የአባል አገራቱ ሰንደቅ ዓላማ

ከ 4 ሰአት በፊት

ኢትዮጵያ ስምንት አባላት ያሉት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊ ድርጅት አባል ልትሆን መሆኑ ተገለጸ።

ሶማሊያን ከተቀበለ ጥቂት ወራትን ያስቆጠረው ቀጣናዊው ድርጅት ኢትዮጵያንም በዘጠነኛ አባልነት ሊቀበል መሆኑን የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የበረሃማ፣ ከፊል በረሃማ አካባቢዎች ክልላዊ ልማት የካቢኔ ፀሐፊ ፔኒናን ማሎንዛ መግለጻቸውን የኬንያ መንግሥታዊ ሚዲያ ኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኬቢሲ) ዘግቧል።

ፀሐፊዋ በኢትዮጵያ እና በምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አመራሮች መካከል እየተደረገ ያለው ንግግር የመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እና በቅርቡም ኢትዮጵያ የኅብረቱ አባል አገር እንደምትሆን የተናገሩት ኪቱይ በተሰኘው አካባቢ የእርዳታ እህል ማከፋፋያ ፕሮግራም እየመሩ በነበሩበት ወቅት እንደሆነ ከኬቢሲ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል መሆን እንደምትፈልግ የገለጸች ሲሆን፣ ጫፍ ላይ ስለመድረሷ ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም።

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊ ድርጅት ስምንት አገራትን ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያን በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ ዋና መቀመጫውም በታንዛኒያ አሩሻ ነው።

የ300 ሚሊዮን ሕዝብ የመገበያያ መድረክ የሆነው ማኅበሩ ኢትዮጵያ አባል በምትሆንበትም ወቅት የግብይት ሁኔታው ከአምስት መቶ ሚሊዮን በላይ እንደሚያደርሰው የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዋና ፀሐፊ ፒተር ማቱኪ በቅርቡ ለኬንያው ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ተናግረዋል።

ግማሽ ቢሊዮን አባላትን የሚወክል ማኅበረሰብ ሳያካትቱ ስለ ገበያም ሆነ ስለደኅንነት የሚደረጉ ውይይቶች የማይታሰቡ ያደርጋቸዋል ብለዋል ዋና ፀሐፊው።

የሰባቱ አገራት ጥቅል ብሔራዊ ምርት (ጂዲፒ) ባለፈው ዓመት 346.17 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትንበያ ወስዶ የዘገበው የታንዛኒያው ዘ ሲትዝን በበኩሉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቡን መቀላቀል ድርጅቱን ኃያል ያደርገዋል ብሏል።

አይኤምኤፍ በባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ያልተጣራ ገቢ 156.1 ቢሊየን ዶላር አንዲሁም የሶማሊያ 8.74 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆን መተንበዩን ጠቁሞ አጠቃላይ የዘጠኙ አገራት ሲደመር 511.1 ቢሊየን ዶላር ይሆናል ተብሏል።

ኢትዮጵያ በምትቀላቀልበት ወቅት ቀጣናዊውን ድርጅት በአፍሪካ ከፍተኛ ጂዲፒ ካላቸው ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ የላቀ ቦታ እንደሚያስቀምጠውም ዘገባው አስነብቧል።

የአባል አገራቱን ቁጥር እየጨመረ ያለው ቀጣናዊው ድርጅት ባወጣው ፕሮቶኮል መሠረት አገራቱ የሚገበያዩበት አንድ ገንዘብ ላይ ለመድረስም ወሳኝ ፖሊሲዎችን እየገመገሙ ይገኛሉ ተብሏል።

በዓለም ላይ ጠንካራ ትስስር ካላቸው የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አንዱ ሆኖ ማየት እንደሆነም ራዕያቸውን የገለጹት ዋና ጸሐፊው ድንበር አልባ የሆነች አህጉር አጀንዳንም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

በተጨማሪም የአገራቱ አየር መንገዶች በጋራ የሚሠሩበት መንገድ ተቀይሶ በአባላቱ መካከል የሚደረገውን የአየር ትራንስፖርትን ተመጣጣኝ በማድረግ ሕዝቡ ቀላል በሆነ መንገድ የንግድ ልውውጥ መደረግ አለበት ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ አርባ ሚሊዮን ዶላር መዋጮ ባለመክፈላቸው ችግር ገጥሞ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ግን አገራቱ ያለባቸውን ውዝፍ መዋጮ እየከፈሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለም ተገልጿል።

የንግድ ማኅበረሰቡ ከአባል አገራቱ መወጮ በተጨማሪ 60 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን የሚያገኘው ከልማት አጋሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ተገልጿል።

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ለ2023/2024 ዓመት 103 ሚሊዮን 842 ሺህ 880 ዶላር በጀት ይዞ እንደነበር ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ባለፈውም ዓመትም የማኅበረሰቡ አጠቃላይ ንግድ ከአውሮፓውያኑ 2022፣ 74.03 ቢሊዮን ዶላር በ13.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2021ም አጠቃላይ ንግዱ 65.268 ቢሊዮን ዶላር እንደነበርም ተመልክቷል።

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 1999 ሲሆን፣ ቀዳሚ አባላቱም ሦስቱ አገራት ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ነበሩ።

በአሁኑ ወቅት አባላቱ ወደ ዘጠነኛ ሊያድጉ ጫፍ ላይ የደረሰው ድርጅቱ ራዕይ ብሎ የያዘው የበለፀገ፣ ተወዳዳሪ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የተረጋጋ እና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው ምሥራቅ አፍሪካን መመሥረት መሆኑን በድረ ገጹ አስፍሯል።