
እኔ የምለዉ ይድረስ ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ
ቀን: April 7, 2024
‹የፆም ወራት የተኩስ አቁም› ለምን አይታወጅም?! –
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
- እንደ መንደርደሪያ
ዓለምን ክፉኛ ባመሰቃቀለውና ሚሊዮኖች በገፍ ባለቁበት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮፓውያኑ የተገበሩት አንድ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ነበር፡፡ ይህ የተኩስ አቁም ‹‹the Christmas Truce/የልደት በዓል ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም›› በመባል ይታወቃል፡፡ መነሻውም አውሮፓውያን በታላቅ መንፈሳዊና ባህላዊ ድምቀት በሚያከብሩት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት/በገና በዓል ሲሆን፣ በዚህ ሰላም በታወጀበት የደስታ/የሐሴት ቀን፣ ‹‹መዋጋት፣ ጦርነትና ደም መፋሰስ የሚገባ አይደለም፤›› በሚል ተግባራዊ ያደረጉት እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ፡፡
እንዲሁም እንደ ክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮም፣ ‹‹Christmas is the Holiday of Forgiveness and Gifts/የልደት/የገና በዓል የዕርቅ/ይቅርታና የስጦታ በዓል ነው›› በሚል በልደት በዓል ዋዜማና የበዓሉ ዕለት በጦርነቱ ወቅት በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲፋለሙ የነበሩ አውሮፓውያን ወታደሮች ጊዜያዊ የሆነ ተኩስ አቁም በማድረግና ስጦታ በመለዋወጥ የገና በዓልን ያለ መሣሪያ የተኩስ ልውውጥ ያሳለፉበት ክስተት ነው፣ ‹‹The Christmas Truce/የልደት በዓል ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም›› ስምምነት፡፡
ይህን በጎ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ይዘን እኛስ እንዴት ነው ቢያንስ በዚህ ፍቅር፣ ሰላምና ዕርቅ በሚሰበክበትና በሚታሰብበት የዓብይ ፆምና የረመዷን የፆም ወራት፣ ‹የፆም ወራት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም/the Fasting Truce› እንዲደረግ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አዋጅ ቢያስነግሩ ምን አለበት፡፡ መንግሥትም ከእልህና በመሣሪያ ኃይል ችግሩን እፈታለሁ ከሚለው ግትርነት ወጥቶ የሃይማኖት አባቶችን በቅንነት መንፈስ ቢተባበር፡፡
ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከሁለት ዓመት በፊት የኮሮና ወርረሽኝ ወቅት በሃይማኖት ተቋማትና በመንግሥት ትብብር በሁሉም ቤተ እምነቶች ፀሎት/ምህላ ታውጆ ነበር፡፡ የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ በወቅቱ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ኮሮና ሕይወታቸውን የነጠቀን ወገኖቻችን ቁጥር አሥር ሺሕ እንኳን አይሞላም፡፡ እንደ አገር ያደረሰብን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብዓዊ ቀውስም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜን የአገራችን ክፍል (በትግራይ፣ በአማራና በአፋር) ካደረግነው ጦርነትና አሁንም በአማራና በኦሮሚያ የአገራችን ክልሎች ካለው ጦርነት ጋር ሲነፃፀርም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ባሳለፍነው የሁለቱ ዓመት ጦርነት ያደረሰብንን ምስቅልቅል በጥቂቱ ለማስታወስ እንሞክር እስቲ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ባደረግነው የእርስ በርስ ጦርነት በታሪካችን ከውጪ ወራሪ ኃይሎችም ሆነ እርስ በርሳችን ባደረግናቸው ጦርነቶች ከደረሰው ዕልቂት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ስደት፣ ወዘተ አንፃር አቻና ተወዳዳሪ ያለው አይደለም፡፡
ከሃይማኖት አባት እስከ አገር ሽማግሌ፣ ከአፈ-ነቢብ እስከ ምሁራን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በሆንበት በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት የደረሰው ዕልቂት (የቁጥሩ ነገር አከራካሪ ቢሆንም በዚህ ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ ለሞት መዳረጉ ይነገራል)፣ መፈናቀል፣ የመሠረተ ልማት ውድመት፣ ወዘተ በአጠቃላይ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊውና ፖለቲካዊ ቀውሱ ከምንገምተው በላይ ነው፡፡
የጦርነት ጎዳና ብዙ ስብራት አምጥቶብናል፡፡ የትግራይ ጦርነቱ ይቁም እንጂ ትቶት ያለፈው ጦስ ቀላል አይደለም፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩትን ሕይወት አሳጥቷል፣ በርካቶችን ለአካል ጉዳተኝነት ዳርጓል፡፡ ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል፣ ከእጥፍ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለከፍተኛ ምግብ እጥረት አጋልጧል፡፡ ልጆችን ያለ ወላጅ፣ ወላጆችን ያለ ልጅ አስቀርቷል፣ ሚስቶችን መበለት አድርጓል፣ ሕፃናትን ሳይቀር ማግዷል፡፡ ኢትዮጵያ እናቶችና አረጋውያን ልባቸው ክፉኛ የተሰበረባት ምድር ሆናለች፡፡
በዚህ ጦርነት ውስጥ ልጆቻችን፣ እህቶቻችንና እናቶቻችን ዘግናኝ በሆነ መንገድ ተደፍረዋል። የአካል ጉዳታቸውና የሥነ ልቦና ስብራታቸው ከቃል በላይ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራችን ስም ጠልሽቷል፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ እንዲነሳ ጥላቻ ተዘርቷል፡፡ የምዕራቡ ዓለምም ፊቱን አዙሮብን ከርሟል፡፡ በርካታ የጤና፣ የትምህርትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፈርሰዋል። አኮኖሚያችንን አድቅቋል፣ ዕዳችንንና ኑሯችንን አክብዷል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሁሉ ረገድ አክስሮናል፡፡ በአጠቃላይ በአገሪቱ በጦርነቱ ሳቢያ የደረሰው ውድመት 1.5 ትሪሊዮን ብር ወይም 28.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነና ለመልሶ ግንባታ ብቻ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ በተለያዩ ጊዜያት ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ሊፈታ ከሚችል ግጭት ውስጥ የተወለደ የወንድማማቾች ጦርነት እንደ መሆኑ መጠን፣ በታሪካችን ትልቅ ጥቁር ጠባሳ ትቶ አልፏል፣ ገና እያለፈ ያለ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ የጦርነት ውድመትና ቀውስ መማር ያቃተን እኛ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ከጦርነት አዙሪት ለመውጣት አልተቻለንም፡፡
ከዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ቀውስ መውጣት እንዲቻለን የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባዔ ተግባራዊ የሆነ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ ለኮሮና ወረርሽኝ አገር አቀፍ ፀሎትን/ምህላን ያወጀው የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ተቋማት ጉባዔ አሁንም ቤተ እምነቶችን አስተባብሮ ምነዋ ሚሊዮኖችን ላሳጣንና አሁንም በየቀኑ ዜጎቻችንን እንደ ቅጠል እያረገፈ ላለው የእርስ በርስ ጦርነት አገር አቀፍ ፀሎት/ምህላ እንዲታወጅና በእነዚህ የፆም ወራትም ‹‹የተኩስ አቁም›› እንዲተገበር መልዕክት ለማስተላለፍ ስለምን ደከመ?
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚገኙ ምዕመናን በፆምና በፀሎት የፈጣሪን ፊትና ምሕረት በሚሹበት በእነዚህ ቅዱስ የፆም ወራት፣ በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎች ጠመንጃቸውን ዘቅዝቀውና የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ በነጋ ጠባ በጦርነት እሳት እየተለበለቡ ያሉ ዜጎቻችን ጥቂት እረፍት እንዲያገኙ፣ በግፍ እየታረዱና በጠራራ ፀሐይ እየታገቱ ያሉ ወገኖቻችንም የሚታደጋቸው ያገኙ ዘንድ፣ የእናቶችና የሕፃናት ዋይታና ሰቆቃ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ያባራ ዘንድ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባዔ ሁለቱ ታላላቅ ቤተ እምነቶች በፆምና በፀሎት ተጠምደው በሚገኙበት በዚህ ቅዱስ የፆም ወራት ‹የፆም ወራት የተኩስ አቁም አዋጅ› በሃይማኖት አባቶች/መሪዎች አማካይነት ቢታወጅ የሚል ለውይይት መጫሪያ የሚሆን ሐሳብ ለማንሳት ወደድኩ፡፡
- ዕርቀ ሰላም ማውረድ ስለምን ተሳነን?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የጌታችንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ዓብይ ፆም የምንፆምበት፣ እንዲሁም በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድም የታላቁ የረመዷን ፆም የሚከናወንበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ እናም በተለይ በእነዚህ ጊዜያት አብልጠን በፆም፣ በፀሎትና በስግደት ወደ ፈጣሪ መቅረብ እንዳለብን፣ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ እንድንተጋና ሰላምና ዕርቅ እንድናወርድ የየሃይማኖቱ መምህራን ለምዕመናኖቻቸው አብዝተው ያስተምራሉ፣ ይመክራሉም፡፡
ቅዱሳት መጻሕፍትም፣ ‹‹ስትፆሙ እንደ ግብዞች አትሁኑ፣ መባህን በመሰዊያው ላይ ከማቅረብህ በፊት ከወንድምህ ጋር አስቀድመህ ታረቅ፣ ይቅር እንድትባሉ ይቅር በሉ፣ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር ተባባሉ፡፡ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፣ ዕርቀ ሰላምን የሚሰብኩ (የሚያስታርቁ) ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና…›› በሚሉ የምክርና የተግሳጽ ኃይለ ቃላት ልባችንን ለሰላምና ለዕርቅ፣ ለፍቅርና ለበጎ ሥራ የተከፈተ/የቀና እንዲሆን አብዝተው ያስተምሩናል፡፡
ግና ይህ አስተምህሮ ከቃል ባለፈ በልባችን ውስጥ ፍሬ እንዳላፈራ አሁን የተዘፈቅንበት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
‹‹አብዛኛው ሕዝባችን ሃይማኖተኛ ነው›› በሚባልባት አገራችን ኢትዮጵያ ሰላምና ዕርቅ እንደ ሰማይ የራቀን፣ እርስ በርሳችን የምንጣላና የምንጠላላ፣ የምንዋጋና የምንበቃቀል፣ የምንከፋፈልና የምንከፋፋ ከሆንን ዓመታት እያስቆጠርን ነው፡፡ በእርግጥ ብዙዎች የሚቀኑበት በርካታ አኩሪ ታሪኮች ያለን ታላቅ አገር የመሆናችንን ያህል፣ በተቃራኒው ደግሞ እንደ ሕዝብ የእርስ በርስ ጥላቻችን፣ ቂምና በቀልን አስወግደን ዕርቀ ሰላምን በማውረድ ረገድ አሁንም ድረስ በትልቅ ፈተና ውስጥ ያለን ነን ብል ከእውነታው የራቅሁ አይመስለኝም፡፡
ለአብነት ያህልም ሚሊዮኖችን የገበርንበት የእርስ በርስ ዕልቂት ገና ደሙ በቅጡ ሳይደርቅ፣ የእናቶቻን ዕንባ ሳይታበስ፣ የሕፃናቱ ሰቆቃና ዋይታ አባሽ/የሚያብሰው ሳያገኝ፣ ወዘተ ለሌላ ዕልቂትና ለሌላ ጦርነት ጦራችንን ሰብቀን፣ ሰይፋችንን ስለንና ጋሻችንን ወልውለን፣
እረ ጥራኝ ጫካው፣
እረ ጥራኝ ዱሩ፣
ለአንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ በሚል ዜማ ወደ ሌላ ጦርነት፣ ወደ ሌላ ዕልቂት ተሸጋግረናል፡፡ በእርግጥም ጦርነትን ባህል ያደረግን፣ የእርስ በርስ ውጊያን የገና ጨዋታን ያህል የቀለለብን ሕዝብ ሆነናል፡፡ አንድ ኬንያዊ ወዳጄ፣ ‹‹…እናንተ ኢትዮጵያውያን ችግራችሁን ለመፍታት ቁጭ ብላችሁ ከመነጋገር ይልቅ፣ አስቀድማችሁ የጦርነት አማራጭን ካስተናገዳችሁና ብዙ ነገር ከከሰራችሁ በኋላ ነው በስንት ተማፅኖ ለንግግር/ለድርድር የምትቀመጡት…›› በማለት ልቡ ያዘነበትን ትዝብቱን አካፍሎኛል፡፡
ዛሬም ቁጭ ብሎ ከመነጋገርና ከመደራደር ይልቅ በጥላቻ ላይ ሌላ ጥላቻን፣ በበቀል ላይ ሌላ በቀልን፣ በቂም ላይ ሌላ ቂምን እየደረብን የሞትንና የዕልቂት መንገዱን ተያይዘነዋል፡፡ እናም ዛሬም የኢትዮጵያችን የደም ምድር/አኬልዳማ እንደሆነች ዘልቃለች፡፡
የሚያሳዝነው ወደ ፈጣሪያችን አብዝተን የምንቀርብበት፣ ለዕርቀ ሰላም የምንተጋበት በምንልበት በዚህ ቅዱስ የፆም ወራት እንኳን የሰላም ምክንያት ሆነን የወገኖቻችን ዕልቂት ልንገታ፣ የእናቶችንና የሕፃናትን ዋይታ ልናስቆምና ሰላም ልናወርድ አልተቻለንም፡፡
የሃይማኖት አባቶቻችንም ከመግለጫ ጋጋታ በስተቀር እንደ ጥንቱ ባህልና ትውፊት ታቦት ተሸክመው፣ መስቀል ይዘው መንግሥትን ለመገሰጽ፣ ዓውደ ግንባር ድረስ ወርደውም ዕርቀ ሰላም ለማውረድ፣ ጎራ ለይተው የሚፋለሙ የአንድ እናት ምድር የማህፀን አብራኮችን ‹አንተም ተው አንተም ተው› ብለው ለመዳኘት አልተቻላቸውም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች በአደባባይ ወጥተው ጦርነትን የሚያውጁ፣ ‹‹እንዴት አንድ ገዳይ፣ እንዴት አንድ ወንድ ይጠፋል?›› የሚሉ የጦርነት ሰባኪ የሃይማኖት አባቶችን ታዝበናቸዋል፡፡
- እንደ መውጫ
እ.ኤ.አ. በ2015 በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ሰላም ለማስፈንና ግጭቶችን ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎችን ሚና በተመለከተ፣ ከኢጋድ አባል አገሮች የተውጣጡ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች ‹‹IGAD Countries Religions Leaders Consultation on the Welfare of the Region›› በሚል መሪ ቃል የተሳተፉበት አንድ ስብሰባ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ለሦስት ቀናት ተካሂዶ ነበር፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ በወቅቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ ‹‹Peace and the Human Race›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት የጥናት ወረቀታቸው የሚከተለውን ሐሳብ አንስተው ነበር፡፡
‹‹ሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት ጎልቶ በሚታይበት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አብዛኛው ሕዝቧ አማኝ በሆነባት አገር፣ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ግጭቶች በሚከሰቱበት ወቅት ወደ አስከፊ ደም መፋሰስና ጦርነት እንዳያመሩ በሰላምና በዕርቅ እንዲቋጩ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው›› አስረድተው ነበር፡፡
ታሪካዊ አብነቶችን ለመጥቀስም ያህልም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ በተለይም ደግሞ አገራችን ኢትዮጵያ በዓለማችን የሚገኙትን ሦስቱን ታላላቅ ሃይማቶችን ጁዳይዝምን፣ ክርስትናንና እስልምናን በሰላም ተቀብላ ያስተናገደች፣ የዘር/የብሔር/የጎሳ፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት ሳያግዳት ከፍ ባለ ሰብዓዊነትና ፍቅር ለሰው ልጆች ሁሉ ‹ሰላምና ፍትሕ› በፅናት የቆመች አገር መሆኗን ለዓለም ያሳየች ናት፡፡
ስለሆነም እነዚህን ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ፋይዳቸው ከፍ ያሉ መልካም እሴቶቻችንን ከፍ በማድረግ እኛ የሃይማኖት መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች በአገራችን ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በአፍሪካና በመላው ዓለም ግጭቶች በሰላም እንዲቋጩና የሰላም፣ የአብሮነትና የወንድማማችነት ምልክት (Symbol) እንድትሆን በማድረግ ረገድ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት የነበራቸውና አሁንም ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ስለሆነም የሃይማኖት አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች ቢያንስ በዚሁ የፆም ወራት እንኳን የመድፍና የመትረየስ ላንቃዎች ዝም ይሉ ዘንድ፣ በግፍ እየታረዱና እየተጨፈጨፉ ያሉ ወገኖቻችንን ዕንባና ደም መፍሰሱ ይቆም ዘንድ፣ የእናቶችና የሕፃናቱ ሰቆቃና ዋይታ ይገታ ዘንድ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን በተፋላሚዎች መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሰላም እንደራሴና አስታራቂ ሆነው ሊቆሙ ይገባል፡፡
በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ምዕመናን በፆምና በፀሎት የፈጣሪን ፊትና ምሕረት በሚሹበት በዚህ ቅዱስ የፆም ወራት፣ በሁሉም ወገን ያሉ ተፋላሚዎች ጠመንጃቸውን ዘቅዝቀውና የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ፣ በነጋ ጠባ በጦርነት እሳት እየተለበለቡ ያሉ ዜጎቻችን ጥቂት እረፍት እንዲያገኙ፣ በግፍ እየታረዱና በጠራራ ፀሐይ እየታገቱ ያሉ ወገኖቻችንም የሚታደጋቸው ያገኙ ዘንድ፣ እንዲሁም የእናቶችና የሕፃናቱ ዋይታና ሰቆቃ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን ያባራ ዘንድ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባዔ ሁለቱ ታላላቅ ቤተ እምነቶች በፆምና በፀሎት ተጠምደው በሚገኙበት በዚህ ቅዱስ የፆም ወራት ‹የፆም ወራት የተኩስ አቁም አዋጅ› በሃይማኖት አባቶች/መሪዎች አማካይነት ቢታወጅ…፡፡
ቢያንስ በዚህ ፍቅር፣ ሰላምና ዕርቅ በሚሰበክበትና በሚታሰብበት የዓብይ ፆምና የረመዷን የፆም ወራት፣ ‹የፆም ወራት ጊዜያዊ የተኩስ አቁም/the Fasting Truce› እንዲደረግና የድርድርና የዕርቅ መንገድ እንዲመቻች የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች አዋጅ ቢያስነግሩ ምን አለበት፡፡ መንግሥትም የሃይማኖት አባቶችን በቅንነት መንፈስ ቢተባበር መልካም ነው፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብና በምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት በዋና ጸሐፊነት ሆነው ያገለገሉ፣ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በጥናትና ምርምር ዘርፍ ከፍተኛ ተመራማሪ፣ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ባለሙያ፣ እንዲሁም በዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን (Universal Peace Federation – UPF) የሰላም አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው fikirbefikir@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡