![አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ዘመነ ካሴ [ከላይ ጀምሮ ከግራ ወደ ቀኝ]](https://i0.wp.com/ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/deb3/live/856ce170-f661-11ee-97f7-e98b193ef1b8.jpg?w=800&ssl=1)
ከ 2 ሰአት በፊት
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎ ድምጽ ተቀድቶ በመሠራጨቱ ምክንያት በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ የተከሰሱ ግለሰቦችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ እንደማይሰማ ፍርድ ቤቱ አስታወቀ።
ችሎቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተመለከተ አቤቱታ በጽሁፍ እንዲቀርብ ብይን መስጠቱን ከተከሳሾች ጠበቃ አንዱ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ብይኑን የሰጠው ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 1/2016 ዓ.ም. የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሕገ መንግሥት እና ሽብር ወንጀል ችሎት ነው።
ችሎቱ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ከ52ቱ ተከሳሾች መካከል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሚገኙት ተከሳሾች ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡትን የቃል አቤቱታ ለመስማት ነበር።
ባለፈው ሳምንት አርብ በነበረው የችሎት ውሎ ከ14ቱ ተከሳሾች መካከል አንደኛ ተከሳሽ አቶ ዮሐንስ አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር። ሁለተኛው ተከሳሽ አቶ ክርስቲያን ታደለ ደግሞ በከፊል አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን ጠበቃቸው አስታውሰዋል።
አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ ቀሪዎቹ 13 ተከሳሾች በዛሬው የችሎት ውሎ አቤቱታቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ሆኖም ግን ፍርድ ቤቱ የዛሬውን የችሎት ውሎ የጀመረው የዐቃቤ ሕግን አቤቱታዎች በመቀበል መሆኑን አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ዐቃቤ ሕግ “የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጸመ የተባለው አካል በሌለበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ መቀበል ተገቢ አይደለም ስለዚህ አቤቱታው መቅረብ ያለበት በጽሁፍ ነው” የሚል ጥያቄ ማንሳቱን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።
- በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና ክርስቲያን ታደለ ላይ የተመሠረተው ክስ ምን ይዟል?5 ሚያዚያ 2024
- በፍኖተ ሰላም ከተማ በቀናት ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ገበያ ውስጥ በፈነዳ ቦምብ 27 ሰዎች ተጎዱ8 ሚያዚያ 2024
- እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ “እንደ መደበኛ ታሳሪ እንዲታዩ” ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አስተላለፈ29 መጋቢት 2024
ከዚህ በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ቀጣይ ቆይታ ላይም አስተያየት ሰጥቷል።
ዐቃቤ ሕግ “እኛ ሥራ የሚበዛብን ስለሆነ ቀጣይ ምርመራዎችም ስላሉብን የፌደራል [ፖሊስ] የወንጀል ምርመራ የጊዜያዊ ማቆያውን ስለምንፈልገው ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ” የሚል አቤቴታ ማቀረቡን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ዛሬ ችሎቱ የተቀጠረው፤ “የቀሪ ተከሳሾችን የሰብዓዊ መብት ጥሰት [አቤቱታ] ለመስማት” መሆኑን በማንሳት የደንበኞቻቸው አቤቱታ አንዲሰማ ጠይቀዋል።
ሆኖም ችሎቱ “በባለፈው ቀጠሮ የሰጠው ትዕዛዝ የቀሪ ተከሳሾችን አቤቱታ ለመስማት ቢሆንም ይኼን የሚያቋርጥ ነገር ተከስቷል” በሚል አቤቱታውን ላለመስማት አቋም ስለመያዙ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።
ችሎቱ “የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታውን የማንሰማበት ምክንያት ከዚህ በፊት የነበረው የችሎት ውሎ ተቀርጾ በመውጣቱ፣ ይህም የፍርድ ቤቱን ገለልተኝነት የሚጎዳ ሆኖ ስላገኘነው ይህንን ላለማስኬድ ችሎቱ አቋም ወስዷል” ማለቱን አቶ ሰለሞን አብራርተዋል።
ይህን ተከትሎም የሰብዓዊ መብት አያያዝን የተመለከተ አቤቱታ በጽሁፍ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ የተከሰሱበት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ፍርድ ቤቶች ተከሳሾች ለሚያቀርቧቸው የመብት ጥያቄ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ያትታል።
የዳኝነት ሥልጣንን የሚያትተው አዋጁ ክፍል፤ “ፍርድ ቤቶች በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘው ሰው ወይም የተከሰሰው ሰው ከአያያዙ ጋር በተያያዘ በሚያነሳው የመብት ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት መመርመር እና ተገቢውን ማስተካከያ እንዲደረግ አግባብነት ላለው አካል ትዕዛዝ መስጠት አለባቸው” ሲል ይደነግጋል።
ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም “የድምጽ ቅጂው ከፍርድ ቤት ነው የወጣው አይደለም የሚለውን ለማጣራት ባለፈው ቀጠሮ የተከሳሾችን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አቤቱታ የቀዳው ማሽን በፌደራል ፖሊስ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ለፍርድ ቤቱ እንዲያቀርብ” ሌላም ብይን ሰጥቷል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከዛሬ ጀምሮ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤቱ ታዝዟል።
የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ሦስት ችሎት ያልቀረቡ ተከሳሾችን በተመለከተም ለ36ቱ በጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግ 40ኛ እና 51ኛ ተከሳሾችን ደግሞ ፖሊስ እንዲያቀርብ አዝዟል።