April 12, 2024 – Konjit Sitotaw
ብሪታንያ፣ በኦነግ አመራር አባል በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ “አስቸኳይ”፣ “ገለልተኛ” እና “ሙሉ” ምርመራ እንዲደረግና የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲኾኑ ጠይቃለች።
በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ዳረን ዌልች፣ በግድያው ዙሪያ “ፍትህ እና ተጠያቂነት” እንዲሰፍን አሳስበዋል።
በኦሮሚያ ክልል በሲቪሎች ላይ የሚፈጸመው ግድያ እንዲያበቃ፣ ፖለቲካዊ ንግግር ማድረግ ቁልፉ ርምጃ እንደኾነም አምባሳደር ዌልች በ”ኤክስ” (ትዊተር) ገጻቸው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ የላይኛው ሕግ አውጭ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ቤን ካርዲን፣ በኦነግ አመራር በቴ ኡርጌሳ ግድያ ዙሪያ ዓለማቀፍ መርማሪ አካል “ተዓማኒ”፣ “ገለልተኛ” እና “ጥልቅ” ምርመራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዲፈቅዱ ጠይቀዋል። ሴናተር ካርዲን፣ የበቴ ኡርጌሳ ግድያ “አስደንጋጭ” እና “የሚረብሽ” እንደኾነ ገልጸዋል። በኦሮሚያ ክልል ከሕግ ውጭ የኾኑ ግድያዎች፣ ማንገላታት እና ፖለቲካዊ አፈና ተንሠራፍቷል ያሉት ሴናተር ካርዲን፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት በፖለቲካ ተቃዋሚዎችና መገናኛ ብዙኀን ላይ በኦሮሚያ ክልል ብቻ ሳይኾን በመላው ኢትዮጵያ ይፈጽመዋል ያሉት “የማሳደድ” እና “የአፈና” ድርጊት በአገሪቱ አለመረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገ ይገኛል በማለት ወቅሰዋል። ሴናተር ካርዲን፣ በአገሪቲ የጭቆናና አፈና ፖሊሲ አራማጆችና የመብት ጥሰት ፈጻሚዎች መጋለጥና ተጠያቂ መኾን አለባቸው በማለትም አሳስበዋል።