
April 10, 2024 – EthiopianReporter.com
መንግሥት የቱሪስት መሠረተ ልማቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መረባረቡ ከፍተኛ መነጋገሪያን የፈጠረ ጉዳይ ነው፡፡ በርካቶች ይህን የመንግሥት የልማት ዕቅድ ሲደግፉት ቢታዩም በርካቶች ደግሞ ይተቹታል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ለሰላም መስፈንና ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ በቂ ትኩረት ሳይሰጥ መናፈሻና ፓርኮችን መሥራቱ ተገቢነት የለውም ብለው የሚቃወሙ አሉ፡፡ ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የአገሪቱን ገጽታ የሚቀይሩ ሥራዎች ናቸው እየተሠሩ ነው የሚሉ ወገኖች ደግሞ አካሄዱን ሲደግፉት ይታያል፡፡ አገሪቱ በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካው ከምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ይህ የቅድሚያ ትኩረቷ ሊሆን አይገባም አሉ፡፡ የውበትና መናፈሻ ፕሮጀክቶቹ የወጣባቸውን ወጪ ለመሸፈን ረጅም ጊዜ የሚጠይቁ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከእነዚህ ይልቅ በፍጥነት ጥሩ ገቢና ዕድገት በሚፈጥሩ ልማቶች ላይ ቢተኮር ይሻላል የሚል ሐሳብ የሚሰጡም አሉ፡፡ ያም ቢሆን ግን መንግሥት ለእነዚህ ልማቶች ልዩ ትኩረትና ቅድሚያ በመስጠት ሲሠራቸው ነው የሚታየው፡፡

ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት መገባደዳቸው ብቻ ሳይሆን በውበትና ጥራት ደረጃቸው የብዙዎችን ትኩረት ማግኘታቸው ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለመገንባት እየጠየቀ ባለው መዋዕለ ነዋይ፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂም የተነሳ ትኩረት ሲስቡም ይታያል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሰሞኑ የተጀመረውና በፍጥነት እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ብዙ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ ነባር የመኖሪያ መንደሮች መፍረሳቸው፣ የከተማውን የቀደመ ታሪክ ያሳያሉ ተብለው የሚገመቱ አካባቢዎች መፍረሳቸውና የቆዩ ሠፈሮች ገጽታዎች እየተቀየረ መሆኑ ከፍተኛ ክርክር አስነስቷል፡፡ ደሃውን የከተማ ነዋሪ ከነባር መንደሮች ማፈናቀል ነው የተያዘው ከሚሉ ወቀሳዎች ጀምሮ የከተማውን ነዋሪ የብሔር ስብጥር ለመቀየር የተጀመረ ፕሮጀክት ነው የሚል የመረረ ክስም በፕሮጀክቱ ላይ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡
ይህን በሚመለከት ከሰሞኑ የከተማው ከንቲባና ምክትል ከንቲባን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በተከታታይ ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠታቸው የተነገረው ከንቲባ አዳነች አቤቤ አምስት ዋና ዋና የከተማዋ መንገዶችን ተከትሎ የሚካሄደው የኮሪደር ልማት ከተማዋን የመቀየር እንጂ ሌላ ፖለቲካዊ ዓላማም ሆነ የተለየ መነሻ እንደሌለው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
የኮሪደር ልማቱን ‹‹ድህነትን ለመቅረፍና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ሲባል የሚሠራ፤›› ብለውታል ከንቲባዋ በዚሁ መግለጫቸው፡፡ ‹‹የዲፕሎማሲ መዲና እንደመሆናችን ተወዳዳሪነታችንን ማሳደግ ይገባናል፤›› በማለትም አክለዋል፡፡ የከተማ አሰፋፈርን ለመቀየርም ሆነ ነባር የከተማ መንደሮችን ስምና ታሪካዊነት ለመቀየር የተጀመረ አለመሆኑን ሞግተዋል፡፡ ቅርሶችን ማፍረስም ግቡ አይደለም ሲሉ ስለፕሮጀክቱ የተከራከሩት ከንቲባዋ፣ ከዚያ ይልቅ የተዋበ፣ ምቹና የተሟላ አገልግሎት ያላት ከተማን መገንባት ያለመ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ያቀፋቸው የመንገዶች፣ የመንገድ ዳርቻዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ አረንጓዴ ልማቶችና አደባባዮች ግንባታ እስከ ሰኔ 30 እንደ ሚጠናቀቁ ቃል የገቡት ከንቲባዋ የፈረሱ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ክፍት ቦታዎችም በግልጽ በሚወጣ ጨረታ ነው የሚሸጡት ብለዋል፡፡ ቦታዎቹን የሚረከቡ ዓልሚዎች በተጠናው መሠረት ከተማውን በሚመጥን መንገድ ግንባታቸውን እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ባለው የፕሮጀክቱ ክዋኔ ሒደት ነዋሪው የሚያነሳው ቅሬታ ካለ የቅሬታ መቀበያና የመፍቻ ሒደት አበጅተናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ዣንጥራር አባይ እሑድ ምሽት ከብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቆይታም ተመሳሳይ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዋና ዓላማ ‹‹የከተማን ደረጃ ማሳደግ፣ የመሬት አጠቃቀም ምጣኔን ማሻሻል፣ ስማርት የሆነ አኗኗር መፍጠር ነው፤›› ብለዋል፡፡
በከተማው በየቦታው የተሠሩ የተበጣጠሱ ልማቶችን ማስተሳሰርም ሌላው ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቤት ልማት አጀንዳችን ነው፣ ቀልጣፋ የትራንስፖርት አገልግሎት መፍጠር አጀንዳችን ነው፣ የሥራ ዕድል መፍጠር አጀንዳችን ነው፣ ልማት አጀንዳችን ነው፣ ይህን ደግሞ በተቀናጀ ሁኔታ ለመምራት ዕቅድ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ የገባበትን መነሻ ተናግረዋል፡፡
ይህ የኮሪደር ልማት ከሁሉም በላይ አንገብጋቢ የሆነው ለብዙ ልማቶች መሠረት ስለሚሆን ነው በማለት የሞገቱት አቶ ዣንጥራር የከተማ አስተዳደሩ ዕቅዱን ካወጣ በጣም መቆየቱንና ሁለት ዓመት ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡
ከንቲባዋ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ፕሮጀክቱ መታቀዱን ቢናገሩም አቶ ዣንጥራር ግን ፕሮጀክቱ ከተወጠነ ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩን ሞግተዋል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝቡን አወያይተናል የሚሉት አቶ ዣንጥራር ዕቅዱ በአማካሪ ድርጅቶች ስለመሠራቱና ቤት ለቤት ተኪዶ ጥናት ስለመደረጉ ጭምር ገልጸዋል፡፡ እሳቸውን ጨምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ወረዳዎች ከሕዝቡ ጋር አመራሩ ምክክር ማድረጉን የገለጹ ሲሆን ‹‹ሚዲያ በይፋ ጠርታችሁ መግለጫ አልሰጣችሁም ካልተባለ በስተቀር ጥናቱ ሲደረግና ሲዘጋጅ ነዋሪው ያውቀዋል፡፡ እኔን ጨምሮ በሁሉም የከተማው ወረዳዎች የሕዝብ ውይይት አድርገናል፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡
የከተማው አመራሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ይህን ቢናገሩም የኮሪደር ልማቱ በበርካታ ስሞታዎች ታጅቦ ነው ትግበራው የቀጠለው፡፡ በቅርቡ በተለይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በማኅበራዊ ገጻቸው ለጠፉት የተባለው በአዲስ አበባ ስለሚካሄዱ ልማቶች የሚያወሳው መረጃ ከዚሁ ከኮሪደር ልማት ጋር ተቆራኝቶ ሲቀርብ ነው የከረመው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ባህል፣ ማንነትና ውክልና እንዲሁም ጥቅም የሚያስከብሩ የልማት ሥራዎች በአዲስ አበባ እየተካሄዱ ነው የሚል ይዘት ያለው የአቶ ሽመልስ መረጃ ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተቆራኝቶ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ የመጠቅለል የፖለቲካ ሴራ ንድፈ ሐሳቦችን እንዲቀሰቀሱ ሲጋብዝ ታይቷል፡፡
በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን በአዲስ አበባ የሚሠሩ የልማት ሥራዎች የአንድ ፖለቲካ ቡድንን ፍላጎትና ጥቅም ማስጠበቂያ ሆነዋል ሲባል መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲመጣ በልማት ስም ማፈናቀል እንደማይኖር ቃል ሲገባ ቢታይም ብዙም ሳይዘገይ በአዲስ አበባ ጉዳይ ኢሕአዴግ የሄደበትን መንገድ እየደገመ ነው የሚል ክስ በተደጋጋሚ ሲሰማበት ቆይቷል፡፡ የአዲስ አበባ መልሶ ማልማት ሥራዎችና ከተማ ነክ ልማቶች ታሪክ ነዋሪውን ያማከሉ አይደሉም ከሚለው በተጨማሪም ታሪካዊ የከተማውን እሴቶች አጥፍተዋል የሚል ወቀሳም መቅረቡ ሲደጋገም ይታያል፡፡
ይህ ያስቆጣቸው የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ጠንከር ያለ ቃላት ሲጠቀሙ ታይተዋል፡፡ ማንም የጠፈጠፈውን ጭቃ ታሪክ አትበሉ ሲሉ በከተማ መልሶ ማልማት ፕሮጀክቶች ወደመ የሚባለውን የከተማ ቅርስ ጉዳይ ጨርሶ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ይህን ቢልም ብዙዎች ግን ለከተማ ልማት ፕሮጀክቱ ፖለቲካዊ ገጽታ ሲያላብሱት ይታያል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓት በተቀያየረ ቁጥር አዲስ አበባን የመሳሰሉ ከተሞች የፖለቲካ ሥርዓቱን መልክ እንዲላበሱ የማድረግ አባዜ የነበረ ነው የሚሉ ወገኖች በንጉሡ ዘመን በዘውዳዊ ሥርዓቱ መጠሪያ የሆኑ ግንባታዎች በርከት ብለው ይገነቡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ደርግ ሲመጣ መስቀል አደባባይን የመሳሰሉ የከተማ ምልክት የሆኑ ቦታዎችን አብዮት አደባባይ ብሎ ኮሙኒስታዊ ገጽታ ከማላበስ ጀምሮ የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት መናፈሻና የድላችን ሐውልት ማሳነፁን በምሳሌነት ያስታውሳሉ፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ አብዮት አደባባይን ወደ መስቀል አደባባይነት መጠሪያውን ከመመለስ ጀምሮ የሌኒን ሐውልትን እስከ ማፈራረስ የመሳሰሉ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን ይገልጻሉ፡፡
ይህ ሥርዓት በተለዋወጠ ቁጥር የከተማ ገጽታን የመቀየር አባዜም መናፈሻ፣ ፓርኮችና ሙዚየሞችን መገንባት በሚያዘወትረው በአሁኑ የብልፅግና መንግሥት ዘመን ስለመቀጠሉ የሚተቹ በርካቶች ናቸው፡፡
ብዙ የከተማውን አካባቢዎች አፍርሶ መልሶ ማልማትን የሚጠይቀው የሰሞኑ የኮሪደር ልማት ትግበራ ከፖለቲካ በተጨማሪም የቅደም ተከተልና የኢኮኖሚ ጥያቄም እየተነሳበት ይገኛል፡፡ አሁን ላይ አገሪቱ ከየት አምጥታ ነው ይህን ፕሮጀክት የምትሠራው ከሚለው ጀምሮ በመንግሥት ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ የራሱን የጊዜ ዑደት ጠብቆ መካሄድ የሚችል ልማት ነው የሚለው ሙግት ተደጋግሞ ሲነሳበትም ቆይቷል፡፡ በሌላ በኩል በከተማ ልማትና መልሶ ግንባታ ስም ውድ የአገር ሀብትና ንብረት ለብክነት እየተጋለጠ ነው የሚል ስሞታ የሚያሰሙም አልጠፉም፡፡
አንዳንድ ወገኖች ፕሮጀክቱ ለሕዝቡ ነው ወይ የሚሠራው ሲሉ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል፡፡ የእናት ፓርቲ ተወካዩ ጌትነት ወርቁ ባለፈው ሳምንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስላደረጉት ምክክር ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ የከተማ መልሶ ማልማት ሥራዎችን የተመለከተ ሐሳብ አንስተው ነበር፡፡ የከተማ መልሶ ማልማቱ ሥራ ለሕዝቡ ከሆነ የሚሠራው ሕዝቡን ከነባር መኖሪያው ማፈናቀሉ ለምን አስፈለገ ሲሉ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ነዋሪው ባለበት ሆኖ ልማቱ መካሄድ ለምን አይችልም በማለትም ተከራክረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በሸገር ሬዲዮ ሸገር ካፌ ፕሮግራም በተከታታይ ይቀርቡ በነበሩ የከተማ መልሶ ልማት ሥራዎችና በዘመናዊነት ዙሪያ ሐሳብ በማጋራት የሚታወቁት ሽመልስ ቦንሳ (ዶ/ር)፣ በአንድ ወቅት የአዲስ አበባን አከታተምና አሰፋፈር ሒደት በሰፊው አብራርተው ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከኢጣሊያ ወረራ በኋላ በነበረው ዘመን ከተማውን አውሮፓ እንዳዩት የተዋበ ለማድረግ ባደረባቸው ቀናይነት ዘመናዊ ግንባታዎችን መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ አደባባዮች፣ ፎቆችና መንገዶች በሰፊው ተገነቡ፡፡ ከተማውን በማስተር ፕላን የመምራት ጥረትም ተደረገ፡፡ ይሁን እንጂ የሕዝቡ አሰፋፈር ያንን የመንግሥትን ሐሳብ የተከተለ መሆን ሳይችል እንደቀረና የራሱን አኗኗርና ማኅበራዊ መስተጋብር ተከትሎ መካሄድ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
ምሁሩ መንግሥት በየዘመናቱ ባካሄዳቸው የከተማ መልሶ ግንባታና ልማት ሥራዎች የሕዝቡን ነባር አኗኗር ተከትሎ ከማካሄድ ይልቅ ከውጪ የተቀዳ የከተማ ልማት ላካሂድ ማለቱ የአዲስ አበባን ገጽታ አዘበራርቆት መቆየቱን ሙያዊ ልምዳቸውን አጣቅሰው በተከታታይ ሲያብራሩ ተደምጠዋል፡፡
ፍሬድሪክ ኤበርት እ.ኤ.አ. በ2012 ባሳተመው ዘመናዊነት ምንድነው (ዋት ኢዝ ዘመናዊነት) በሚል የተለያዩ ምሁራን ሐሳባቸውን ባሰፈሩበት አንድ ጥናታዊ ዕትም ላይ የኪነ ሕንፃ ምሁሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው መምህር ፋሲል ጊዮርጊስ የአዲስ አበባ ከተማ ከተሜነት ዕድገትን ዳሰውት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከሌሎች የቅኝ ተገዥ አፍሪካ አገሮችም ሆነ ታዳጊ አገሮች በተለየ ሁኔታ ደሃውና ሀብታም ተጎራብተው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗ እንደጠቀማት ከትበዋል፡፡ የደሃ መንደር በሚባሉ መኖሪያ ሠፈሮች ሳይቀር አለፍ ሲሉ እጅግ ዘመናዊ ግንባታዎችና ፎቆች መታየታቸው የከተማዋን ማኅበራዊ ስብጥር ቅይጥ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡
አዲስ አበባ በአፄ ምኒልክ ዘመን የመኳንንቱ፣ የጦር መሪዎቹ፣ መሳፍንቱና ባላባቶቹ የሰፈሩበትን ቦታዎች ተከትላ አነስተኛ ሠፈሮች ይበቅሉባት ጀመር፡፡ የዘውዳዊ ሥርዓቱ ባለሥልጣናትን አሰፋፈር እየተከተለ ሠራዊቱና ተከታያቸው በዙሪያው የሰፈረባቸው መንደሮች ተፈጠሩ፡፡ ክፉ ቀን የተባለው የረሃብ ወቅት ወደ አዲስ አበባ ሠፈሮች የሚገባውን ፍልሰተኛ እንደ ጨመረውና ወደዚያ ለመኖር የሚመጡ መሳፍንትን ቁጥር እንዳበዛው ይነገራል፡፡ አፄ ምኒልክ የመንግሥታቸውን ገቢ ለመጨመር በሚል አዲስ አበባ የአገሪቱ የንግድ መስመሮች የሚነኳትና ብዙ የንግድ ልውውጥ የሚያልፍባት ከተማ እንድትሆን ጥረት አድርገዋል፡፡ ከቀረጥና ታሪፍ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር በሚል ብዙ የንግድና ሸቀጦች ፍሰት መዲና አድርገዋታልም ይባላል፡፡
በአዲስ አበባ ቤተ ክርስቲያናት የሚገኙበት ቦታን ከቦ መስፈርም በሕዝቡ ዘንድ የተለመደ ባህል ነበር፡፡ ከዓድዋ ድል በኋላ በሰፊው የገቡት የህንድ፣ የአርመንና የግሪክ ዜጎችም በአንድ አካባቢ ሰብሰብ ብሎ መኖርና መስፈር ጀመሩ፡፡ እነዚህ ሠፈሮች አንዱ ከሌላው ጋር በመንገድ ከመገናኘት በተጨማሪ ቀስ በቀስ እየሰፉ የአንድ ወጥ ከተማነት ቅርፅ መያዝ ጀመሩ፡፡
በልዑል አልጋ ወራሽነታቸው ወቅት አውሮፓን የጎበኙት አፄ ኃይለ ሥላሴ በውጭ ያዩትን ዘመናዊነት ለማምጣት ሞክረው ነበር፡፡ የውጭ አማካሪዎችና ከተማ ቀያሾች ቀጥረው ጭምር መንገዶችና ዘመናዊ መኖሪያ ሠፈሮችን ማስገንባት ጀመሩ፡፡ ይህን ዑደት ተከትላ ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ግንባታ ይካሄድባት ጀመር፡፡ ኢጣሊያን የምትመስል ከተማ ለመፍጠርም በፍጥነት የከተማ ልማት ሥራዎች መተግበር ቀጠሉ፡፡ ባለሁለት ድርብ ሕንፃዎች፣ የአውሮፓ ኪነ ሕንፃ አሻራ ያረፈባቸው ግንባታዎች በሰፊው ተካሄዱ፡፡ ጣሊያን ተሸንፎ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ ዙፋናቸው ሲመለሱ ደግሞ በአውሮፓ ያዩትን የከተማ አከታተም ባህል ለማስፈጸም ተነሱ፡፡ የእንግሊዝ አማካሪዎች ተቀጠሩ፡፡ አዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ከረጃጅም ፎቆች ጋር መተዋወቅ ጀመረች፡፡ በተመረጡ ቦታዎች በጊዜው ሰማይ ጠቀስ የተባሉ ፎቆችም መገንባት ጀመሩ፡፡
አዲስ አበባን ዘመናዊ በሚሏቸው ረጃጅም ፎቆች የማንቆጥቆጥ ፍላጎት ከዚያን ጊዜ ወዲህ በመጡ መንግሥታትም ዘመን ቀጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አበባ በሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ከመሞላት ይልቅ በተሰባጠረ አከታተም ነው የቀጠለችው በማለት የከተማ ልማት ምሁሩ ፋሲል ጊዮርጊስ በሰፊው ከትበውታል፡፡
ሲቀጥሉም አዲስ አበባ ስብጥሩ በበዛ ሀብታምና ደሃ ተጠጋግቶ በሚኖርበት የከተማ አሰፋፈር መሞላቷ ብዙ ማኅበራዊ መስተጋብር መፍጠሩን ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ አሁን አሁን ሀብታሞች በከተማው ዳርቻ በሚባሉ ሠፈሮች በሚገነቡ አዳዲስና ዘመናዊ ሠፈሮች መኖር መጀመራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ የቀደመው የተሰባጠረ አሰፋፈር በከተማዋ ከሌሎች አገሮች በተሻለ ወንጀል እንዲቀንስ፣ የዳበረ የማኅበራዊ ትስስር እንዲፈጠርና ሰላማዊ አኗኗር እንዲኖር ማስቻሉን ይገልጻሉ፡፡
በአዲስ አበባ የሚካሄደው የከተማ መሠረተ ልማት ግንባታና የከተሜነት መስፋፋት በቅርብ ዓመታት የሕዝብ የጋራ መገልገያ የሆኑ ክፍት ቦታዎችንና አደባባዮችን ጭምር መስዋዕት እያደረገ የሚገኝ ጤናማ ያልሆነ ልማት መሆኑን የጠቆሙት ምሁሩ እንደ ጃን ሜዳና መስቀል አደባባይ ያሉ ምልክት የሆኑ ቦታዎችን ማቆየት ፈተና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በየቦታው ከሚገጠገጡ ቁመታም ሕንፃዎች በተጨማሪ ቀለበት መንገድ ማሳለጫ እየተባለ ሰፋፊ መንገድ የመገንባት አካሄድ መስፋፋቱን ያስረዳሉ፡፡ ይህ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ ያሻሽላል ግንኙነትን ቀልጣፋ ያደርጋል ተብሎ የሚካሄድ ልማት ግን የመኪና ቁጥርን የሚጨምር፣ የመኪና እንቅስቃሴን የሚጨምር፣ የነዳጅ ፍጆታንና የአየር ብክለትንም በዛው ልክ የሚጨምር እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በከተማ ልማት ሒደት ትልቁ ቁም ነገር ለአገር የሚስማማ የልማት ፎርሙላን ማግኘት ነው የሚሉት የኪነ ሕንፃ ምሁሩ ፋሲል ጊዮርጊስ ከውጭ የተቀዳ ዘመናዊ የሚባል ነገርን ከመኮረጅ ይልቅ አገር በቀል ሐሳብና ዕውቀትን የቀመረ ከተጨባጩ አገር አቀፍ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚሄድ ዘዴን መተግበር ጤናማ ከተማን ለመፍጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል፡፡
በዚሁ የጥናታዊ ወረቀቶች ዕትም ከተማን የማደስና የመልሶ ማልማት ግንባታን የተመለከተ ሙያዊ ምልከታቸውን ያሰፈሩት ሌላኛው የኪነ ሕንፃ ምሁር ኤልያስ ይትባረክ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከተማ ማልማት፣ ከተማ ማዘመንም ሆነ ከተማ ማሳደግ ምንን ታሳቢ አድርጎ መከናወን እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ካሉ ቤቶች ውስጥ 70 በመቶዎቹ የቀበሌ ቤት የሚባሉ የጭቃ ቤቶች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ከተማውን የማሳደግ ልማት ተብሎ 80 ሺሕ ኮንዶሚኒየም ቤት መገንባቱን ይጠቁማሉ፡፡ የከተማውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ግን በወቅቱ 300 ሺሕ ቤት መገንባታ ያስፈልጋል ስለመባሉም ይገልጻሉ፡፡ የቀበሌ ቤቶች የሚባሉ በከተማው መሀል እምብርት የሚገኙ መኖሪያዎች በከተማው ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 40 በመቶውን እንደሚያኖሩ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ መኖሪያ መንደሮች የደሃ መኖሪያዎች ቢባሉም የከተማውን የቆዳ ስፋት 12 በመቶ ብቻ የሚሸፍኑ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
አዲስ አበባ እንደ ሌሎች ታዳጊ አገሮች ከተሞች ሁሉ ፈጣን የከተሜነት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ እየፈተናት ይገኛል፡፡ ይህ የከተሜነት ዕድገት ደግሞ ከተማውን ሙሉ ለሙሉ ገጽታውን እስከ መቀየር መሄድ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጉዳይ መጠየቅ አለበት፡፡ ከተማን መለወጥ፣ ከተማን መቀየር፣ ከተማን ማስዋብ ሲባል ሥር ነቀል የሆነ አብዮት ማካሄድ ነው ወይ የሚለው መጠየቅ አለበት፡፡ ከተማ ማልማትና ከተማ ማሳደግ ጭርንቁስ ወይም የደሃ መንደሮች የሚባሉ አካባቢዎችን ደረጃውን በሚመጥን የመሠረተ ልማት ግንባታ ማደስ ወይም ነባር ማንነታቸውን ሳይለቁ ዘመናዊ ማድረግ ሊሆንም ይችላል ሲሉ ባለሙያው ያብራራሉ፡፡
በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የከተማ ልማት እንቅስቃሴ በተለይም በአዲስ አበባ የተለመደው አሠራር የአውሮፓዊ ዘመናዊነት ባህል የተጫነውና በመንግሥት ፍላጎት ብቻ የሚመራ ነው ሲሉም ባለሙያው ኤልያስ (ዶ/ር) ይበይኑታል፡፡
የከተማ ነዋሪ መሆን የተሻለ መሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ያመጣል ለዘመናዊነትና ለሥልጣኔ ቅርብ ያደርጋል የሚለው እምነት በኢትዮጵያ ገዥ ሐሳብ መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአንድ ከተማ መኖርና ተወልዶ ማደግ ልክ እንደ ሌላው አካባቢ ሁሉ ከቦታው ጋር የሚያቆራኝ የባለቤትነት (የራሴ ነው) የሚል ስሜት የሚፈጥር ነው ይሉታል፡፡
የፈለገውን ያህል የደሃ ሠፈር አንድ አካባቢ ቢባልም ሆነ በከተማ ማዘመን ስም ይፍረስ ተብሎ የሚፈረድበት የፈለገውን ያህል ጭርንቁስ ቢሆንም የእኔ ሠፈር ነው የሚለውና የሚኮራበት ነዋሪ አለው፡፡ ያን ደሳሳ ሠፈር መለያ ማንነቱ አድርጎ ስሙን በኩራት የሚጠራው ሕዝብ መኖሩ ሁሌም መረሳት የለበትም ይላሉ፡፡
የደሃ የሚባሉ ሠፈሮችም ሆነ የተለያዩ የከተማ አካባቢዎች ከማንነታቸው ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው ሰዎች ምልክት የሚያደርጓቸው መሆናቸውን በማስታወስም እነዚህን ሠፈሮች በጅምላ ከማፍረስና ለከተማው አዳዲስ ቅርፅና ማንነት ከማበጀት ይልቅ ነባሩን ሠፈር ከእነ ነባርነቱ ማዘመንን ታሳቢ ያደረገ ሚዛኑን የጠበቀ የከተማ ልማት ሥራ እንዲካሄድ ይመክራሉ፡፡ ሕይወት የሌላቸው በጡብ ድርድሮች የሚሠሩ ዘመናዊና ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ያላቸውን መንደሮች ከማስፋፋት ጎን ለጎን ነባሩን የኢትዮጵያዊያን የአኗኗር እሴት የተከተለ ከተማ ልማት ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ ይሞግታሉ፡፡