
ከ 5 ሰአት በፊት
ሰናይት አሰፋ “ሰርከስ ዓለሜ፣ ሕይወቴ ነው” ትላለች።
ከዚህ የልጅነት ህልሟ ያገኘችው ትርፍ ካለ ለሌሎች አርአያ መሆኗ እንደሆነ ትገልጻለች።
ብሪታንያ የምትኖረው ሰናይት በአሜሪካ፣ ስፔን፣ ስዊትዘርላንድ፣ ዱባይ፣ ቻይና፣ ጀርመን፣ ሩሜንያ፣ ቤላሩስ እና አውስትራሊያ ላይ ባሳየችው ትርዒት መድረክ ላይ ኮከብ ሆና ለመድመቅ በቅታለች።
በዓለም አቀፍ የሰርከስ ትርዒቶች ላይ የምትሳተፈው ይቺ ወጣት የተወለደችው በሰሜን ኢትዮጵየዋ ትግራይ ዋና ከተማ ከመቀለ 45 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ውቅሮ ውስጥ ነው።
“ሴት ልጅ አይደለሽ ቤትሽ አትቀመጪም!”
ሰናይት በርካታ የሰርከስ ስፖርተኞችን ካፈራው ሰርከስ ትግራይ ጋር መሥራት የጀመረችው በ11 ዓመቷ ነው።
ለሰርከስ ባላት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ሰናይት “ሰርከስ ይቅርብሽ፤ ትምህርትሽ ላይ አተኩሪ” የሚለውን የቤተሰቧን እና የማኅበረሰቡን ጫና ተቋቁማ ዝንባሌዋን ልትከተል ችላለች።
“ከቤተሰቦቼ እና ከጓደኞቼ ብዙ ጫና ይገጥመኝ ነበር። ሰዎች ‘ቤተሰብሽ የሚልሽን ለምን አትሰሚም? ሰርከስ ምን ያደርግልሻል? ሴት ልጅ አይደለሽ ቤትሽ አትቀመጭም?’ ይሉኝ ነበር። ነገር ግን ሰርከሱን ስለምወደው ውስጤ አልተቀበለውም” ስትል አጋጥሟት የነበረውን ተግዳሮቶች ታስታውሳለች።
“ሙሉ ቀን ትምህርቴን እማርና አመሻሽ ላይ ከጓደኛዬ ጋር በመሆን ወላጆቼ ሳያውቁ ወደ ሰርከስ እሄዳለሁ። አንዳንዴ አባቴ እና እናቴ እንዳይጠረጥሩኝ ሰርከስ የምሰራበትን ‘ታይት’ ከውስጥ ከላይ ደግሞ ቀሚስ ለብሼ ደብተር እና መጽሐፌን ይዤ እሄድ ነበር።”
በልጃቸው ፍላጎት ምክንያት የወላጆቿ ልብ ለሁለት ተከፈለ፤ “እናቴ አስተማሪ ስለሆነች አባቴን ‘ከፈለገች ሰርከስን መቀጠል ትችላለች’ ትለው ነበር። አባቴ ግን አልተቀበለውም።”
ወደ ሰርከስ ስትሄድ እናቷ “ገበያ ላኳት” እያሉ ብዙ ጊዜ ሸፍነውላታል። አንድ ቀን ግን ከአባቷ ጋር እንድትጋፈጥ ያደረጋት አጋጣሚ ተፈጠረ። ሰናይት ያችን ቀን መቼም አትረሳትም።
“ለትርዒት በምንለማመድበት ቀን እዚያው አደርኩ። በማግስቱ ጠዋት ‘ሰናይት የት ሄደች?’ ሲል አባቴ ጠየቀ። እናቴ፣ ‘እኔ ልኪያታለሁ’ ትላለች። በድንገት እህቴን ሲጠይቃት ‘ቤት አላደረችም’ ትለዋለች። አባቴ ሰርከስ ወደምንሠራበት ቦታ መጥቶ…ቤት ወስዶ ገረፈኝ። ነገር ግን ቅጠቱ ሰርከሱን የበለጠ እንድወደው አድርጎኛል” ትላለች።
አባቷ በግል ትምህርት ቤት ሙሉ ቀን እንድትማር ከማድረግ አልፈው ልጃቸውን ወደ ሰርከስ እንዳትሄድ የቻሉትን ሁሉ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
- የወታደሮችን ልብስ ከማጥበብ እስከ ቢሊየነርነት የደረሱት – አቶ ሰዒድ መሐመድብርሀን6 ሚያዚያ 2024
- የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያዋን ወደ ትልቅ ቢዝነስ ያሸጋገረችው ኢትዮጵያዊት17 መጋቢት 2024
- ኢትዮጵያ፡ በዩቲዩብ እንዴት ‘በቀላሉ’ ገንዘብ ማግኘት ይችላል?6 መጋቢት 2024

“ሕልሜ እውን እንዲሆን ያደረገኝ አጋጣሚ”
ሰናይት የአባቷን ከቤት መውጣት እየተከተለች ወደ ሰርከስ ስትሄድ፣ አባቷ ከቤት ውስጥ ባጧት ቁጥር ሲቆጡ ዓመታት አለፉ።
አንድ ጊዜ ግን አንዲት ሞንጎሊያዊት የሰርከስ አሠልጣኝ ሰርከስ ላይ የሚሳተፉ ሴት ልጆችን ለመመልመል ወደ መቀለ ስትመጣ ለሰናይት “ሕልሟን እውን ያደረገ ዕድል” ሆነ።
ከወላጆቿ ጋር ያላትን አለመግባባት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት እና የወደፊት ዕጣዋን ለማስተካከል ድፍረት ሰጣት።
“ለአባቴ ይህ ትልቅ ዕድል ስለሆነ ሰርከስ ውስጥ እንድሠራ ልትፈቅድልኝ ይገባል። ትምህርት ቤትም አልሄድም አልኩት። አልተቀበለውም… ለሁለት ሳምንታት ከቤት ጠፍቼ በሞንጎሊያዊቷ ሴት ወደተዘጋጀው ዝግ የሥልጠና ካምፕ ሄድኩ።”
የሰናይት ከቤት መጥፋት አባቷ አቶ አሰፋ የልጃቸውን ፍላጎት እንዲቀበሉ አስገደዳቸው።
“ሲቃወሙኝ የነበሩ ይደግፉኝ ጀመር”
ከሞንጎሊያዊቷ ካገኘችው ሥልጠና በኋላ በ14 ዓመቷ ሰናይት ከትምህርት በላይ ቅድሚያ ለሰጠቸው ሞያዋ ወደ ቻይና በመሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የሰርከስ ትርኢት ላይ ተሳተፈች።
“የቻይና የሁለት ወር የሰርከስ ጉዞዬ ጥሩ እና የተሳካ ነበር። የ14 ዓመት ልጅ ሆኜ በዚያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትውልድ አገሬ ወጥቼ ያሳየሁት ትርዒት፣ ሲቃወሙኝ የነበሩትን ‘በቃ ሰርከስ የሕይወቷ መንገድ ነው’ ብለው እንዲቀበሉ ያስቻለ ስለሆነ የማልረሳው መድረክ ነው” ትላለች።
ይህ የቻይና መድረክ ሰናይት በብዙ አገሮች ትርዒት እንድታቀርብ በር ከፍቷል። ከዚያ በኋላ በዱባይ፣ በስፔንና ስዊትዘርላንድ ከሚገኙ የሰርከስ ቡድኖች ጋር ትርዒት አቅርባለች።
ከዚያ በኋላ በግል ብዙ ዕድሎች መጡላት።
“እውነት ለመናገር በቡድን ውስጥ መሥራት የብቸኝነት ስሜት እንዳይሰማ ያደርጋል፤ ነገር ግን በግል መሥራት ደግሞ ለራ ኃላፊነት ስለሚወሰድ የበለጠ ጠንካራ ያደርጋል። ከቡድን ይልቅ በግል የሠራሁት የበለጠ ውጤታማ እንድሆን አስችሎኛል ብዬ አስባለሁ” ትላለች።
ሰናይት በተለያዩ አገራት ትርኢት ለማቅረብ ስትሄድ የቡድኗ አባላት የሆኑ ጓደኞቿ እነዚያ አገራት ውስጥ ለመቅረት ሲያስቡ እሷ ግን ይህን አልመረጠችም።
“በወጣሁበት መቅረት አልፈልግኩም፤ ምክንያቱም በችሎታዬ ውጤታማ መሆን እየቻልኩ ለምን እቀራለሁ ብዬ ነው የማምነው። በወደዱት አገር ውስጥ ለመቅረት ቀላል ነበር፤ ነገር ግን ከሕይወት መስመር ያስወጣል።”

“እውነት ሰውነቷ አጥንት አለው?”
በአሜሪካው ውድድር ‘አሜሪካስ ጋት ታለንት’ ላስ ቬጋስ፣ ኒውዮርክ፣ ጀርመን፣ በሩሜንያ ‘ሩሜንያ ጋት ታለንት’፣ ቤላሩስ፣ አውስትራሊያ- ‘ሲድኒ ኦፍ ዘ ሐውስ’ እና፣ እንግሊዝ ‘ለንደን ፓላድዮ’ ላይ ሰናይት መድረክ ላይ ስትደምቅ እና ሰውነቷን ሲተጣጠፍ በቀጥታ የተመለከቱ ተመልካቾች በችሎታዋ ተገርመው አድንቀዋታል።
የሰናይት የሰርከስ ስታይል ‘ኮንትሮሽን’ እየተባለ የሚጠራ ሲሆን መድረክ ላይ ወጥታ በምታሳያቸው ትርዒቶች እና የፈጠራ ውጤቶች የተመልካቾችን ቀልብ መግዛት ችላለች። ‘እውነት ሰውነቷ አጥንት አለው?’ የሚል ጥያቄን አስነስቷል። ሰውነቷ እንደ ላስቲክ ይተጣጠፋል።
ሰናይት ይህ ስታይል ቀላል እንዳልሆነ እና ከተፈጥሯዊ ብቃቷ ባለፈ የሰውነቷን የመተጣጠፍ ችሎታ ለመጠበቅ በየቀኑ ልምምድ እንደምታደርግ ትናገራለች።
“በልጅነቴ የሰርከስ ትርዒት እሠራ በነበረበት ጊዜ ህመም የሚሰማኝ አይመስለኝም ነበር። ጀርባዬ በተፈጥሮው በጣም ይተጣጠፋል። ነገር ግን ሥራውን ሲያዳብሩት ትንሽ እየከበደ ይሄዳል። ስለዚህ ተጣጣፊ ሰውነቴን ለመጠበቅ በየቀኑ ለሁለት ሰዓታት ልምምድ አደርጋለሁ” ትላለች።
ከዕለት ተዕለት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ ምግቦች ተጽእኖ ስላላቸው አመጋገቧም በጥንቃቄ ነው።

“ሥራ ነው የሚያስከብረው”
ሰናይት በተለያዩ የዓለም አገራት በተደጋጋሚ ተዘዋውራ የሰርከስ ትርዒት ብታቀርብም በ2013 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ትግራይን ለቃ እንድትወጣ ያደረገ አጋጣሚ ተፈጠረ።
የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ ሁለት ቀን በፊት አዲስ አበባ ነበረች። ድንገት ብዙ ነገር ተለወጠ…ከዚያ በኋላ በሙያዋ ጠቅልላ ወደ እንግሊዝ አቀናች።
ምንም እንኳን ከአገር ተወጥቶ ሕይወት ቀላል ባይሆንም የበለጠ ጠንካራ ከመሆን ሌላ አማራጭ አልነበራትም።
ብዙ ጊዜ የትውልድ አገራቸውን ጥለው ወደ ሌላ አገር ከሚሄዱ ብዙ ሰዎች መካከል አዲስ ሕይወት፣ ቋንቋው እና ባህሉ የሚፈታተናቸው ጥቂቶች አይደሉም። ሰናይት እነዚህን ፈተናዎች ያሸነፈችበት ምሥጢር ለሙያዋ ያላት ቁርጠኝነት እንደሆነ ትጠቅሳለች።
“ከልቤ የምወደው ሙያ ስላለኝ በውስጤ የምፈልገውን ስለማውቅ ሁሌም ስኬታማ ለመሆን ችያለው። ለሰርከስ ታላቅ ፍቅር አለኝ። ሁሉንም ፈተናዎች እንዳልፍ እና እዚህ ደረጃ ላይ እንድደርስ አስችሎኛል። ሕይወት አስቸጋሪ ብትሆንም ያለ ችሎታን በመጠቀም ቢያንስ ለራስ አንድ ሰዓት መስጠት ያስፈልጋል… የሚያስከብረው ሥራ ነውና” በማለት ለስኬት ሙያቸውን ከልብ መውደድ ቁልፍ ጉዳይ ነው ትላለች።

የወደፊት ዕቅዷ…
ሰናይት ከምትወደው ሰርከስ በተጨማሪ እራሷን በፊልም ኢንደስትሪ ውስጥ ማየት ትፈልጋለች። ይህንን ምኞቷን ዕውን ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ በለንደን ከተማ ሊት ኮሌጅ ትወና እና ‘ሞክአፕ’ እየተማረች ነው።
“ከሰርከስ በተጨማሪ ትወናን እወዳለሁ። ከኮንትሮሽን ጋር በተያያዘ ፊልም ውስጥ መግባት እፈልጋለሁ። እኔ ለዚህ ተስማሚ በሆነ ጥሩ አገር ውስጥ ስላለሁ ፍላጎቴን እያዳበርኩ ነው” ትላለች።
በዋና ዋና ዓለም አቀፍ መድረኮች ደምቃ የወጣችው ሰናይት አሰፋ በሰርከስ ጥበብ ለ13 ዓመታት ሠርታለች።
“የሕይወት ፈተናዎችን አልፌ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሴን የሚረዱት አሠልጣኞቼ እኔን እንደ ምሳሌ ሲገልጹኝ በማየት፣ ለሌሎች አርአያ በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። ስለዚህ ሴት ልጆችም መጠንከር አለባቸው” ትላለች።
ለዚህ ደግሞ ሰናይት የራሷን አስተዋጽኦ ለማበርከት ታስባለች “እግዚአብሔር ሃገራችንን ሰላም ካደረገልን፣ እኔ በሰርከስ ያገኘሁትን ዕድል እና ስኬት ሌሎች እንዲያገኙ ትግራይ ውስጥ የሰርከስ ትምህርት ቤት ከፍቼ ሴቶችን ለማስተማር ምኞት አለኝ።”