ራስል ኮክ

ከ 3 ሰአት በፊት

የማይታሰብ የሚመስለውን ፈተና ለመጋፈጥ እራሱን ሲያዘጋጅ፤ “ቆም ብዬ ሕይወቴን ተመለከትኩት” ይላል የ27 ዓመቱ ወጣት።

ወጣቱ በአእምሮ ጤና ይሰቃያል። የመጠጥ እና የቁማር ሱሶች ሕይወቱን አመሰቃቅለውታል።

“ምንም ባጣ የሚቆጨኝ ነገር የለም” ብሎ በማመኑ ከባዱን ፈተና በመጋፈጥ በሕይወቴ ለውጥ ማምጣት አለብኝ ብሎ ተነሳ።

ራስል ኮክ የተባለው እንግሊዛዊ ሕይወቱን የሚቀይረው አፍሪካን የሚያካልል ርቀት በመሮጥ መሆኑን አምኗል።

በብዙ ፈተናዎች መካካል 16 አገራትን በማቆራረጥ 16ሺህ 400 ኪሎ ሜትሮችን በ352 ቀናት የሮጠረው ወጣት ለእርዳታ ድርጅት ከግማሽ ሚሊዮን ፓዎንድ በላይ ማሰባሰብ ችሏል።

ራስል የካቲት 2015 ዓ.ም. ሩጫውን ለማድረግ ሲነሳ የነበረው እቅድ 360 የማራቶን ውድድሮችን የሚሸፍን ርቀትን በ240 ቀናት ውስጥ ከቱኒዚያ እስከ ደቡብ አፍሪካ መሮጥ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ እቅዱ ገና በጥንስሱ የአልጄሪያ ቪዛ ባለማግኘቱ እክል ገጠመው። እጅ ያልሰጠው ራስል መነሻው ከደቡብ አፍሪካ አድርጎ በርካታ ከተሞችን አቆራርጦ፣ ተራራዎችን ወጥቶ እና ወርዶ፣ በሰሃራ በረሃ መካከል ሮጦ ግቡን አሳክቷል።

ዘረፋ እና የጤና እክል

ራስል ደቡብ አፍሪካ እና ናሚቢያን በሩጫ አቆራርጦ አንጎላ ሲደርስ ካሜራ፣ ስልክ፣ ጥሬ ገንዘብ፣ ፓስፖርት እና የጉዞ ፍቃዱን ሰነዶች በታጠቁ ዘራፊዎች ተዘረፈ።

ከሌሎች ባገኘው ድጋፍ ግን ራስል አደገኛውን የሩጫ ጉዞን ቀጠለ።

ራስል ኮክ

ራስል ግን በመንገዱ ዘራፊን ብቻ አልነበረም የተጋፈጠው። አደገኛ የጤና መቃወስ አጋጥሞት ነበር።

በየዕለቱ ከማራቶን በላይ መሮጡ በአካሉ ላይ ችግር ማምጣቱ አልቀረም።

በ45ኛ ቀኑ ሐኪሞች በደም እና ሽንቱ ውስጥ ፕሮቲን በማግኘታቸው እረፍት ማድረግ እንዳለበት አሳሰቡት።

ብዙም ሳይቆይ ወደ ሩጫው ተመለሰ።

200ኛ ቀን ሲደርስም ሌላ የጤና ችግር ገጥሞት ነበር። በዚህ ጊዜ ናይጄሪያ ገብቷል። ናይጄሪያዊው ዶክተር በየቀኑ በሩጫ የሚያካልለውን ርቀት እንዲቀንስ እና ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እረፍት እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጡት።

ራስልን ግን የሚያቆመው አልተገኘም።

“ሁለት ቀናት የወሰዱት ምርመራዎች በአጥንቶቼ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማስከተላቸውን አሳይተዋል። ስለዚህ ጠንካራ የሕመም ማስታገሻ መድሃኒት ወስዶ ወደ ሩጫ መመለስ ነው” ብሎ ራስል ወደ ሩጫው ተመልሷል።

ራስል ኮክ

ራስል ሞሪሺያስ ገብቶ ወደ አልጄሪያ ሊሻገር ሲል ከአቅሙ በላይ የሆነ ፈተና ይገጥመዋል።

278ኛው ቀን ላይ የአልጄሪያ ቪዛ በመከልከሉ ድንበር መሻገር ሳይችል ቀረ።

ራስል ጉዳዩን ወደ ማሕብራዊ ሚዲያ ወስዶ በኤክስ ገጹ እባካችሁ ተባበሩኝ ሲል ጠየቀ።

ይህ የራስል ቪዲዮ 11 ሚሊዮን ተመልካችን አግኘቶ ነበር። ይህ ቪዲዮ ኢላን መስክ እና የዩናይትድ ኪንግደም የፓርላማ አባላት ተመለከቱት።

ራስል ቪዲዮ ማውጣቱ ረድቶት በአልጄሪያ የሚገኘው የዩኬ ኤምባሲ ቪዛ እንዲሰጠው ማድረጉን አስታወቀ።

ራስልም በሩጫው ቀጥሎ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዛሬ መጋቢት 29 2016 ዓ.ም. መጨረሻውን በቱኒዚያ ያደርጋል።

ራስል ሩጫ በሚያጠናቅቅበት ቦታ በርካታ ደጋፊዎቹ እንደሚገኙ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም በዩኬ ታዋቂ የሙዚቃ ባንድ ቢዛርቴ በተሰኘች የቱኒዚያ ከተማ የሙዚቃ ድግስ ተዘጋጅቶለታል።