ዜና
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ በፀጥታ ችግር ሥራ ለማቆም እየተገደደ መሆኑ…

ፅዮን ታደሰ

ቀን: April 10, 2024

የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት የስኳር ፋብሪካ በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ መሆኑንና ችግሩ ትኩረት ተሰጥቶት በፍጥነት ካልተፈታ ፋብሪካው እስከ መዘጋት ሊደርስ እንደሚችል ተገለጸ፡፡

በደቡብ ኢትየጵያ ክልል የሚገኘውና በ2013 ዓ.ም. ተጠናቆ ሥራ የጀመረው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት የስኳር ፋብሪካ፣ በአካባቢው የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ካልተፈታ፣ ማዘጋት ደረጃ እንደሚያደርስ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ ፈለቀ ቶማ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹የፀጥታው ችግሩ እጅግ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በየጊዜው መሐንዲሶች ይገደላሉ፣ በዚህም ምክንያት ሠራተኞቹ ከፋብሪካው እየለቀቁ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ችግሩ  ባለሙያዎችን እንዲያጡ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ የፀጥታ ችግሩን ፋብሪካው ሊፈታው ስለማይችል የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት በጋራ ሆነው መፍትሔ እንዲፈልጉ ጠይቀዋል፡፡

ፋብሪካው ከ25 ሺሕ ሔክታር መሬት በላይ የሚሸፍን መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ጥበቃውን ለማጠናከር ያልተቻለው በስፋቱ ምክንያት መሆኑን ገልጸው፣ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ማስተባበር ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ምንም እንኳን በፋብሪካው አካባቢ የመንግሥት የፀጥታ አካላት ቢኖሩም፣ ችግሩ ፖለቲካዊ መፍትሔ ጭምር የሚሻ ነው ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከስኳር ፋብሪካው የሥራ ኃላፊዎች፣ ከሠራተኞች ተወካዮች፣ ከወረዳ አመራሮችና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ በውይይቱ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ ኮሬ (ዶ/ር) በአካባቢው ያለው የፀጥታ ችግር እንዲፈታ፣ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግሥት አመራሮች ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከፋብሪካው ኃላፊዎች ጋር በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው ነበር፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ወለይቴ ቢቶ፣ የፋብሪካው መገንባት ለአካባቢው ሕዝብ ጥቅም እንዳለው ገልጸው፣ አልፎ አልፎ የሚታየውን የፀጥታ ችግር ለማስወገድ የአካባቢው ማኅበረሰብ የበለጠ ኃላፊነት ወስዶ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዚዳንት የመሠረተ ልማት አማካሪ አቶ ይልማ ሱንታ፣ ፋብሪካው የፌዴራል ፕሮጀክት በመሆኑ የፌዴራል መንግሥት ወደ ፋብሪካው የሚወስደውን 86 ኪሎ ሜትር የመንገድ ችግር መፍታት ይገባዋል ብለዋል፡፡

ፋብሪካው ሥራ ቢጀምርም የፕሮጀክት ሥራው ባለመጠናቀቁ በተለይም ፋብሪካው መፍጨት የሚችለውን ያህል ሸንኮራ ማምረት አለመቻሉን ዋና ሥራ አስኪያጁ ፈለቀ (ኢንጂነር) ገልጸው፣ በተያዘው ዓመት 151,200 ኩንታል ስኳር ለማምረት ዕቅድ ተይዞ ባለፉት ስምንት ወራት 94,570 ኩንታል ማምረት መቻሉን አስረድተዋል፡፡