ማኅበራዊ
በአሶሳ ከተማ በተፈጠረ የውኃ እጥረት ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ

የማነ ብርሃኑ

ቀን: April 7, 2024

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ከተማ በተፈጠረ የውኃ እጥረት ነዋሪዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ በአሶሳ ከተማ በተፈጠረ ከፍተኛ የውኃ ችግር፣ አንድ ጄሪካን ውኃ እስከ ሃያ ብር ለመግዛት ተገደዋል፡፡

የከተማዋ የውኃ ችግር ሥር የሰደደ ነው የሚሉት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ቀደም ሲል በሳምንትና በአሥራ አምስት ቀናት በፈረቃ የሚያገኙት ውኃ ከተቋረጠ ወራት ተቆጥረዋል ብለዋል፡፡  

– Advertisement –

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የጤና ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በውኃ እጥረት እየተፈተኑ እንደሚገኙ፣ ሕፃናትና እመጫት እናቶች ይበልጥ የችግሩ ሰለባ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

እኝሁ አስተያየት ሰጪ የችግሩን አሳሳቢነት ለከተማው የመንግሥት አካል በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ ጆሮ ሰጥቶ የሚያዳምጣቸውና መፍትሔ የሚሰጣቸው አካል አለመገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ውኃና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጀርሞሳ ተገኝ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአሶሳ የውኃ ፕሮጀክት ሲገነባ ከ50 እስከ 70 ሺሕ ለሚሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡

ሆኖም በአሁኑ ወቅት በአጎራባች ሱዳንና በኦሮሚያ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት እየተፈናቀሉ ወደ አሶሳ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ፣ እንዲሁም ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ የውኃ ፍላጎት እያደገ ስለሆነ ከአቅርቦቱ ጋር ሊጣጣም አልቻለም ብለዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በከተማዋ የሚታየውን ከፍተኛ የውኃ ችግር ለማቃለል ከውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተገኘ 36 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አራት ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች እየተቆፈሩ ነው፡፡

በአሶሳ ከተማ አቅራቢያ ‹‹አምባ አንድ›› በሚባል አካባቢ እየተቆፈሩ የሚገኙት  ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶች ሲጠናቀቁ፣ የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ያቃልላሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ ከውኃ ሥርጭት ጋር ተያይዞ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍም ቢሮው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ፣ በወጣቶች መዝናኛ፣ እንዲሁም በስታዲየም አካባቢዎች እያንዳንዳቸው 350 ሜትር ኪዩቢክ ውኃ መያዝ የሚችሉ ታንከሮች ግንባታ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝም አቶ ጀርሞሳ አክለው ተናግረዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ የውኃ ችግር ጉድጓድ በመቆፈር ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ‹‹ዳቡስ›› እና ‹‹ሆሃ›› በተባሉ ወንዞች ግድብ ለመገንባት የሚያስችል ጥናት ተካሂዶ ለውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር መላኩን፣ ግድብ ገንብቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውኃ ለማቅረብ ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ መጠየቁንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡