
ከ 3 ሰአት በፊት
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ “የተገባልን ቃል አልተፈጸመም” ያሉ ታጣቂዎች የወረዳውን አስተዳዳር ህንጻ በመቆጣጠር የመንግሥት ሠራተኞችን ለሰዓታት አግተው እንደነበር የዐይን እማኞች እና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ይህን ክስተት ተከትሎ በዛሬው ዕለት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደተዘጉ እና ትምህርትም እንደተቋረጠ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በክልሉ መንግሥት እና በትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ በነበረው የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ አንጻራዊ ሰላም በሰፈነበት መተከል ዞን ውስጥ በምትገኘው ድባጤ ወረዳ፤ የቀድሞ ታጣቂዎች እገታ የፈጸሙት ትላንት ሰኞ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም. ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የመንግሥት ሠራተኞች እና ነዋሪዎች እንደሚገልጹት እገታው የተፈጸመው በድባጤ ከተማ ውስጥ በሚገኘው እና የወረዳው አስተዳደር መሥሪያ ቤቶችን በያዘው ባለ ሦስት ወለል ህንጻ ውስጥ ነው።
የወረዳው አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊዎችን ጨምሮ 21 የሴክተር መሥሪያ ቤቶችን በያዘው በዚህ ህንጻ፤ ቢያንስ 800 የአስተዳደሩ ሠራተኞች የሚገኙበት እንደሆነ ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እገታው ሲፈጸም በሥራ ላይ የነበሩ ሁለት የዐይን እማኞች እንደገለጹት፤ ታጣቂዎቹ ህንጻው ወደ የሚገኝበት ግቢ የገቡት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ ላይ ነው።
እገታውን የፈጸሙት የሰላም ስምምነቱን መፈረም ተከትሎ ከትጥቅ ትግል የተመለሱ የጉሕዴን ታጣቂዎች መሆናቸውን የዐይን እማኞች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በሰዓቱ በሥራ ላይ የነበሩት ስማቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ የትምህርት ባለሙያ፤ “የመንግሥት ሠራተኛው በሥራ ላይ እያለ [የታጣቂዎቹ መሪ] ታጣቂዎቹን አሰልፎ ይዞ መጣ። ታጣቂዎቹን በህንጻው ዙሪያ ቦታ ቦታ አስያዛቸው” በማለት ታጣቂዎቹ ቦንብ እና ክላሽ ታጥቀው ወደ መንግሥት መሥሪያ ቤት መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የመንግሥት ሠራተኛም ታጣቂዎቹ ህንጻውን ሲከቡ ቦንብ እና ጠመንጃ የታጠቁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
- በፍኖተ ሰላም ከተማ በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ገበያ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ 27 ሰዎች ተጎዱ8 ሚያዚያ 2024
- በባሕር ዳር ከተማ እሁድ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት “አምስት ሙስሊሞች” መገደላቸው ተገለጸከ 7 ሰአት በፊት
- ሕይወት ከመርዓዊ ግድያ በኋላ4 ሚያዚያ 2024
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዐይን እማኞች የታጣቂዎቹ ብዛት ከ30 ያላነሰ እንደሆነ ተናግረዋል። ሁለቱ ዐይን እማኞች እንደሚናገሩት ታጣቂዎቹ ሲመሩ የነበረው በትጥቅ እንቅስቃሴ ላይ በነበሩት እና ካላፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ የወረዳው ሲቪል ሰርቪስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በተሾሙት አቶ ሚሊሻ ቅላንጮ ነው።
“በህንጻው ውስጥ እናቶች፣ ባለሙያዎች ነበሩ። [ታጣቂዎቹ ሲገቡ] ጭንቀት ውስጥ ገብተው ራሳቸውን የሳቱ ነበሩ” ያሉት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ዐይን እማኝ፤ ሠራተኞች ራሳቸውን ለማትረፍ ወደ ህንጻው የተለያዩ ወለሎች ሲሯሯጡ እንደነበር አስረድተዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ ህንጻው ከገቡ በኋላ “ያልተመለሰላቸው ጥያቄ” እንዳለ በመግለጽ በየቢሮው እየዞሩ የወረዳውን አመራሮች ሲፈልጉ እንደነበር የዐይን እማኞቹ ገልጸዋል። በሰዓቱ ታጣቂዎቹ ያላቸው ጥያቄ ምን እንደሆነ በግልጽ እንዳልተናገሩም አክለዋል።
ይሁንና የታጣቂዎቹ ጥያቄ ለመቋቋሚያ የተሰጣቸውን የወርቅ ማውጫ ማሽን ሥራ ለማስጀመር ከሚያስፈልጋቸው የነዳጅ አቅርቦት ጋር የተያያዘ እንደሆነ መስማታቸውን የዐይን እማኞቹ እና የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ፤ የሚፈልጉት የወረዳውን ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደሆነ በመጥቀስ ወደ ህንጻው በመግባታቸው የተደናገጡትን ሠራተኞች ለማረጋጋት ሲሞክሩ እንደነበር የዐይን እማኞቹ ተናግረዋል።
አንድ የዐይን እማኝ፤ “[የታጣቂዎቹ መሪ] መጨረሻ ላይ ወደ ግራውንድ ወረዱ እና ውይይት እናድርግ አለ። …‘እናንተን ምንም አናደርጋችሁም። እኛ ጥያቄያችን እስከሚመለስ እናንተ ነገም ቢሆን ሥራ እንዳትገቡ’ አለ። ባለሙያውም ወደ ቤቱ ተሰናበተ” ሲሉ ሁለት ሰዓት በላይ ከቆየ እገታ በኋላ ከህንጻው መውጣታቸውን ገልጸዋል።
የትምህርት ባለሙያ የሆኑት የዐይን እማኝም ሠራተኞች ሥራ እንዳይገቡ በታጣቂዎቹ እንደተነገራቸው አረጋግጠዋል። ይህንን ተከትሎም ዛሬ [ማክሰኞ ረፋድ ድረስ] ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ሁለቱም የመንግሥት ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድባጤ ከተማ ነዋሪ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን አረጋግጠዋል። ዛሬ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት የሄዱ ተማሪዎችም ከቆይታ በኋላ መመለሳቸውን እና ከትላንት [ሰኞ] ጀምሮ የባንክ አገልግሎት መቆሙን ሦስት ነዋሪዎች አስረድተዋል።
ቢቢሲ የትናንቱን ክስተት አስመልክቶ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ወደ መተከል ዞን እና ድባጤ ወረዳ ኃላፊዎች ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች አልተሳኩም።
ሰኞ ዕለት እገታውን የፈጸሙት የጉሕዴን ታጣቂዎች መሆናቸውን የዐይን እማኞች ቢናገሩም የጉሕዴን ሊቀ መንበር አቶ ግራኝ ጉደታ፤ ፓርቲው ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እንደሌሉት ለቢቢ ተናግረዋል። አቶ ግራኝ፤ ትናንት ስለተፈጸመው እገታ የደረሳቸው ሪፖርትም ሆነ የሰሙት መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።