
ከ 9 ሰአት በፊት
ለምን ያህል ሰዓት በአውሮፕላን ተጉዘው ያውቃሉ?
ለ10 ሰዓት፣ ለ15 ሰዓት? በበረራ ውቅት ተኝተው ነበር ወይስ እንደነቁ?
ምናልባት መልስዎ ተኝተው እንደነበር ሊሆን ይችላል።
ረዥም ሰዓት ሳይተኙ መብረር ቀላል ሊሆን አይችልም።
አውሮፕላን አብራሪዎችስ ምን ያደርጋሉ?
ለምሳሌ በዓለማችን ረዥም ከሆኑ በረራዎች መካከል አንዱ ከኒው ዮርክ ወደ ሲንጋፖር የሚደረገው ነው።
ይህ በረራ 18.5 ሰዓታትን ይወስዳል። አንድ ቀን ሊሞላ ጥቂት ሰዓታት ማለት ነው።
ከሰሞኑ ፓይለቶች ሳያቋርጡ ለረዥም ሰዓት ማብረራቸው እና የሚሰማቸው ድካም መነገጋሪያ ሆኗል።
ለዚህም መነሻ የሆነው በአንድ የኢንዶኔዢያ በረራ ላይ ዋና እና ረዳት አብራሪዎች ተኝተው መገኘታቸው ዜና መሆኑን ተከትሎ ነው። ምንም እንኳን የኢንዶኔዢያው በረራ መነሻ ቢሆንም ለበርካታ አስርት ዓመታት መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ነው። በተለይም በወታደራዊ ተቋማት ዘንድ።
እናም አስገራሚ መፍትሄ አግኝተዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንድ የናዚ አብራሪ በብሪታኒያ ኃይል ተመትቶ ወደቀ።
በፓይለቱ ኪሱም ውስጥ ሜታአምፌታሚን የተሰኙ አበረታች እንክብሎች አገኙ። በአሁኑ ወቅት በዋናነት ለመዝናኛነት የሚውለው ይህ አበረታች መድኃኒት ትኩረት የሚያንሳቸው ሰዎችም ይገለገሉበታል።
በጀርመን አየር ኃይል (ሉፍትዋፍ) በረዥም በረራ ለሚደክሙ ፓይለቶች አማራጭ መድኃኒት ነበር።
መድኃኒቱን በነጻነት መውሰድ ስለሚቻል “የፓይለቶች ጨው” የሚል ስያሜንም አግኝቶ ነበር።
ብሪታኒያንን ያካተተው ኅብረቱ ኃይሎች የጀርመን የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች አበረታች መድኃኒት ይወስዳሉ ብለው ቢጠራጠሩም በእርግጠኝነት ግን አያውቁም ነበር።
የተገኘው አበረታች መድኃኒት ላይም ምርመራ ተደርጎ፣ ብዙም ሳይቆይ ብሪታኒያውያን ይህንኑ መድኃኒት በራሳቸው ማምረት ጀመሩ።
- በረራ ላይ ሳሉ የተኙ ሁለት የኢንዶኔዢያ አየር መንገድ አብራሪዎች ምርመራ ተከፈተባቸው11 መጋቢት 2024
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ አብራሪዎች ‘እንቅልፍ ወስዷቸው’ መዳረሻውን አልፈው ነበር ተባለ19 ነሐሴ 2022
- ከአፍሪካ አየር መንገዶች በአውሮፕላን ብዛት ቀዳሚዎቹ የትኞቹ ናቸው?8 መጋቢት 2024
ይህንንም ተከትሎ አበረታች መድኃኒቱ በሰፊው ተሰራጨ። በአውሮፓ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን በምሽት ለማድረግ ይህ መድኃኒት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
ይሄ ገና በመጀመሪያው ወቅት ነበር። ከሜታአምፌታሚን ጋር ተዛማጅነት ያለው ዴክስትሮሜታአፌታሚን የተሰኘው አበረታች መድኃኒት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1990-91 በነበረው የባሕረ ሰላጤው (የኢራቅ እና ኩዌት) ጦርነት ላይ ገነነ።
በኩዌት የነበሩትን የኢራቅን ጦር በቦምብ ለማጥቃት የተሳተፉት አብዛኞቹ ተዋጊ አብራሪዎች ይህንን አበረታች መድኃኒት ይወስዱ ነበር።
ይህ መድኃኒት አሁንም ቢሆን በአሜሪካ ወታደራዊ አብራሪዎች ጥቅም ላይ ይውላል። ረዘም ያሉ ሰዓታትን ወይም ቀናትን የሚወስዱ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ አብራሪዎች ድካም ተሰምቷቸው ደኅንነታቸው አደጋ ላይ እንዳይወድቅ በሚል ነው ይህ መድኃኒት አገልግሎት ላይ የሚውለው።
ነገር ግን መድኃኒቱን እንዲሁ ዝም ብሎ መውሰድ ቀላል አይደለም። አምፌታሚንስ ተብለው የሚጠሩት እነዚህ መድኃኒቶች ከፍተኛ ሱስ ውስጥ ሊያስገቡ ይችላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1940ዎቹ እንኳን ያላግባብ የሚጠቀሙባቸው በርካቶች ነበሩ። እናም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ወታደራዊ ተቋማት ሌላ አማራጭ ፍለጋ ላይ ናቸው።
ተመራጭ ያደረገውም ሞዳፊኒ የተባለው አበረታች መድኃኒት ነው።
ይህ አበረታች መድኃኒት ናርኮሌፕሲ የተሰኘ እንቅልፍን የመቆጣጠር ችሎታን የሚጎዳው ስር የሰደደ የነርቭ በሽታን እንዲሁም በቀን ላይ ከመጠን ያለፈ እንቅልፍንም ለማከምም አገልግሎት የዋለው በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ነው።
አበረታች መድኃኒቱ በበርካቶች ለመታወቅ ብዙ ጊዜም አልፈጀበትም።
መድኃኒቱ ሰዎች እንዳይተኙ ለመከላከል ከመርዳት በተጨማሪ ሌሎች ጥቅሞችም አሉት። መድኃኒቱ ማስታወስን ለማሻሻል፣ አጠቃላይ ግንዛቤን ለመጨመር እንዲሁም በተለይም ከፍተኛ ድካም በሚሰማበት ወቅት ንቁነትን ለማሳደግ ይጠቅማል።
ሞዳፊኒ ይህንን ያህል ጥቅም ቢኖረውም የራሱ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት፤ ከነዚህም መካከል ላብ፣ የከባድ የራስ ህመም እንዲሁም የሌሉ ነገሮችን ማየትና መስማት (ሃሉሲኔሽን) ይገኙበታል።
እንዲህ አይነት ጉድለቶች ቢኖሩበትም መንቃት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ዋነኛ መድኃኒት ነው።
ቀደም ብሎ በተደረገ አንድ ጥናት መድኃኒቱ ሰዎች እስከ 64 ሰዓታት በንቃት እንዲሠሩ ያደረጋቸው ሲሆን፣ ይህም 20 ኩባያ ቡና ከመጠጣት ጋር ተነጻጽሯል። እንዴት ነው የሚሰራው? ለምንስ ጥቅም ላይ ይውላል?

የአየር ኃይል አባላት የሚወስዷቸው አበረታች መድኃኒቶች
በተዋጊ አብራሪዎች ዘንድ ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች አሉ እነርሱም ‘ጎ ፒልስ’ እና ‘ኖ ጎ ፒልስ’ ይሰኛሉ።
ጎ ፒልስ የሚሰኙት አነቃቂዎች ሲሆኑ፣ የማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት እንቅስቃሴን ይጨምራሉ።
ለዚያም ነው አምፌታሚን የሚባሉት አበረታች መድኃኒቶች በተለምዶ ‘ስፒድ’ (ፍጥነት) የሚል ስያሜ የተሰጣቸው።
‘ኖ ጎ ፒልስ’ የሚባሉት ደግሞ በአዕምሮ እና በሌላኛው የሰውነታችን ክፍል መልዕክት የሚተላለፍበትን ፍጥነት የሚቀንሱ አደንዛዥ (ዲፕሬሳንት) ንጥረ ነገሮች ናቸው።
አንዳንድ ጊዜ ለከፍተኛ ንቃተ ህሊና እንቅልፍ መተኛት ወሳኝ በሚሆንበት ጊዜ ፓይለቶች እነዚህን መድኃኒቶች ይወስዳሉ።
በዚህም መንገድ ሰውነታቸው እንዲተባበራቸው እና እንቅልፍ እንዲወስዳቸው ያደርጋሉ።
ሞዳፊኒል የሲንጋፖር፣ የሕንድ፣ የፈረንሳይ፣ የኔዘርላንድስ እና የአሜሪካ አየር ኃይሎች ለመጠቀም ፍቃድ አግኝተው አባሎቻቸው ይወስዱታል።
በአውሮፓውያኑ 2001 የአፍጋኒስታን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የመከላከያ ሚኒስቴር ጠቀም ያለ የሞዳፊኒል ክምችት መግዛቱን የዩኬው ዘ ጋርዲያን ባቀረበው የምርመራ ዘገባ አጋልጧል።
ሌላኛው የመከላከያ ሚኒስቴሩ የሞዳፊኒል ትዕዛዝ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2002፣ ከኢራቅ ወረራ በፊት ነበር። በዚህ ወቅት የመከላከያ ጥናት እና ምርምር ኤጀንሲ በመድኃኒቶቹ ላይ ሙከራዎችን ቢያደርግም በአየር ኃይል አብራሪዎች ጥቅም ላይ አልዋሉም ነበር ተብሏል።
ሆኖም እውነታው ባለፉት አስር ዓመታት አበረታች መድኃኒቶችን የወሰዱ የአየር ኃይል አባላት በመቶዎች በሚቆጠሩ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ ተሳትፈዋል።
ተዋጊ አብራሪዎች አካባቢያቸውን አጥንተው ስጋት የሚሉትን ዒላማ ለማድረግም ሆነ ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ለመወሰን የሚኖራቸው ጥቂት ሰኮንዶች ብቻ ናቸው።
ድካም ተሰማቸው ማለት ደግሞ በቀላሉ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።
በከባድ ጦርነቶች ወይም ወታደራዊ ተልዕኮዎች ጊዜ ብቻ አይደለም አብራሪዎች ከእንቅልፍ እጦት ጋር የሚታገሉት። ረጃጅም እና አሰልቺ በረራዎች ለአብራሪዎች ፈተና ናቸው።
“ዝም ብለህ ቁጭ ብለህ የምትታዘብ ከሆነ ወታደራዊ ወይም የውጊያ ተልዕኮ ከምትሠራበት ጊዜ በበለጠ የአምስት ሰዓት ርዝመት ይሰማሃል” ይላሉ በኔዘርላንድስ የመከላከያ ሚኒስቴር የኤሮስፔስ የህክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ሌተናል ኮሎኔል ያራ ዊንጌላር ጃግት።

ፈጣን በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሰውነት የራሱን አበረታች ንጥረ ነገር (አድሬናሊን) ያመነጫል፤ ይህም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ንቃትን በመጨመር የድካም ስሜትን ይቀንሳል።
በሌላ በኩል ብዙም እንቅስቃሴ የሌላቸው ተልዕኮዎች ወደ መሰላቸት ሊያመሩ ስለሚችሉ የድካም ስሜትን ሊያመጡ ይችላሉ።
በዚህ ዓመት ኤ320 ኤርባስ አውሮፕላን 153 መንገደኞች እና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች አሳፍሮ ከኢንዶኔዢያዋ መዲና ጃካርታ ሱላዌሲ ከተማ መብረር ጀመረ።
ዋናው አብራሪ ረዳት አብራሪውን ትንሽ ልተኛ ስለሆነ ኃላፊነቱን ውሰድ አለው። ረዳት አብራሪውም ተስማማ። ነገር ግን የሆነው ይህ አይደለም።
የኢንዶኔዢያ ብሔራዊ የትራንስፖርት ኮሚቴ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱ አውሮፕላኑ ለ28 ደቂቃ ያህል ፓይለት አልባ ሆኖ ቆይቷል ብሏል። ሁለቱም አብራሪዎች በአንድ ላይ ተኝተው ነበር።
ክስተቱ አገራዊ ጥያቄዎችን ያስከተለ እንዲሁም በንግድ በረራዎች ላይ ያለውን የፓይለቶች ከፍተኛ የድካም ችግር አጉልቶ ያሳየ ሆኗል።
“ከጥቂት ዓመታት በፊት በሙከራ ላይ ያሉ ወታደራዊ ፓይለቶቻች አዲስ ተልዕኮ ሲያጠናቀቁ ድካም መከላከያ የተባለው ቡና በቂ አይደለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር” ሌተናል ኮሎኔል ያራ ዊንጌላር ጃግት ብለዋል።
አክለውም “በበራው ወቅት ነቅተው እንዲቆዩ የሚረዳቸው ሌላ ነገር እየፈለጉ ነበር” ይላሉ።
አማራጩ ሞዳፊኒል እንደሆነ ለማወቅትም ሌተናል ኮሎኔሉ እና ባልደረቦቻቸው ሙከራ አካሂደዋል።
በሮያል ኔዘርላንድስ አየር ኃይል አባላት የሆኑ በጎ ፈቃደኞች ለ17 ሰዓታት ያህል እንዳይተኙ ተደረጉ።
ከዚያም ሞዳፊኒል፣ ካፌይን (ቡና) ወይም ምንም ውጤት የማያመጣ ነገር (ፕላሴቦ) እንዲወስዱ ተደረገ። ንቃታቸው እና የእንቅልፍ ሁኔታቸው ሲገመገምም ካፌይን እና ሞዳፊኒል ውጤታማ መሆኑ ቢደረስበትም ሞዳፊኒል ረዘም ላለ ጊዜ በመቆየት የበለጠ ውጤታማ መሆኑን ሙከራው አሳይቷል።
ሌሊቱን ሙሉ ሳይተኙ ቀርተው ሞዳፊኒል ከወሰዱ በኋላ ሳይተኙ ሌላ ቀንም እንደገና መሥራት እንደሚችሉም ተሰምቷቸው እንደነበርም ይገልጻሉ።
“ሞዳፊኒል በመውሰዳቸው ምክንያት የድካም ስሜታቸው ቀንሶ የበለጠ ንቁ እንደሆነ ተሰምቷቸዋል” ይላሉ ሌተናል ኮሎኔሏ።
በወታደራዊ በረራዎች አውድ ውስጥ በእንቅልፍ እጦት ምክንያት የሚሰቃዩት አብራሪዎች ብቻ አይደሉም። በወታደራዊ ተልዕኮዎች ላይ በሄሊኮፕተሮች ላይ ተቀምጦ አነጣጥሮ መተኮስ ሥራቸው የሆኑ (ዶር ገነር) እንዲሁም አስፈላጊ መሳሪያዎችን የሚጭኑ እና የሚያወርዱም (ሎድ ማስተሮች) ያለ እንቅልፍ እና መድከም ሥራቸውን ማከናወን ብቻ አለባቸው።
ወታደራዊ አውሮፕላኖች ከመሬት ላይ ተነስተው ተልዕኳቸውን እስኪያጠናቅቁ ድረስ የሚያግዟቸው የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችም እንዲሁ በንቃት መከታተል አለባቸው።
ፈታኙ አበረታች መድኃኒት የመውሰድ ውሳኔ
ለወታደራዊ አብራሪዎች እና ሠራተኞች እንደ ሞዳፊኒል ያሉ አበረታች መድኃኒቶችን መስጠት በቀላሉ አይታይም።
ከአበረታች መድኃኒቶቹ ጋር የተያያዙ ከባድ የሥነ ምግባር እና የሕግ አንድምታዎች አሉ።
አንድ የወታደራዊ በረራ ሠራተኛ ለተልዕኮው መሳካት አስፈላጊ ሆኖ የተገኘውን አበረታች መድኃኒት ለመውሰድ ፈቃደኛ ካልሆነ ምን ይደረጋል? የሚለው አንደኛ ጥያቄ ነው።
ለዚህ የካናዳ የአየር ኃይል ጥሩ ማሳያ ነው። በካናዳ አንድን ሰው መድኃኒት እንዲወስድ ማስገደድ ሕጋዊ ባይሆንም፣ ነገር ግን ወታደራዊ ሠራተኞች የተሰጣቸውን ተልዕኮም ሆነ ተግባር በማንኛውም ጊዜ ቀን ከሌት ሠርተው በጥሩ ሁኔታ የማሳካት ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው።
ስለዚህ እነዚህ የአየር ኃይል ሠራተኞች ሞዳፊሊን መውሰድ ካልፈለጉ አሻፈረኝ ማለት ቢችሉም ነገር ግን በእንቅልፍ ወይም በድካም ምክንያት ተልዕኳቸው ላይ ምንም ክፍተት ሊታይ አይገባም።
ተልዕኳቸውን በአግባቡ ማጠናቀቅ አለባቸው።
ከዚህም በተጨማሪም ለእነዚህ አብራሪዎች አበረታች መድኃኒቶቹን ያለመውሰድ ጉዳቱ ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም ድንገት ደክሟቸው እንቅልፍ ካሸለባቸው ሲቪሎችንም ጨምሮ ሕይወት ሊቀጠፍ ይችላሉ።
እንዲሁም ከባድ የሚባሉ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ከማደናቀፋቸው በተጨማሪ በአስር ሚሊዮኖች የወጣበት አውሮፕላንም ጉዳት ሊደርስበት ይችላል።

“ለእኛ [በሮያል ኔዘርላንድስ አየር ኃይል] አንድ ሰው ሞዳፊሊን እንዲወስድ አለማስገደዳችን መሠረታዊ ነገር ነው” ይላሉ ዊንጌላር ጃግር።
“እነዚህን መድኃኒቶች አለመውሰድ ከድካማቸው ጋር ተቃራኒ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ድካማቸው ሙሉ በሙሉ አይጠፋም። ስለዚህ ድካማቸውን ለማስቀረት የሥራ ወቅትን ማጤን ጨምሮ ሌሎች አጽንኦት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ” ይላሉ።
ዊንግላር ጃግት ለምሳሌ ሁሉም በምሽት የሚደረጉ በረራዎች እና ተልዕኮዎች ምን ያህል መሠረታዊ ናቸው የሚለውን መጠየቅ እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ።
አንዳንዶቹን የምሽት ወታደራዊ ተልዕኮዎችን በጭራሽ ማስቀረት ባይቻልም ሌሎቹን ግን መገምገም እንደሚገባ ነው የሚናገሩት።
ሞዳፊኒል ፍጹም የሚባል አይደለም፤ ልክ እንደ ሁሉም መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት። እነዚህም አዕምሯዊ እንዲሁም አካላዊ ሊሆኑ ይችላሉ።
በርካታ ጥናቶች እንዳረጋገጡት ይህ አበረታች መድኃኒት ሰዎች በውሳኔያቸው ከመጠን በላይ እንዲተማመኑ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ይህ ደግሞ በከፍተኛ ፍጥነት 1 ሺህ 915 ኪሎሜትር በሰዓት እያበረሩ ያሉ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎችን በቀላሉ ለሞት ሊዳርጋቸው ይችላል።
ናዚዎችም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለጦር አውሮፕላን አብራሪዎቻቸው አበረታች መድኃኒት ሲሰጡ ተመሳሳይ ችግር አጋጥሟቸው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1940 የፀደይ እና የበጋ ወራቶች ብቻ 35 ሚሊዮን ሜታአምፌታሚን እንክብሎችን ለወታደራዊ ሠራተኞቻቸው አከፋፍለው ነበር።
ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ይህንን አበረታች መድኃኒት የወሰዱ የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች ወታደራዊ ተልዕኳቸውን በተሳካ ሁኔታ እየተወጣን ነው ብለው ቢያምኑም እውነታው ግን ከዚህ የራቀ ነበር።
ውሎ አድሮም ባለሥልጣናቱ ፐርቨቲን በሚል ስያሜ የሚሸጡት እነዚህ መድኃኒቶች አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አደረባቸው።
ልክ እንደ አምፍታሚንስ አበረታች መድኃኒቶች ያህል ጠንካራ ባይሆንም የሞዳፊኒል እንክብሎችም ሱስ ሊያስይዙ ይችላሉ።
እነዚህ መድኃኒቶች ከአየር ኃይል አብራሪዎች በተጨማሪም በአውሮፓውያኑ 2000ዎቹም ሙሉ ሌሊቱን በትጋት ለማጥናት በሚፈልጉ ተማሪዎች እንዲሁም የጊዜ ገደብ የተቀመጠባቸው ሠራተኞች ታዋቂ ሆኗል።
የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎችስ?
ስለ ጦር አውሮፕላን አብራሪዎች አበረታች መድኃኒት መጠቀም ስናወራ የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎችስ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች የሥራ ፈረቃ ርዝማኔያቸው ከወታደራዊ አብራሪዎች የበለጠ ቁጥጥር ይደረግበታል።
ሆኖም ከፍተኛ ድካምን ተቋቁመው በዓመት 1 ሺህ ሰዓታት በደመና ላይ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ያሉ 6 ሺህ 900 አብራሪዎችን ባሳተፈ አንድ ጥናት መሠረት 72.9 በመቶዎቹ የሚሆኑ ፈረቃቸውን ከጨረሱ በኋላም ከድካማቸው ለማገገም በቂ እረፍት እንደሌላቸው ይሰማቸዋል።
ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ፓይለቶች ደግሞ በሥራ ላይ ሆነው እንቅልፍ ሸለብ አድርጓቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በሌተናል ኮሎኔሏ አስተያየት ምንም እንኳን የሞዳፊኒል አበረታች መድኃኒቶች ለጦር አውሮፕላን አብራሪዎች የሚሰጠው ጥቅም በንግድ አቪዬሽን ላይም ተግባራዊ ሊሆን ቢችልም ይህ መደረግ የለበትም ሲሉ ይመክራሉ።
“የንግድ አውሮፕላኖች ላይ ስንመጣ ከአብራሪዎች እና ከመንገደኛው ኅብረተሰብ እየጠየቅን ያለው ምንድን ነው? የሚለውን ማወቅ አለብን።
“አብራሪዎች ሌሊቱን ሙሉ ተጉዘው እንዲወስዱን ነው የምንፈልገው? ወይስ አብራሪዎችም ሰዎች መሆናቸውን እና የራሳቸው ውስንነት እንዳላቸው መቀበል? ሁሉም ሰው እንቅልፍ እንደሚያስፈልገው እነሱም እንዲሁ እረፍት ያስፈልጋቸዋል የሚሉ ነገሮችን ልናጤን ይገባል” ይላሉ።
ዊንግላር ጃግት ሞዳፊኒል አበረታች መድኃኒቶች ከፓይለቶች ይልቅ ረጅም ሰዓት ለሚሰሩ እንደ ድንገተኛ እንክብካቤ ወይም የእሳት አደጋ ሠራተኞች ላሉ ሌሎች ሙያዎች ጠቀሜታ ሊኖረው ይችላል ይላሉ።
“በእነዚህ ሙያዎች ላይ ሠራተኞች ድካም እየተሰማቸው ቢሆን ምንም ስህተት የሌለበት ፍጹም የሆነ ተግባር ማከናወን ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ ያስረዳሉ።
አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሌሊቱን ሙሉ የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ዶክተሮች ተግባራቸውን በተሻለ ሁኔታ ማከናወናቸውን አሳይቷል።
ሞዳፊሊን አበረታች መድኃኒቶችን የወሰዱ እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች በዕቅድ ተግባሮቻቸውን በማከናወን፣ በማስታወስ ችሎታቸው፣ ችግሮችን በመፍታት ረገድ እንዲሁም በጥንቃቄ በመወሰን የበለጠ ውጤታማ ነበሩ ተብሏል።
ነገር ግን እንደ ወታደራዊ አብራሪዎች የህክምና ባለሙያዎችም እነዚህን አበረታች መድኃኒቶች እንዲጠቀሙ ጫና ሊደረግባቸው ይችላል የሚሉ የሥነ ምግባር ጥያቄዎችም ይነሳሉ።