
ከ 3 ሰአት በፊት
የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጀርመን ለእስራኤል የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲያስቆማት ኒካራጓ ጠየቀች።
ጀርመን የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋትን ለመከላከል የተደረገውን ስምምነት በመጣስ መሳሪያ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ በመሸጥ እንዲሁም ለተመድ የእርዳታ ኤጀንሲ ድጋፍ በመከልከልም ነው የተከሰሰችው።
ክሱን ውድቅ ያደረገችው ጀርመን መከላከያዋን ለአለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) ማክሰኞ ታቀርባለች።
ባለፈው ዓመት 30 በመቶ የሚሆነው የእስራኤል የጦር መሳሪያ ከጀርመን የተሸመተ ሲሆን በአጠቃላይም 326 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትም ተገልጿል።
እስራኤል ባለፈው ዓመት ከጀርመን የገዛችው የ326.5 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ሽያጭም ከአውሮፓውያኑ 2022 ጋር ሲወዳደር በአስር እጥፍ ጭማሬም አሳይቷል ስትል ኒካራጓ ከሳለች።
በዚህም እስራኤል እየፈጸመች ባሉ የጦር ወንጀሎችም ጀርመንን ተባባሪ ያደርጋታል ብላለች።
መስከረም መጨረሻ ላይ በተፈጸመው ጥቃት አንዳንድ የኤጀንንሲው ሰራተኞች ተሳታፊ ነበሩ በሚል ውንጀላም ለተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ኤጀንሲ የገንዘብ ድጋፍ ካቋረጡ ምዕራባውያን አገራትም አንዷ ጀርመን ናት።
- እስራኤልን የጦር መሳሪያ የሚያስታጥቋት አገራት እነማን ናቸው?8 ሚያዚያ 2024
- በጋዛ ሰራተኞቻቸው የተገደሉባቸው የረድዔት ኃላፊ እስራኤል መኪኖቻቸውን ኢላማ እንዳደረገች ተናገሩ4 ሚያዚያ 2024
- የጋዛ ረሃብ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠር እንደሚችል ተመድ ገለጸ28 መጋቢት 2024
ኒካራጓ ለአይሲጄ ያቀረበችው ክስም የተመድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (አይሲጄ) ጀርመን ለእስራኤል የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ እንዲያስቆማት እና አሁንም በጋዛ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ጥቂት አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት አንዱ ለሆነውም የተመዱ ኤጀንሲ የምታደርገውንም ድጋፍ እንደገና እንድትጀምር የሚጠይቅ ነው።
እስራኤል ከዚህ ቀደምም በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በደቡብ አፍሪካ ክስ የተመሰረባት ሲሆን በሄግ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉ የአይሲጄ ዳኞች እስራኤል የዘር ማጥፋት ድርጊትን ለማስወገድ “የሚቻለውን ሁሉ እንድታደርግ” ውሳኔ አስተላልፈዋል።
ፍርድ ቤቱ ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ ከእስራኤል የወሰዳቸውን ታጋቾችም በሙሉ በአስቸኳይ እንዲፈታም አዟል።
እስራኤል በጋዛ ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው የሚለውን ክስ የማትቀበለው ሲሆን ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ትናገራለች።
እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የማያባራ ጥቃት ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። ከተገደሉት ውስጥ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውን በሐማስ ስር ካለው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።
እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት የጋዛ ሰርጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በከፍተኛ የምግብ እጦት እየተሰቃዩ እንደሆነ አለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶች ይናገራሉ።