

ዜና የዶንጋ ብሔረሰብ ተወላጆች እስራትና ዕገታ እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገለጸ
ቀን: April 10, 2024
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሲመሠረት የዶንጋ ብሔረሰብ መሥራች ከሆኑት ውስጥ አንዱ ቢሆንም፣ የየብሔረሰቡ ተወላጆች በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተደራጅተው ልዩ ወረዳ የመሆን ጥያቄ ሲያነሱ እስራትና ዕገታ እየደረሰባቸው መሆኑን፣ የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት አስታወቀ፡፡
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 የክልሉ መንግሥት መሥራች ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩል መብትና ሥልጣን አላቸው ቢልም፣ የዶንጋ ብሔረሰቦች መብት እየተከበረ አለመሆኑን ፓርቲው ሰኞ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የዶንጋ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀመንበር አቶ አየለ መኮንጎ እንደገለጹት፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መሥራች ከሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ዘጠኙ በዞንና በልዩ ወረዳ የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት አኳያ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የዶንጋ ብሔረሰብ ሕገ መንግሥታዊ የመደራጀት ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ ምላሽ አላገኘም፡፡
የዶንጋ ብሔረሰብ ተወላጆች ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡ፣ ተወላጆችም ሆኑ የድርጅቱ አባላት እየታሰሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ እስካሁን ዘጠኝ የድርጅቱ አባላትና ሃያ የብሔረሰቡ ተወላጆች ሲታሰሩ 16 ተወላጆች ደግሞ መታገታቸውንና የት እንደገቡ እንደማይታወቅ ከወላጆቻቸው ማወቅ መቻሉን ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
የዶንጋ ብሔረሰብ በልዩ ወረዳ የመደራጀት መብት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረ በርካታ ዓመታት መቆጠሩን ያስታወሱት ሊቀመንበሩ፣ በአሁኑ ወቅት የዶንጋ ብሔረሰብ ተወላጆች በከንባታ ዞን አስተዳደር አመራሮች ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕገ መንግሥታዊ የመብት ጥያቄዎች ሳይመለሱ ረዥም ጊዜ ማስቆጠሩ የተዛባ የፖለቲካ አጀንዳ በመፍጠር የክልሉን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶችን አደጋ ላይ መጣሉን አክለው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የብሔረሰቡ በልዩ ወረዳ የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚደግፍ የጠንባሮ፣ የወላይታና የሀዲያ ተወላጆች በከንባታ ዞን ዱራሜ ማረሚያ ቤት ውስጥ መታሰራቸውን አብራርተዋል፡፡
‹‹የዶንጋ ብሔረሰብ መንግሥትን እየጠየቀ ያለው የልማትና የመዋቅር ጥያቄ እንጂ የአመራር ለውጥ አይደለም፡፡ የአመራሮች መቀያየር ለዶንጋ ብሔረሰብ ምንም ዓይነት ልማትና የመዋቅር ለውጥ እያመጣ ስላልሆነ፣ በነባሮች አመራሮች የሚደረግ የአደረጃጀት ለውጥ ለሕዝብ አገልጋይነት ሳይሆን የግል ፍላጎቶችን ለማርካታ ነው፤›› በማለት ድርጅቱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በዚህ መሠረት የከምባታ ዞን አመራሮች የዶንጋ ብሔረሰብ ዞኑ ውስጥ ተለጥፎ ይኖራል የሚለውን ዕሳቤ በመያዝ፣ ሕዝብ ያላመነውን አደረጃጀት ለመሥራት ከመረባረብ ይልቅ በብልፅግና ዕሳቤ ሕገ መንግሥቱን የመተርጎም ድርሻ እንዲወጣ ድርጅቱ አሳስቧል፡፡
የዶንጋ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ እንሁን የሚለውን ጥያቄ በማቅረቡ የመንግሥት ሠራተኞች የሁለት ወራት ደመወዛቸውን መከልከላቸውን ጠቅሰው፣ የጤና ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ጭምር መዘጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ምክንያት የዶንጋ ብሔረሰብ ተወላጆች ወደ ወላይታ ሄደው የሕክምና አገልግሎት እንደሚያገኙ፣ በአሁኑ ወቅትም በርካታ የብሔሩ ተወላጆች ከትምህርት ገበታቸው መቅረታቸውን አክለዋል፡፡
የዶንጋ ብሔረሰብ ይህንን ጥያቄ በመጠየቁ የብሔረሰቡ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ አታገኙም እየተባሉ እንደሆነ የተናገሩት የዶንጋ ብሔረሰብ ተወላጅና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካይ አቶ ደነቀ ዲጃኮ ናቸው፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተመሠረተው በአሥር ብሔር ብሔረሰቦች መሆኑንና በሕገ መንግሥቱ ውስጥም መቀመጡን ገልጸው፣ የዶንጋ ብሔረሰብ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ልዩ ወረዳ እንሁን የሚል ጥያቄ ለክልሉ በያተደጋጋሚ ቢያቀርብም መልስ አለማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በፊት በከንባታ ጠንባሮ ዞን ውስጥ ሦስት ብሔር ብሔረሰቦች ማለትም ከንባታ፣ ጠንባሮና ዶንጋ የተሰኙ ብሔር ብሔረሰቦች አብረው እንደሚኖሩና በአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ አደረጃጀት የጠንባሮ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ መሆኑን የዶንጋ ብሔረሰብ ሽማግሌዎች በመግለጫው ወቅት ተናግረዋል፡፡
በዚህ መሠረት የዶንጋ ብሔረሰብ እንደ ጠንባሮ ብሔረሰብ ልዩ ወረዳ የመሆን ጥያቄ ማቅረቡን የገለጹት የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች፣ ጥያቄውንም ለክልሉ መንግሥት ሲያቀርቡ ውይይት ተደርጎበት ምላሽ እስከሚሰጥ ድረስ ታገሱ መባላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ለክልሉ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ በተደጋጋሚ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልጸው፣ ብሔረሰቡ አዎንታዊ ምላሽ ያለገኘበት ምክንያት ምን እንደሆነ ወደፊት የክልሉን መንግሥት እንደሚጠይቁ ገልጸዋል፡፡