ተማሪዎች በፈተና ላይ
የምስሉ መግለጫ,ተማሪዎች በፈተና ላይ

9 ሚያዚያ 2024

የዓለም ባንክ በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በሚከሰት የሙቀት መጨመር ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ውጤት ምን ያህል ተጽዕኖ ደርሶበታል በሚል ጥናት አጥንቶ በቅርቡ ይፋ አድርጓል።

በዚህ ጥናቱም በትምህርት ዓመቱ በተለይ ደግሞ በፈተና ወቅት ለከፍተኛ ሙቀት ተጋላጭ የሆኑ ተማሪዎች ከሌሎች በተለየ ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

ዓለም ባንክ ለዚህ ጥናቱ ከአውሮፓውያኑ ከ2003 እስከ 2019 ድረስ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ 2.47 ሚሊዮን ተማሪዎች ውጤትን ለዚህ ጥናት ግብዓትነት መጠቀሙን ገልጿል።

በዚህ ጥናቱም ከፍተኛ የሙቀት መጠን የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ ፈተና ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው መረዳታቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምርምር ቡድኑ አባል ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተነሳ የሙቀት መጨመርን ተከትሎ ከሰሃራ በታች የሚገኙ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በክፍል ውስጥ ሙቀትን ለመቀነስ የሚረዱ ቴክኖሎጂዎች የሏቸውም ሲሉ ያብራራል።

የዓለም ባንክ በዚህ ጥናቱ የሙቀት መጨመሩ በትምህርት ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ ለመዳሰስ ዓመቱን ሙሉ የተመዘገበውን የሙቀት መጠን ተመልክቷል።

ተማሪዎችም ውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የታየው ፈተና በወሰዱበት ወቅት በነበረው የሙቀት መጠን የተነሳ ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት ዓመቱ በሙሉ በነበረው ሙቀት የተነሳ ጭምር መሆኑ ተመልክቷል።

በዓለም ባንክ ጥናት በሙቀት መጨመር ምክንያት ከፍተኛ የውጤት መቀነስ የተመዘገበባቸው ደጋማ የሆኑ አካባቢዎች መሆናቸውን ይጠቁማል።

ቢቢሲ ያናገራቸው በዓለም ባንክ የምርምር እና ጥናት ቡድኑ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ክብሮም ታፈረ ሲያስረዱም “በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎች የሙቀት መጠኑን ተለማምደውታል” ይላሉ።

በሙቀት መጨምር ምክንያት ውጤታቸው ከቀነሱ ተማሪዎች መካከል ደግሞ “ወንዶች የበለጠ ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸውን እና ሴቶች የበለጠ የሙቀት መጨመርን ተቋቁመው መገኘታቸውን” ይጠቁማሉ።

የዓለም ባንክ የጥናት እና ምርምር ቡድን አባላት እኤአ ከ2003 እስከ 2019 ድረስ ያለውን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና ውጤት በመሰብሰብ የሙቀት መጨመር የተማሪዎች ውጤት ላይ ያመጣውን ተጽዕኖ ለማየት መሞከሩን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ጥናቱ ባካተተው ዓመት ውስጥ የታየውን የሙቀት መጠን በመሰብሰብም በጥናታቸው ውስጥ ማየታቸውን ይናገራሉ።

አቶ ክብሮም “ለትምህርት ከ18 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እስከ 21 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ድረስ ያለው የሙቀት መጠን ተስማሚ ነው ተብሎ ይመደባል” ይላሉ።

ነገር ግን በኢትዮጵያ በትምህርት ዓመቱ ከፍተኛ የሙቀት መጠን በተመዘገበ ወቅት ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ መከታተል ላይ አሉታዊ ተዕዕኖ አምጥቶ ታይቷል።

አቶ ክብሮም በትምህርት ዓመቱ “አስር ተጨማሪ ሞቃታማ ቀናት፣ ከ33 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በተመዘገበበት ወቅት በብሔራዊ መልቀቅያ ፈተና ላይ ዝቅተኛ ውጤት ተመዝግቦ ታይቷል” ይላሉ።

ተማሪዎች ሙቀቱ ከፍተኛ በሆነባቸው ዓመታት ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል አይችሉም የሚሉት አቶ ክብሮም፣ እነዚህ ተማሪዎች ፈተና ሲቀመጡ ደካማ ውጤት ያስግባሉ ሲሉ ስለ ጥናታቸው ያብራራሉ።

ወደፊት የዓለም ሙቀት መጨመሩ ስለማይቀር የተማሪዎች ውጤት ላይ ያለው ተጽዕኖ ታይቶ መንግሥት ምን ማደረግ ይኖርበታል የሚለውን የፖሊሲ አማራጭ ለመጠቆም ያለመ ጥናት መሆኑን ባለሙያው አክለዋል።

አቶ ክብሮም የሙቀት መጨመር ተማሪዎች ውጤት መቀነስ ላይ ያለው ተጽዕኖ “አነስተኛ ነው፣ 3 በመቶ ያህል” በማለት ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን የታየው ውጤት መቀነስ ላይ የሙቀት መጨመር የሚኖረው አስተዋጽኦ “እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ” ጨምረው አስረድተዋል።