሆነ ታሪኳ ያትታል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ብዙ ለውጦች ተደርገውባታል። እንዲያውም እ.ኤ.አ. በስልሳ አራት ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባት ነበር። በዚያን ጊዜ የከተማዋ ሦስት-አራተኛ ያህል በቃጠሎው ወደመ። በዘመኑ የነበረው ቄሳር ኔሮ ሮም እየተቃጠለች ይዘፍን ነበር ይባላል። የሮም ነዋሪዎችም ቃጠሎውን ራሱ ኔሮ ነው ያዘዘውና ያስፈጸመውም ብለው በሰፊው አምተውታል። ያም ሆኖ ሮም እዚህ የደረሰችው በረጅም ዘመን የግንባታ ሒደት ነው። እንደዚያም ሆኖ በሮም ግንባታ ዘመን የነበረው ውበት፣ ልማት፣ የሰው መብት፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ ጥያቄዎች የተለያየ ትርጉምና ዋጋ የሚሰጣቸው በመሆኑ የአዲስ አበባን ግንባታና መዘመን መመርመር ያለብን አሁን ባለው መሥፈርት እንጂ በሮማውያን ዘመን ሊሆን አይችልም።
ታዲያ አንድ የከተማው ባለሥልጣን በፒያሳ አካባቢ ከተመዘገቡ 42 ታሪካዊ ቤቶች 36 መሥፈርቱን አያሟሉም ሲል የሰማሁት መሰለኝ። ለእኔ ግን ፒያሳ ራሷ ታሪክ ነበረች። ታሪክ እንዴት ይታያል ለሚለው መልሱ ንጉሦች የኖሩበት፣ የሰፈሩበት፣ ፍርድ የሰጡበት፣ ወዘተ. ከሆነ ብዙዎቹ ቤቶች ያንን መሥፈርት ላያሟሉ ይችሉ ይሆናል። ብዙ ጊዜ የሚያነታርከው ታሪክ የማነው? የንጉሦችና የባላባት ወይም የመሪዎች? የኃይለኞች፣ የጦረኞች ወዘተ ብቻ ነው ወይ? ሕዝብስ የታሪክ አካል አይደለም ወይ? ከተባለ ፒያሳ የሕዝብ ታሪክ የሰፈረባት የአዲስ አበባ ነፍስ ነበረች። ፒያሳ መፅዳት፣ በአግባቡ ታሪካዊነቷን ጠብቃ መዘመን አልነበረባትም ወይ? እንዴታ በደንብ። መንገዶቿ ብዙ ሳይነካኩ፣ ወርቅ ቤቶቿ፣ ሱቆቿ፣ ታሪካዊ አርክቴክቸሮቿ፣ ሻይ ቤቶቿ፣ ምግብ ቤቶቿ ታሪካዊነታቸውን እንደ ጠበቁ ሊዘምኑ አይችሉም ነበር ወይ? በሚገባ እንዴት አይቻልም? ለዘመናዊ አርክቴክቸርና ምህንድስና ምሥጋና ይግባውና የማይቻልበት ምክንያት ያለ አይመስለኝም። ትክክለኛውም አማራጭ ይኸው ነበረ። ብዙዎች ትልልቅ ከተሞችም ይኸንኑ ነው የሚያደርጉት። ልማት በሚል ሰበብ የከተሞቻቸውን ነፍስ አያጠፉም፣ አያፈርሱም። በየአገሩ ታላላቅ ከተሞች፣ የታወቁ ሰዎች ሻይ ይጠጡባቸው የነበሩ፣ ከጓደኞቻቸው ጋር ተገናኝተው ይወያዩባቸው የነበሩ ቦታዎች ሳይቀሩ የታሪክ ዋጋ ተሰጥቷቸው ይጠበቃሉ። ከላይ የጠቀስኩት ባለሥልጣን ሐኪም ወርቅነህ የኖሩበትን ቤት መኖሪያ መሆኑን እንኳን ማረጋገጥ አልተቻለም ሲል የሰማሁትም መሰለኝ።
የታሪካዊነት መሥፈርት እንደ ሰዎች ሊለያይ ይችላል። ዋና ዓላማው ማፍረስ የሆነ ማፍረስ የሚያስችለውን መሥፈርት ሊያወጣ ይችላል። የአንድ ከተማ ባለቤት ነኝ ብሎ የሚያስብ፣ ወይም ለከተማዋ ፍቅር ያለው፣ ወይም ለታሪክና ለቅርስ በተወሰነ ደረጃ ሐሳብ ያለው ሲሆን ደግሞ የሚያወጣውን መሥፈርት ተጠንቅቆ ያዘጋጃል። የዛሬ ዘመን መንግሥት በተለይም ደግሞ በምርጫ ሥልጣን ያዝኩኝ ብሎ የሚያስብ ሲሆን፣ በሚሠራው ማናቸውም ሥራው የመራጩን ሕዝብ ስሜትና ፍላጎት ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። በተለይ በመንግሥት የሚከናወን ሥራ በሕዝብ ገንዘብ የሚሠራ መሆኑን መዘንጋት አይቻልም። ስለዚህ መንግሥት የሚሠራው ማንኛውም የልማት ሥራ የሚከናወነው በሕዝብ ገንዘብ እንደ መሆኑ መጠን በዋናነት የሚሠራው ለሕዝቡ ነው። ሕዝብ እንዲጠቀምበት፣ ኑሮው እንዲሻሻልበት፣ ቁሳዊና ህሊናዊ እሴቶቹን ከግምት ያስገባ፣ መብትና ጥቅሙን ያከበረና ለሰው ዋጋ የሚሰጥ መሆን አለበት።
እነዚህን መሥፈርቶች ማሟላት የግድ የሚለው ሥራው የሚከናወነው በሕዝብ ገንዘብ በመሆኑ፣ የሚሠራውም ለሕዝብ ጥቅም በመሆኑ፣ ሕዝብ ተኮርና ሕዝብን ማዕከል ያደረገ መሆን ስላለበት ነው። አሁን ያለውን ሕዝብ አክብረን መብቱን ጠብቀን፣ የሥራችን ማዕከልና ዋና ትኩረት አድርገን፣ ልማትን ወይም ዝመናን ስንሠራ ነው ለወደፊቱ ትውልድ የሚተርፍ ሥራ መሥራት የምንችለው። አለበለዚያ በግለሰቦች ፍላጎት ብቻ፣ በጉልበትና በታይታ የምንሠራው ሥራ ለወደፊቱ ትውልድ የሚያመጣው ትሩፋት እጅግም ነው። አሁን ያለን ሕዝብ ያላከበረ፣ መብቱን ያልጠበቀ፣ እንዳሻው የሚሠራ ባለሥልጣን፣ ለወደፊቱ ትውልድ ብሎ እየሠራ ነው ለማለት አይቻልም። ሊሆን የሚችለው ለግል ስምና ዝና ብቻ ነው። የግል ስምና ዝና ደግሞ ሕዝብን ማዕከል አድርጎ በሚሠራ ሥራም ጭምር ይመጣል፣ እንዲያውም ውጤቱ በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የሕዝብን ጥቅም መጠበቅ፣ መብት ማክበር፣ ሕዝብን የልማት ዋና ማዕከል አድርጎ መሥራት ለራስም ነው።
ብዙ ከተሞች ሌላው ቀርቶ በጊዜው ብዙም የማይታወቁ በኋላ ላይ ግን ትልቅ የሆኑ ሰዎች ይሄዱባቸው የነበሩ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች ሳይቀሩ ታሪካዊ ቦታ ሆነው እንዲጠበቁ ያደርጋሉ። እኛ ግን እነ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ እነ ዮሐንስ ስብሃቱ፣ እነ ዳዊት ዮሐንስ፣ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ እነ ጌታቸው ሀብቴ፣ እነ ማርታ መብረሃቱ፣ እነ ተመስገን ኃይሌ፣ ምናልባትም እነ ጥላሁን ግዛው፣ እነ ዋለልኝ መኮንን፣ በኋላም እነ መለስ ዜናዊና ሌሎችም በርካታ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪዎች ዋና ጣቢያ የነበረውን ጆሊ ባርን በግሬደር ስንንድ ቁብ የሰጠን አይመስለኝም። አረረም መረረ ያ ቦታ የታሪካችን አንድ አካል ነው። ሌላው ቀርቶ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው አጥር ላይ ተንጠልጥለው ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩትን አጥር መናድ ለምን ያስፈልጋል። ይህ ድልድይ መገንባት ነው? ወይስ ድልድይ ማፍረስ?
በማናቸውም መንገድ ዝመና ዓላማው ምንድነው? የሰዎችን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማሻሻልና ማሳደግ በጣም አጭሩ ትርጉም ይመስለኛል። ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት በጣም የታጨቀ ሐሳብ ነው። ሲዘረዘር የሰዎችን የሚበላ የሚጠጣ፣ መጠለያ መኖሪያ፣ መጓጓዣ ትምህርት፣ ጤና፣ ሕክምና፣ ባህል፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ሃይማኖት፣ ሌሎችም መንፈሳዊና ህሊናዊ ስሜቶችን በዘመናዊ መልክ ማሟላት ነው። የፒያሳ ነፍስነት የአዲስ አበቤዎች መንፈሳዊ ስሜት መገለጫ ነው። መንፈሳዊ መገለጫ የሆነው ከላይ ለማሳየት እንደ ሞከርኩት ፒያሳ ከአዲስ አበባ እንዲሁም ከአዲስ አበቤው ሕይወት ጋር የተሳሰረ የከተማው ነፍስ በመሆኗ ነው። ይህችን የከተማዋን ነፍስ ማዘመን ማለት በማፍረስና አዲስ መገንባት ነው ማለት በፍጹም ሊሆን አይችልም። የአንድን ከተማ ነፍስ ማፍረስ ማዘመን ሳይሆን፣ ማጥፋት ነው፣ ማውደም ነው። ማልማት ወይም ማዘመን ሊሆን አይችልም። የሮም፣ የለንደን፣ የአቴንስ፣ የካይሮ፣ የኒውዮርክና የሌሎችም ከተሞች ነፍሶች እንዲጠፉ አልተደረገም። እንዲዘምኑ ግን ተደርገዋል። ማዘመንና ማጥፋት ለየቅል ነው። ማዘመን የሰዎችን ሥነ ልቦናዊ፣ ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ፣ እሴቶችን በሚያጠፋ መልክ ከሆነ መዘመን ሊሆን አይችልም። ዝመና የሚያስፈልገው ለአሁኑም ለወደፊቱም ትውልድ ነው። ስለዚህም የዝመናው ዕቅድ ራሱ የነዋሪዎችን ፍላጎትና ስሜት ያከበረ ሊሆን ይገባዋል።
ኔሮ በራሱ ስም ከተማ ለመገንባት አስቦ ሮምን አቃጠላት ተብሎ በሰፊው የታማው፣ ሁኔታው እውነት ስለሆነ ወይም ደግሞ ሕዝቡ ያልደገፈው ዕርምጃ በመሆኑ ሊሆን ይችላል። እውነትም ላይሆን ይችላል። ሮም እየተቃጠለች ኔሮ ሲዘፍን ከነበረ ግን ሕዝብ አንድ ለጥርጣሬ መነሻ የሆነ ምክንያት እንደነበረው መካድ አይቻልም። ውጤቱም የሕዝብን መብት ያላከበረ፣ ያፈናቀለ፣ ሕዝብን ለችግርና ለጉስቁልና የዳረገ ዕርምጃ ነበር ማለት ነው። የኔሮ ዕርምጃ ሮምን በከፍተኛ ደረጃ ለውጧት ሊሆን ይችላል። የዛሬዋ ሮም ከዚያ አሳዛኝ ገጠመኝ ያገኘችው ትንሽም ቢሆን ጠቀሜታ ይኖር ይሆናል። ግን ሮም ከላይ እንዳየነው በረጅም ዘመን ሒደት ነው የተገነባችው፣ የዛሬዋ ውብ ከተማ የብዙ ውጣ ውረድ ውጤት ነች። ኔሮ ግን (ብዙ የሚነሱበት ክፉ ታሪኮች እንዳሉ ሆኖ) ዛሬም ሮምን ለራሱ ዝና ሲል አቃጥሏል፣ ሕዝብን አፈናቅሏል፣ ለችግር ዳርጓል መባሉን ታሪኩ አንጠልጥሎት ይኖራል።
አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነች። ስለዚህም ማንኛውም ከተማዋን የሚመለከት ለውጥ፣ ዝመና፣ ዕድገት፣ ነዋሪዎቿን ያማከለ፣ ያማከረ፣ ስሜታቸውን የጠበቀና መብታቸውን ያከበረ መሆን አለበት። የሰዎችን መብት ያላከበረ ዕድገት፣ ዝመና ትክክለኛ ዕድገትና ዝመና ሊሆን አይችልም። እንደ አለመታደል ሆኖ አዲስ አበባ የራሷ መሪዎች አግኝታ አታውቅም። ሁልጊዜም ፖለቲከኞች ይመደቡባታል እንጂ በምርጫ እንኳን መጥተውላት አያውቁም። ተመረጡ የሚባሉትም የራሳቸውን አጀንዳ የሚያስፈጽሙባት ነች እንጂ የነዋሪዎቿን ፍላጎት ያገናዘቡና ያመዛዘኑ አይደሉም። ያም ቢሆን በምርጫ መምጣት ብቻውን የሕዝብን ፍላጎት ማሟላትን አያሳይም። የተመረጡ ፖለቲከኞች ምርጫ አሸነፉ ማለት የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት ጠብቀው ሠሩ ማለት አይደለም። ምርጫ የመጀመሪያው ደረጃ እንጂ መጨረሻ አይደለም። የተመረጡ መሪዎች የመረጧቸውን ዜጎች ስሜትና መብት በአግባቡ መረዳትና በዚያ መሠረት መሥራት አለባቸው። ምርጫ ለተከታዩ ሥራ መነሻ እንጂ ዋናው ፈተና የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎትና ስሜት የጠበቀ ለጋራ የሕዝብ ጥቅምና ዕድገት የሚውል ሥራ መሥራት ነው። በተለይ ዘመናዊ መንግሥታት የሚሠሩት ልማትና ዝመና ዋና ዓላማው የሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት መሆን አለበት። አለበለዚያማ በዓለም ላይ እኮ በምርጫ ሥልጣን ይዘው ቅልጥ ያለ ጨቋኞችና ዲክታተሮች የሆኑባቸው በርካታ የታሪክ አጋጣሚዎች አሉ። ስለዚህ አስተዳዳሪዎቻችን/ገዥዎቻችን በምርጫ አሸንፈን መጥተናልና የፈለግነውን የማድረግ መብት አግኝተናል ሊሉን አይችሉም። በዚህም ላይ ተመሥርተው የከተማችንን ነፍስ በዘፈቀደ ሊያጠፉ አይገባቸውም።
እንዳጋጣሚ በቅርቡ አንድ የቢቢሲ አጭር ዶክመንተሪ ስመለከት ነበረ። ዶክመንተሪው በዓለም ላይ ከ1‚000 በላይ በጣም ረጃጅም ፎቆች/ሕንፃዎች አሉ ይላል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በአውሮፓ ውስጥ የሚገኙት ሰባት ብቻ ናቸው። ያም ሆኖ እነዚህ በአውሮፓ የሚገኙ ረጃጅም ሕንፃዎች ከሌሎቹ ጋር በእርዝማኔያቸው ይህን ያህልም የሚወዳደሩ አይደሉም። ለዚህ ዋናው ምክንያቱ ታሪካዊ ሀብትን (Protection of Cultureal Heritage) መጠበቅና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የይቅርብኝ ውሳኔዎች (Conscious Rejection) ናቸው ይላል። በእርግጥ አንዳንዶች በጣም ረጃጅም ፎቆችንና የቀለጠ ከተማን እንደ ዝመና ምልክት ሊወስዷቸው ይችላሉ። ይህ ጸሐፊ ረጅም ሕንፃ እንዳይሠራብን ብለው የከለከሉ ትንንሽ ከተሞች ያውቃል። በቃ አያስፈልገንም ብለው ነዋሪዎች ወሰኑ። ነዋሪዎች ናቸው የወሰኑት፣ ጥቂት ባለሥልጣናት አይደሉም።
የአዲስ አበባ መንገዶች ኮሪዶር ልማት
አዲስ አበባ ውስጥ ከመጋቢት ወር መጀመሪያ ጀምሮ እየፈረሰ ያለው ፒያሳ ብቻ አይደለም። የመንገድ ኮሪዶር ልማት ተብሎ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች አካባቢ የሚገኙ ሕንፃዎች፣ ቤቶች፣ አጥሮች፣ የመብራት መስመሮች እየፈረሱና እየተነሱ ነው። በስንት መከራ ያደጉ የሚያማምሩ ዛፎች ተጨፍጭፈዋል። በአንድ አገላለጽ ከስመዋል። አንዳንዶቹ መንገዶች ገና ተሠርተው ከማለቃቸው እንደገና የማስፋት ሥራ እየተከናወነባቸው ነው። ፒያሳ ዋናውን ዜና ያዘች እንጂ “የመንገድ ኮሪዶር ልማቱ” ከፒያሳ፣ ከአራት ኪሎ መገናኛ፣ ከቦሌ በቀለበት መንገድ መገናኛ፣ ከፑሽኪን አደባባይ በቄራ፣ ጎተራ፣ ወሎ ሠፈር፣ ከመገናኛ ሲኤምሲ/አያት አደባባይ፣ አያት አካባቢም እንዲሁ የማፍረስ ሥራዎች እየተካሄዱ ነው ወይም ታስቦላቸዋል።
‹‹በመንገድ ኮሪዶር ልማቱ›› የጠፋው ንብረት ፒያሳ ላይ ከደረሰው የንብረት ውድመት ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም። ‹‹የመንገድ ኮሪዶር ልማቱ›› ዋና ዓላማ በጣም ሰፋፊ ቡልቫርዶችን፣ መንገዶችን ለአዲስ አበባ ማምጣት ነው ተብሏል። ሰፋፊ ቡልቫርዶች 19ኛውን ክፍለ ዘመን ይዞ 20ኛው ከፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ በአውሮፓም፣ በአሜሪካም ተሠርተዋል። እነ ሻንዜሊዜ፣ ስትራንድና የዋሽንግተን ዲሲን ቡልቫርዶች/እጅግ ሰፋፊ መንገዶችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ መንገዶች እርግጥ ነው ያምራሉ። ለከተሞቹም ከፍ ያለ ግርማ ሞገስ ይሰጣሉ። ዛሬ በ21ኛው ከፍለ ዘመን ግን እንደነዚህ ያሉ ቡልቫርዶች ብዙም የሚበረታቱ አይደሉም። ሥራቸውም በእጅጉ እየቀነሰ ነው። ዓለም የምትሠራቸውን ሰፋፊ መንገዶች በልኩ እያደረገች ባለችበት በአሁኑ ዘመን አዲስ አበባ እነዚህ መንገዶች ያስፈልጓታል ወይ? በዓለም ላይ የሚያማምሩ ግን ግማሽ ከተማ የሚወስዱ እጅግ ሰፋፊ መንገዶች (ቡልቫርዶች) የሌሉባቸው ከተሞች የሉም ወይ?
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአሜሪካና የተባባሪዎቿ ጦር ጠቅላይ አዛዥና በኋላም የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሬዚዳንት ድዋይት አይዘንሀወር፣ ከጦርነት የተመለሰውን ወታደርና ሥራ ያጣ ኃይል የመንገድ ፕሮጀክትና በጀት አስፈቅደው፣ ዛሬ አብዛኛዎቹን የአሜሪካንን ግዛቶች ያገናኙ በጣም ሰፋፊና ረጃጅም መንገዶችን አሠርተዋል። እነዚያ ትልልቅና አገር አቋራጭ መንገዶች ፕሬዚዳንቱ በደግ ከሚነሱባቸው ከፍተኛ ሥራዎቻቸው ውስጥ ሁልጊዜም ይጠቀሳሉ። እነዚህ መንገዶች አሜሪካንን የሚያህል አገር በመንገድ አስተሳስረዋል። ይህ ታላቅ ታሪክ ነው። ለፕሬዚዳንቱ የተረፈ ስም ነው፣ ዝና ነው።
እነዚህ የምንሠራቸው መንገዶች ዋጋቸው ምንድነው? ዋጋቸው ምንድነው ስል፣ መንገዱ የሚሠራበትን ወጪ ብቻ ማለት አይደለም። የፈረሱት የሥራ ቦታዎች፣ ቤቶች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የፈረሱት አጥሮች፣ የፈረሱት መንገዶች፣ የተጨፈጨፉት ዛፎች፣ የተነሱት የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ የውኃ መስመሮችና ሌሎችም መሠረተ ልማቶች ዋጋ ስንት ነው?
መኖሪያ ቤታቸውን ያጡ ቤተሰቦች፣ የሥራ ቦታቸውን ያጡ ሰዎችና ቤተሰቦች፣ በራሳቸው ከተማ የተፈናቀሉ፣ ትናንት መኖሪያ ቤት የነበራቸው፣ ቤታቸውን ዛሬ ማንሳት አለብህ ተብለው የሱሪ ባንገት ትዕዛዝ የተሰጣቸው፣ በጥድፊያ ቤት አልባ የሆኑ ሰዎች፣ የሥራ ቦታቸው የፈረሰባቸውና የዕለት ጉርስ የተዘጋባቸው ሰዎች ቁሳዊ ጉዳት ምን ያህል ነው? እነዚህ ሰዎች በደረሰባቸው መፈናቀል የደረሰባቸው ህሊናዊ ጉዳትስ ምን ያህል ነው? እኛ በአጋጣሚ ቤታችን ለጊዜው ያልፈረሰው፣ የሥራ ቦታችን ለጊዜው ያልፈረሰው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በምናየውና በምንስማው የመፍረስ፣ የመቆረጥ፣ የመፈናቀል ዜና የደረሰብን የህሊና ጉዳት ዋጋው ምን ያህል ነው? በአዲስ አበባ ውስጥ መኖር አስተማማኝ ባለመሆኑ እየደረሰብን ላለው የህሊና ጭንቀት፣ ተስፋ ማጣት/እርግጠኛ አለመሆን ዋጋው ምን ያህል ነው? መንገድ በየቦታው እየተዘጋ፣ የትራፊክ መጨናነቅ በመድረሱ የደረሰብን ጉዳት ዋጋው ምን ያህል ነው? ይህ እንግዲህ አንዱ ገጽታ ነው። ይህ የፈረሰው የወደመው የአገር ሀብት ነው። በዚህ ውድመት አገር ምን ያህል ተጎዳች? የሚደንቀው ደግሞ በአንዳንድ መንገዶች ላይ (ከተባለው ኮሪደር ውጭ) የፀደቁ፣ ያደጉ በጥሩ ሁኔታ ጥላ እየሰጡ ያሉ ዛፎች ሳይቀሩ እየተቆረጡ አዳዲስ ዛፎች እየተተከሉ ነው።
ከመንገድ ኮሪደሩ ጋር በተያያዘ አንድ ባለሥልጣን እየፈረሱ ያሉት ግንባታዎች፣ ቤቶችና የሥራ ቦታዎች ከመንገዱ ጋር ‹‹የማይመጥኑ›› በመሆናቸው ነው የሚፈርሱት ሲሉ ሰምተናል። ይህ አባባል በጣም የሚያሳዝን ነው። ብዙዎቹ የፈረሱና እየፈረሱ ያሉ ቤቶች፣ በየጊዜው ከተማዋን ሲያስተዳድሩ በነበሩ ኃላፊዎች ፈቃድ ይመጥናሉ ተብለው ፈቃድ የተሰጣቸው፣ በሚኖሩባቸው፣ ቤተሰብ እያስተዳደሩ የዕለት ጉርሳቸውን ለማሸነፍ ሲሠሩባቸው በነበሩ ሰዎች ላብና ድካም የተሠሩ ናቸው። አሁን አይመጥኑም ማለት ቤቶቹንና የሥራ ቦታዎቹን ብቻ ሳይሆን ሰዎቹንም የሚመለከት ይመስላል። ይህ በጣም ቅጥ ያጣ አገላለጽ ነው። እየፈረሱ ያሉት ቤቶች በርካታ ቤተሰቦችን ያኖሩ የነበሩ፣ ሰዎች እየሠሩ ራሳቸውንም የሚያስተዳድሩበት፣ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት፣ ከሥራቸው በሚያገኙት ገቢ ላይም ለመንግሥትም ግብር የሚከፍሉባቸው ቤቶች ናቸው። እነዚሁ ሰዎች ናቸው ዛሬ ቤታቸውን ለማፍረስ ግሬደር፣ አካፋ፣ ዶማ ይዘው የመጡትን ሰዎች መሪዎቼ ይሆናሉ፣ መብቴን ያስከብሩልኛል፣ በወጉ ያስተዳድሩኛል ብለው የመረጡአቸው። ዛሬ ቤታቸው ወይም ሥራቸውን የሚያካሂዱበት ታዛም ሆነ ከለላ፣ ወይም መደበኛ ቤት ለመንገዱ አይመጥንም እየተባለ እየፈረሰ የሚገኘው።
በሌላ በኩል ደግሞ የመልሶ ግንባታው ወጪ ምን ያህል ነው? ምናልባት ፒያሳ በፈረሱት መኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ቦታ ላይ ሕንፃ የሚገነቡት የግል ባለሀብቶች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ በግል ባለሀብቶች የሚሠሩ ግንባታዎች ለሕዝብ ጥቅም የሚሠሩ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ጥያቄ ለጊዜው እንተወውና ከመንገዱ ዳርና ዳር የነበሩ ቤቶችን፣ መንገዶችን፣ የመብራት መስመሮችን፣ የውኃ መስመሮችን፣ የተቆረጡ ዛፎችን መተካቱ፣ መሬቱን እንደ ገና ማሳመሩ (Landscaping and Decoration) ዋጋው ምን ያህል ነው? እነዚህን ከየአቅጣጫው የሚመጡ ወጪዎችና ጉዳቶች ባለሙያዎች፣ ጉዳዩ የሚሰማቸው ድርጅቶች ሠርተውት አንድ ቀን ሪፖርት ያደርጉታል ብዬ አስባለሁ። መሠራትም አለበት፣ ምክንያቱም ታሪካችን ነዋ።
በተለይ ደግሞ ካለንበት አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ እነዚህ ወጪዎች በአሁኑ ወቅት ተገቢ ናቸው ወይ? የሚለው መልስ ስለሚያስፈልገው ነው። ‹‹ሥራ የፈታ መነኩሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል›› እንደሚባለው ነው እንዳንል ብዙ የምንሠራቸው ነገሮች አሉ። ላለፉት ዓመታት አገራችን ያለችበት ሁኔታ ለማንም ግልጽ ነው። በጣም በትንሹ ከ2007 እና 2008 ዓ.ም. ጀምሮ አስካሁን አገራችን እንደተናጠች ነው ያለችው። የእርስ በርስ ግጭቱ፣ የሰዎች ሞት፣ መፈናቀል፣ የሰላም ዕጦት እንዳለ ነው። አሁን ደግሞ ረሃብ፣ እንደ ወባና ኮሌራ ያሉ ወረርሽኞች በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነውብናል። ከሰሞኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነ መሥሪያ ቤት፣ የእህል እጥረትና ረሃብ ላለባቸው አካባቢዎችን ዕርዳታ ለማቅረብ በእጄ ካለው ገንዘብ በተጨማሪ ቢያንስ አንድ ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ማለቱን ሰምተናል። ምንም እንኳን የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት ሐሰት ነው ቢሉም፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የእህልና የመድኃኒት እጥረቱ በጣም የከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ነዋሪዎችና አንዳንድ የአካባቢው ባለሥልጣናት ሲማፀኑ ሰምተናል። አገሪቱ እንዲህ ባለ ችግር ላይ እያለች ተጨማሪ ተፈናቃይ፣ ሥራ አጥ፣ መፍጠር ተገቢ ነው ወይ? መቅደም ያለበት ከላይ የተገለጹትን ችግሮች ማስወገድ መሆን የለበትም ወይ? ቅድሚያ ለሰው ልጆችና ለሰላም መሆን የለበትም ወይ? ለዚያውስ እነዚህ ቅንጡ ሰፋፊ ቡልቫርዶች አስፈላጊ ናቸው ወይ? የሚለውም መታየት አለበት።
እንዲያው ለትዝብት ያህል የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት መሪዎች ጉባዔ ከመደረጉ በፊት በነበሩት ወራትና ዓመታት፣ አዲስ አበባ ስንት ተፈናቃዮችን ታስተናግድ ነበረ? በየመንገዱ፣ በየንግድ ማዕከሉ በራፍ፣ ሰው ይገኝበታል በተባለው አካባቢ ሁሉ ልጆች ታቅፈው፣ ምርኩዝ ይዘው፣ በላያቸው ላይ ያለቀ ነጠላና የተገኘውን እራፊ ለብሰው ሕይወታቸውን ለማቆየት ምፅዋት ሲለምኑ፣ በየመንገዱ ሲንከላወሱ የነበሩ በርካታ ሰዎች እንደነበሩ በዓይናችን ያየነው ነው። ችግራቸው አንጀታችንን የበላን፣ ካለን ላይ የቻልነውን ያህል ለማካፈል ስንሞክር የቆየንበት ነው። ይህንን ማንም ሊክደን፣ ሐሰት ብሎ ሊያስተባብለን አይችልም። ከስብሰባው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ግን እነዚያ ሁሉ የተፈናቀሉ፣ የተጎሳቆሉ ዜጎች/ሰዎች ወዴት እንደሄዱ የሚያውቀው መንግሥት ብቻ ነው። በሆነ ተዓምር መልሰው ተቋቁመው ወይም ወደ ቀዬአቸው ተመልሰው እንደሆነ ግን እኛ አናውቅም። አሁን ከጉባዔው በኋላ ደግሞ፣ መንገድ ላይ የሚታዩት ተፈናቃዮች ቁጥር እንደ ገና እየጨመረ ይመስላል። ይህ የሰብዓዊ ችግሩ አንዱና በጣም ትንሹ መገለጫ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሙቀቷ እየጨመረ ነው። ይህ አጠቃላይ የዓለም ችግር ነው ሊባል ይችል ይሆናል። እርግጥ ነው እ.ኤ.አ. በ2023 ሪኮርድ መያዝ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ ሙቀት የነበረበት ዓመት ነው ተብሏል። የእኛም አገር ከዚህ ችግር ውጪ ልትሆን እንደማትችል ይህ ጸሐፊ ይረዳል። ሆኖም ግን አዲስ አበባ ለወትሮው ከባህር ጠለል በላይ ባላት ከፍታ ምክንያት ቀዝቀዝ ያለች ነበረች። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢዋ ደኖች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል። አሁን ግን ምንም እንኳን ላለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት የደን ልማትና ማስፋፋት ሥራውን አጠናክሮ የተያያዘ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ ከሚታየው የአዲስ አበባ ደኖች ጭፍጨፋ፣ ጋራዎች ላይ ቤት መሥራት እየተስፋፋ መሄዱ፣ የአዲስ አበባን ቀዝቃዛ አየር ምንጮች እየቀነሰና እየተገዳደረ የሚገኝ ይመስለኛል።
ይህንን የግል ምልከታዬን የሚቲዮሮሎጂ ባለሙያዎች ትክክል አይደለም የሚሉ ከሆነ፣ ስህተቴን ለማረም ዝግጁ ነኝ። ከሃያና ሃያ አምስት ዓመታት በፊት አዲስ አበባ ብትሞቅ እንኳ ከ23-26 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ አትሞቅም። ከአንድ ሦስት ወይም አራት ዓመት በፊት ይመስለኛል ሙቀቱ 31 ዲግሪ ሴልሺየስ ደርሶ አይቼ በጣም ደንቆኝ ነበር። ይህ አዲስ አበባ ውስጥ የማይታሰብ ነበር። ይህን የታዘብኩት በግንቦት ወር ውስጥ ነው። ግንቦት ለወትሮውም ሞቃት ነው፣ ግን 31 ዲግሪ ለአዲስ አበባ በጣም ከፍተኛ ይመስለኛል። የሚገርመው ግን ይህ ሙቀት በዘንድሮው ዓመት በግንቦት ሳይሆን በየካቲትና የአሁኑ ዝናብ ከመምጣቱ በፊት በመጋቢት ወር ውስጥም ተባብሶ ቀጥሎ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት ያውም በግንቦት፣ ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን የነበረ ከፍተኛ የሙቀት መጠን አሁን ግን በየካቲትና በመጋቢት ወራት በተደጋጋሚ 31 እና 32 ዲግሪ ሴልሺየስ ደርሶ ታዝቤአለሁ።
ይህ ሙቀት የዓለም አጠቃላይ ሙቀት መጨመር፣ በተጨማሪም የኤሊልኒኖ ሁኔታ ያመጣው ነው ሊባል ይችላል። ሆኖም የአካባቢው ደን መሳሳት፣ የአስፋልት መንገዶች መስፋት፣ የመስታወት ሕንፃዎች መብዛትና የመሳሰሉት ሰው ሠራሽ ነገሮች ሙቀቱን አላባባሱትም ማለት አይቻልም። አሁን የምንጨምራቸው ሰፋፊ ቡልቫርዶች ደግሞ ያባብሱታል አንጂ አይቀንሱትም። እነዚህ ልማቶች በእርግጥ ያስፈልጉናል ወይ? ከላይ ከጠቃቀስኳቸው ዋጋዎች በላይ ጥቅማቸው ይበልጣል ወይ? ለታይታ መልካም ሊሆን ይችላል፣ ለጎብኝዎች መደመምን ሊፈጥር ይችላል፣ ለአዲስ አበባ ነዋሪ ግን ምን ዋጋ ይጨምርለታል?
አብዛኛዎቻችን በመካከለኛ ዕድሜና ከዚያ በላይ የምንገኝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ፣ የሕይወታችን አብዛኛውን ጊዜ መንገድ ይሠራል እየተባለ መንገድ ሲዘጋ፣ ማሳበሪያ መንገድ ስንፈልግ፣ ለሰዓታት ቆመን ማለፊያ ስንጠብቅ፣ በሌሊት ተነስተን መንገድ ሳይዘጋ ወደ ሥራ ወይም ልጆች ትምህርት ቤት ለማድረስ ስንጣደፍ ነው የኖርነው። አንድ ጊዜ በአንድ ትልቅ የመንገድ ሥራ ምክንያት መንገድ ተዘግቶብን ለረጅም ጊዜ መቆየታችንንና ሁልጊዜም ከ11 ሰዓት በፊት እንደምንነሳና አጅግ በጣም ብንዘገይ ከ12፡30 ሰዓት በፊት ከቤታችን መውጣት እንዳለብን፣ ይህ ደግሞ ለዓመታት የተለመደ ሥራችን መሆኑን ይህ ጸሐፊ እያማረረ ሲናገር አንድ ወዳጁ፣ ‹‹አይዞህ ይህ መንገድ ሲያልቅ ችግሩ ሁሉ ይቃለላል፣ ትንሽ ነው የቀረው፣ ትንሽ ታገስ፤›› ያለውን ያስታውሳል። መንገዱ ተሠርቶ ካለቀ አሁን ወደ አስራ አምስት ዓመት ይሆነዋል። መንገዱ ሲያልቅ የባቡር ሐዲድ መስመር ዝርጋታው መጣ፣ እንዲህ እያለ ሌሎች መንገዶችም መሠራታቸው ቀጠለ። የትራፊኩ ችግር ግን አየተባባሰ መጣ እንጂ አልቀለለም። ምናልባት ይህ አዲሱ የሰፋፊ መንገዶች ሥራ (ቡልቫርድ) የአዲስ አበባን የትራፊክ ችግር ያቃልለዋል ተብሎ ታስቦ ከሆነ፣ በዚህ ጸሐፊ እምነት አያቃልለውም። የትራፊክ ችግር መሠረታዊ የዕይታ ለውጥ (Paradigm Shift) ይፈልጋል እንጂ የመንገድ ስፋት መፍትሔ አያመጣም። እንዲያውም ይህ የከተማዋን ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድ ሰፊ የመንገድ ኮሪዶር የአዲስ አበባን ሙቀት ከሚያባብስና ‹‹ጉድ ነው›› ከሚባል በቀር የትራፊክ ችግርን አያስቀርም። ቢሆን ኖሮ ያ ወዳጄ እንዳለው ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት በመሠራት ላይ የነበሩት መንገዶች ሲጠናቀቁ የትራፊክ ችግር ይቃለል ነበረ። ያም ባይሆን ከዚያ ወዲህ የተጀመሩት መንገዶች ሲጠናቀቁ የትራፊክ ችግር ይቃለል ነበረ፣ እስካሁን አልተቃለለም። እንዲያውም የትራፊክ ችግር እየተባባሰ ነው። የሚሠሩት ቡልቫርዶችም አያቃልሉትም። እንዲያውም ከላይ ከተዘረዘሩት ችግሮች ጋር ተዳምሮ አዲስ አበባን የባሰ ፌርሜሎ እያደረጋት ይሄዳል።
ያ ሁሉ ሆኖ ሕዝብ በሕይወቱ፣ በንብረቱ፣ በሥራው፣ በሥነ ልቦናው የሚደርስበትን ጉዳት እንዴት ነው ጥቂት ባለሥልጣናት ብቻ የሚወስኑበት? ያውም እንዲህ ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ሲታሰቡ ከቦታው የሚነሱ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢው ነዋሪ በሙሉ ሊመካከርበትና ሊስማማበት፣ ተገቢ ካሳ ሊከፈል፣ ይገባል የሚል ሕግ እያለ?
ይህ ጸሐፊ የግል ቤት የነበራቸው ሰዎችም ሆኑ በመንግሥት/በቀበሌ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ የነበሩና የሥራ ቦታቸው አድርገው ሲኖሩ የነበሩ ሰዎች በሙሉ መብታቸው በአግባቡ ሊከበር፣ ሊጠበቅ ሲገባ፣ የማፈናቀሉ ሥራ የሰዎችን መብት ያላከበረ፣ የሕዝብ ጥቅም ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ የጎደለው ነው ብሎ ያምናል። ከተመለከታቸው ሁኔታዎች ሰዎች ቀድሞ ነገር በዚህ ጊዜና ሁኔታ ከቤታቸው፣ ከቀዬአቸውና ከሥራ ቦታቸው ሊፈናቀሉ አይገባም የሚለው ሙግት እንዳለ ሆኖ፣ አብዛኛው የተነቀለው ሰው በአጭር ጊዜ ማስጠንቀቂያ፣ አንዳንዱም ምትክ ሊሰጥህ የሚችለው ከመኖሪያ ወይም ከሥራ ቦታ ስትመርጥ ነው እየተባለ፣ ከአንድ ሳምንት በፊት ያላችሁበት ቦታ ይፈርሳል የተባሉ ሰዎች በሳምንቱ መጨረሻ ወይም ከአሥር ቀን በኋላ ሰዎቹ ቤታቸውን ዘግተው በሄዱበት፣ አፍራሾች መጥተው እስከ ሰዓት በኋላ ዕቃችሁን ካላወጣችሁ ቤቱን ልናፈርሰው ነው የተባሉበት፣ የፍርድ ቤት ዕግድ አምጥተው የተሳቀባቸው እንዳሉ ያውቃል።
ሌላው የሚገርመው ገንዘቡ ከየት ነው የሚመጣው? ወጪው በግራም በቀኝም የትየለሌ መሆኑን አይተናል። ይህንን ሁሉ ወጪ እንዴት ነው መሸፈን የሚቻለው? ይህንን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ አሁን ላለንበት ችግር ማዋሉ ይቅር፣ ምናልባት ሐሳቡ ቅንጦት ሊሆን ይችላል። የኑሮ ውድነቱን፣ ግሽበቱን፣ አዲስ ሥራ አጥ መጨመሩን፣ የጦም አዳሪውን መጨመር አያባብሰውም ወይ? የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በዚህ ላይ ምን ብለዋል? ምንስ ይላሉ?
ለዚህ ሁሉ ለሚፈርሱት ግንባታዎችና ቤቶችም ሆነ ለሚሠሩት ቤቶች የሚወጣው ወጪ ከየት የመጣ ነው? ወይም ከየት ይመጣል? ከላይ እንደተመለከተው፣ ይህ ገንዘብ የተፈናቀሉትን መልሶ ለማቋቋም፣ የተራቡትን ለመመገብ፣ በበሽታ ለሚሰቃዩት ሕክምናና መድኃኒት እንዲደርስ ለማድረግ፣ ካልሆነም ሌሎች መንገድ ለሌላቸው አካባቢዎች መንገድ በመሥራት፣ ትምህርት ቤት ለመሥራት፣ አገር ለማረጋጋት (በጉልበትና በጦር ሳይሆን)፣ ሰላም ለማምጣት ቢውል አይሻልም ነበር ወይ? የሚለውን ሐሳብ መሪዎቻችን እንዴት ሊስቱት እንደቻሉ መረዳት በጣም ይከብዳል። አቶ አሰፋ ጫቦ አንድ ጊዜ ሲጽፍ፣ ‹‹የኢሕአዴግን ሐሳብ እንኳን ሰው እግዚአብሔርም አያውቀውም›› ያለውን ይህ ጸሐፊ ያስታውሳል። ተመልሰን እዚያው ገባን ወይ? ፕሮፌሰር መስፍንም እኛ አገር ዕውቀት ከሥልጣን ይመነጫል ያሉት አባባልም አለ።
ይህን ገንዘብ አንድም አፍንጫውን ተይዞ የጣሪያ ግድግዳ ግብር እየተባለ የአዲስ አበባ ሕዝብ እያለቀሰ የሚያዋጣው፣ ምናልባት የተወሰነው ከግብር ሌላው ደግሞ ከዕርዳታ የተገኘ ሊሆን ይችላል። የግብርና የአዲስ አበባ ሕዝብ የግድ መዋጮ መቼም ዕዳው ገብስ ነው። ሕዝቡ እንዲህ እየተፈናቀለ፣ እየተራበ፣ የእርስ በርስ ግጭቱ በየቦታው ሰላም እያሳጣ፣ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ መሄድ ፈተና እየሆነ፣ የኑሮ ውድነት ከልክ እያለፈ፣ ግሽበት ጣሪያ እየነካ፣ የሥራ አጥነት በየቀኑ እያሻቀበ፣ ከተማ አፍርሼ ከተማ ልሠራ ነው፣ መንገድ አፍርሼ ላሰፋ ነው፣ ቡልቫርድ ልሠራ ነው ብለን ስንለምን ህሊናችን ምን ይለን ይሆን? ህሊናችንስ እሺ ይቅር፣ የምንለምናቸው ወገኖችስ አይታዘቡንም ወይ? መታዘቡም ይቅር፣ ገንዘቡም ተመልሶ የማይከፈል ይሁን፣ እንዲህ ያለ ዕርዳታ የሚሰጡን ወገኖች የረጅም ጊዜ ግባቸውና ዓላማቸው ምንድነው? የዕርዳታው ዓይነትና መጠን፣ የሚያመጣው የረጅም ጊዜ ተፅዕኖ ምንድነው? ይህ መቼም የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። የፋይናንስ፣ የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራን፣ የሕግ አዋቂዎች፣ ሌሎችም ሌሎችም ባለሙያዎች በሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በኩል አጥንተው፣ በግልም በውይይት መድረኮችም ተሳትፈው፣ ጉዳዩን መርምረው ተወያይተው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመወሰኑ በፊት ምክረ ሐሳብ ሊያቀርቡበት፣ ምክር ቤቱም ነገሩን አብላልቶ አውጥቶ አውርዶ ሲያምንበት፣ ከአገሪቱ ጠቅላላ በጀት ውስጥ ጨምሮ ውሳኔውን ሊሰጥ ይገባል። ያካልሆነ ወዴት እየሄድን ነው የሚለው ጥያቄ በእጅጉ ያሳስባል።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡