tank

ከ 5 ሰአት በፊት

እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቀጥሎ ጋዛ ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ባለፉት ሳምንታት ደግሞ የእርዳታ ሠራተኞች ላይ ሠራዊቷ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት ከወዳጆቿ ሳይቀር ከባድ ተቃውሞ ገጥሟታል።

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው ጥፋት ምክንያት በዘመናዊ መሳሪያዎችን በሽያጭ እና በድጋፍ ሲያስታጥቋት የነበሩት ምዕራባውያን አገራት የሚያቅርቡላትን ጦር መሳሪያ እንዲያቆሙ ጥሪ እየቀረበላቸው ነው።

እስራኤል የጦር መሳሪዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከቀዳሚ አገራት ተርታ ብትሰለፍም የአገሪቱ ጦር የተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ ቦምቦችን እና የሚሳኤሎችን ፍላጎቱን የሚያሟላቸው ከሌሎች አገራት በከፍተኛ መጠን በማስገባት።

ተንታኞች እንደሚሉት እስራኤል ከውጭ የሚገቡ ጦር መሳሪያዎችን በመጠቀም በቅርብ ጊዜ ታሪክ ከፍተኛ ውድመት የፈጠረች አገር ናት።

እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለችው ጦርነት ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ በቂ እርምጃ እየወሰደች ስላልሆነ ምዕራባውያን አጋሮቿ የጦር መሳሪያ አቅርቦታቸውን እንዲያቆሙ ግፊት እየተደረገባቸው ነው።

በቅርቡም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለእስራኤል የሚደረግ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እንዲቆም በ28 ድጋፍ፣ በ6 ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ታዕቅቦ ውሳኔ አሳልፏል።

ለእስራኤል ጦር መሳሪያ በማቅረብ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት አሜሪካ እና ጀርመን ግን ይህን የመንግሥታቱ ድርጅትን የውሳኔ ሃሳብ ተቃውመዋል።

እስራኤል ከሐማስ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ጀምሮ የጦሯ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም ሐማስ ግን ሆነ ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን ለጥቃት እንዲጋለጡ ያደርጋል ስትል ትከሳለች።

ኤፍ-35 የጦር ጄት
የምስሉ መግለጫ,በዘመናዊነት ተወዳዳሪ የሌላቸውን ኤፍ-35 የጦር ጄቶችን ከአሜሪካ አግኝታለች

አሜሪካ

አሜሪካ ከየትኛውም አገር በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለእስራኤል ሠራዊት በሽያጭ እና በድጋፍ የምታቀርብ አገር ነች።

እንደ ስቶኮልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ከሆነ እስራኤል ከ2019 እስከ 2023 ወደ አገሯ ከስገባቻቸው አጠቃላይ ጦር መሳሪያዎች 69 በመቶ የሚሆነው ከአሜሪካ የመጣ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ባለፉት 10 ዓመታት 3.8 ቢሊዮን ዶላር በየዓመቱ ወጪ በማድረግ የእስራኤል ጦር በቀጠናው ካሉ አገራት ጋር ተፎካካሪ ሆኖ እንዲቆይ ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች።

እስራኤል ይህን የገንዘብ ድጋፍ በመጠቀም 75 እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን ኤፍ-35 የጦር ጄቶችን ከአሜሪካ ያዘዘች ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 30ዎቹን ተረክባለች።

የአሜሪካ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወታደራዊ ድጋፍ የእስራኤልን የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓትንም ሲያጠናክር ቆይቷል።

የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎም አሜሪካ ለእስራኤል የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ የሚጨምርበትን ሁኔታ አሜሪካ እያጤነች እንደነበረ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረው ነበር።

ባለፈው መስከረም ወር ማብቂያ ላይ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አሜሪካ ለበርካታ ጊዜያት ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጓ ቢነገርም፣ ለሕዝብ ይፋ የሆነው ግን ሁለት ጊዜ የሰጠቻቸው ወታደራዊ ድጋፎች ብቻ ናቸው።

ለሕዝብ ይፋ የሆነው መረጃ አሜሪካ 106 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ 14 ሺህ የታንክ ጥይቶችን እና 155 ሚሊ ሜትር ተተኳሽ ጥይቶችን መሥራት የሚያስችል ግምቱ 147 ሚሊዮን ዶላር የሆነ ወታደራዊ ድጋፍ ማድጓ ነው።

አንዳንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለሕዝብ ይፋ ሳያደርግ እንደ ቦምብ፣ አነስተኛ ጦር መሳሪያዎች እና ምሽግ መከላከያዎችን የመሳሰሉ ወታደራዊ ድጋፎችን ለእስራኤል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዘግበዋል።

ለእስራኤል የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡ አገራት በመቶኛ

ጀርመን

ስቶኮልም ኢንተርናሽናል ፎረ ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት እአአ ከ2019 እስከ 2023 እስራኤል ወደ አገሯ ካስገባችው አጠቃላይ ጦር መሳሪያ 30 በመቶ የሚሆነውን ያገኘችው ከጀርመን መሆኑን ያመለክታል።

አውሮፓዊቷ አገር ጀርመን እየተካሄደ ያለው የጋዛ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ለእስራኤል ያደረገችው የመሳሪያ ሽያጭ መጠን ከ300 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ነው።

ከጦር መሳሪያ ሽያጭ በተጨማሪም ጀርመን ለእስራኤል ታደርግ የነበረው ወታደራዊ ድጋፍ ከመስከረም መጨረሻው የሐማስ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ በ10 እጥፍ ጨማሪን አሳይቷል።

የአየር መከላከያ መሳሪያ ግብዓቶች እና የግንኙነት መሳሪያዎች እስራኤል ከጀርመን ከምታስገባቸው መሳሪያዎች አብዛኛውን ቦታ ይይዛሉ።

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ በጦርነቱ ጅማሬ ወቅት እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት አላት በማለት ለቴል አቪቭ የማይቋረጥ አጋርነት እንዳላቸው ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም፤ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ግን የእስራኤል የጋዛ ወታደራዊ ዘመቻ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ነው።

እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ዘመቻ የደረሰ ውድመት
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ዘመቻ የደረሰ ውድመት

ጣሊያን

ከአሜሪካ እና ከጀርመን በመቀጠል ጣሊያን ለእስራኤል ሦስተኛዋ ጦር መሳሪያ አቅራቢ አገር ነች።

ጣሊያን ከአሜሪካ እና ከጀርመን ጋር ሲነጻጸር ለእስራኤል ሠራዊት የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ እና ሽያጭ በመጠን ሲለካ እዚህ ግባ የሚባይል ባይሆንም፤ ቴል አቪቭ ከሮም የምታገኘው ድጋፍ በሠራዊቷ ዘመቻ ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዳለው ይገለጻል።

ጣሊያ ወደ እስራኤል ከምትልካቸው ጦር መሳሪያዎች መካከል ሄሊኮፍተሮች እና ለባሕር ኃይሉሏ አገልግሎት የሚውሉ ተተኳሾች ናቸው።

ባለፈው ዓመት ጣሊያን 13.7 ሚሊዮን ዶላር በሆነ ወጪ ለእስራኤል ወታደራዊ ቁሶች ሸጣለች።

ጋዛ ውስጥ በምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ሰብዓዊ መብት እየጣሰች ትገኛለች ለምትባለው እስራኤል የጦር መሳሪያ ሽያጭ እየተደረገ መሆኑ የጣሊያን ፖለቲከኞችን አስቆጥቶ ነበር።

ነገር ግን የጣሊያን መከላከያ ሚንስትር ጦር መሳሪያዎቹ ለእስራኤል በሽያጭ የተሰጡት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ለማድረግ እንደማይውሉ በዝርዝር ከተለየ በኋላ ነው ብለዋል።

የመድፍ ተተኳሾች እና አንድ ወታደር
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ብቻ ሳይሆን ተተኳሾችን ሳይቀር ከአሜሪካ ታገኛለች

ሌሎች አገራት

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለእስራኤል የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ “በአነጻራዊነት አነስተኛ ነው።” እንደ ዩኬ መንግሥት አሃዝ ከሆነ እአአ 2022 ላይ ለእስራኤል በሽያጭ የተላለፈው ጦር መሳሪያ መጠን 42 ሚሊዮን ፓዎንድ ግምት አለው።

ዩኬ ከእአአ 2008 ጀምሮ ጦር መሳሪያዎችን ለእስራኤል ለመሸጥ የንግድ ስምምነት ከአገሪቱ ጋር ተፈራርማለች።

በዚህ ስምምነት እስራኤል አሜሪካ ሰራሽ ለሆኑ የጦር አውሮፕላኖች መለዋወጫዎችን ከዩኬ በሽያጭ ማግኘት ያስችላታል።

የዩኬ መንግሥት ይህን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንዲያቆም ከፍተኛ ጫና እየተደረገበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ እንዲቀጥል እስራኤል ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕጎችን እንድታከብር ጠይቀዋል።

ሌላው ለእስራኤል የወታደራዊ ጦር መሳሪያዎችን ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው የካናዳ መንግሥት ነው። እአአ 2022 ላይ እስራኤል 15 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሳሪያ ሽያጭ ከካናዳ ፈጽማለች።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ወራት በፊት የካናዳ መንግሥት ጦር መሳሪያዎቹ ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ የካናዳ ሕግን የማይጻረር መሆኑ እስኪረጋገጥ ድረስ የጦር መሳሪያ ሽያጩን አቁሚያለሁ ብሏል።

እስራኤል እራሷ የምታምርተው እና ጋዛ ላይ እየተጠቀመችው ያለው ድሮን
የምስሉ መግለጫ,እስራኤል እራሷ የምታምርተው እና ጋዛ ላይ እየተጠቀመችው ያለው ድሮን

የእስራኤል ጦር ኢንዱስትሪ

እስራኤል በአሜሪካ ድጋፍ የራሷን ጠንካራ የጦር ኢንዱስትሪ ገንብታለች።

እስራኤል ጦር መሳሪያዎችን ከውጭ አገራት እንደማስገባቷ፣ ለሌሎች አገራት ጦር መሳሪያዎችን ትሸጣለች።

ጦር መሳሪያ ለዓለም ገበያ በማቅረብም ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። እስራኤል ትኩረቷን በግዙፍ ጦር መሳሪያዎች ላይ ከማድረግ ይልቅ በቴክኖሎጂ የረቀቁ መሳሪዎችን ለገበያ በማቅረብ ከ2019 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት 12.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝታለች።

እስራኤል ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው መሳሪዎች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ሰው አልባ አውሮፕላኖች ናቸው።

ሚሳኤሎች፣ ሮኬቶች፣ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች፣ የራዳር እና ኤሌክትሮኒክ ጦርነት መካላከያ ሥርዓቶች እስራኤል ለገበያ የምታቀርባቸው የጦር መሳሪያ ውጤቶች ናቸው።

በእስራኤል የአሜሪካ መሳሪያ ማከማቻ

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ቢነሳ አልያ ደግሞ እስራኤል በአስቸኳይ ጦር መሳሪያ ቢያስፈልጋት በሚል እአአ 1984 ላይ እስራኤል ውስጥ የገነባችው ግዙፍ ጦር መሳሪያ ማከማቻ አላት።

አሜሪካ በዚህ ማከማቻ ምን ያክል እና ምን ዓይነት የጦር መሳሪያ እንዳከማቸች አይታቅም።

በቅርቡ ግን ፔንታገን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ 300 ሺህ ባለ 155 ሚሊ ሜትር ተተኳሾችን ወደዚሁ ማከማቻው ልኳል።