
April 7, 2024
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 16 ዓመታት 386 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የግብርና ምርቶችን ቢያገበያይም፣ በዋናነት ሲያገበያያው የነበረው የቡና ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ ሆኗል፡፡ በአምስት ዓመት የግብይት መጠኑ ከ24 ቢሊዮን ብር ወደ 10.7 ቢሊዮን ብር ወርዷል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያመለክተው በዓመት ከ326 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ማገበያየት ችሎ የነበረው ምርት ገበያ፣ በአሁኑ ወቅት ይህ መጠን ወደ 57 ሺሕ ቶን መውረዱን ያመላክታል፡፡
የምርት ገበያውን የተከታታይ ዓመታት የግብይት ክዋኔ የሚያመለክተው መረጃ፣ ቡና ግብይት በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የመጣው ከ2009 ዓ.ም. በኋላ ነው፡፡
ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰውም የቡና ግብይት ከምርት ገበያው ውጭ በተለያዩ የግብይት አማራጮች እንዲካሄድ መደረጉ ነው፡፡
ይህ ዕርምጃ በኢትዮጵያ የምርት ገበያ በኩል የሚካሄደውን የግብይት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱም፣ በምርት ገበያ ገቢ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል፡፡
ከገቢው መቀነስ በላይ ግን ከምርት ገበያው ውጪ የሚካሄደው ግብይት፣ ለሕገወጥ ተግባራት በር እየከፈተ መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ እየተነገረም ነው፡፡
በምርት ገበያው በኩል የሚገበያይ ቡና በመጠንም ሆነ በገንዘብ ደረጃ እያዘቀዘቀ መምጣት፣ እንዲሁም ከምርት ገበያው ውጭ የሚካሄደው የቡና ግብይት አሳሳቢ በመሆኑ፣ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለመንግሥት ጥያቄ እንዲቀርብ የሚያስገድድ ሆኗል፡፡
በቡና ግብይት ዙሪያ የታየውን ክፍተት በተመለከተ ጥያቄ ሪፖርቱ የቀረበላቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኝ ነገራ፣ በምርት ገበያው በኩል ግብይት የሚደረግበት የቡና ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን አረጋግጠዋል፡፡
ከምርት ገበያው ውጪ የሚካሄደው የቡና ግብይት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ከግምት በማስገባት፣ ጉዳዩን መንግሥት ዓይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ በማቅረብ እየተነጋገሩበት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
ሪፖርተር ያገኘው አኃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2011 በጀት ዓመት ምርት ገበያው 22.8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው 326,586 ቶን ቡና ማገበያየት ችሎ የነበረ መሆኑን ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. ግን ይህ የግብይት መጠን ቀንሶ በምርት ገበያው መገብየት የቻለው የቡና መጠን 155 ሺሕ ቶን ሊሆን ችሏል፡፡ ይህም በገንዘብ ሲተመን 20.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር ያመለክታል፡፡
በ2013 ዓ.ም. ደግሞ የግብይት መጠኑ በእጅጉ አሽቆልቁሎ በዓመቱ ውስጥ 63,267 ቶን ብቻ አገበያይቷል፡፡ ይህም በ2013 በጀት ዓመት የተገበየው ቡና 12.7 ቢሊዮን ብር ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የ2015 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙም ከምርት ገበያው ውጭ የሚደረግ የቡና ግብይት እየጨመረ በምርት ገበያው የሚካሄድ የቡና ግብይት ደግሞ እየቀነሰ ስለመምጣቱ የበለጠ ማሳያ ተደርጎ ታይቷል፡፡ በመረጃው መሠረት በ2015 የበጀት ዓመት በምርት ገበያው የተገበያየው የምርት መጠን 57,117 ቶን ሲሆን፣ ይህም 10.7 ቢሊዮን ብር ብቻ ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተጠናከረውን ተጨማሪ መረጃ በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዓምድ ሥር ይመልከቱ፡፡